Search

Monday, April 20, 2015

የምናዝነው ስንት ሰው ሲሞት ነው? - by daniel kibret - free to SHARE SHARE

የምናዝነው ስንት ሰው ሲሞት ነው?

በየመን፣ በደቡብ አፍሪካና በሊቢያስለሚሞቱት ዜጎቻችን የሚሰጡት መንግሥታዊ መግለጫዎች ሁለት ነገር የጎደላቸው ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ሰብአዊ ስሜት፡፡ ማንኛውም ሰብአዊፍጡር ስለሌላው ሰብአዊ ፍጡር መከራና ስቃይ ሲሰማ መጀመሪያ አንዳች የኀዘን ስሜት ይሰማዋል፡፡ ከዕውቀት ይልቅ ስሜት ለሰዎች ቅርብነውና፡፡ ባለሥልጣን ቢሆን፣ ፖሊስ ቢሆን፣ ዳኛ ቢሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሆን ሰው ነውና ስሜት አለው ተብሎ ይታሰባል፡፡ ያዝናል፣ይከፋዋል፣ ልቡ ይረበሻል፣ ሆዱ ይባባል፣ ኅሊናው ይደማበታል ተብሎ ይታመናል፡፡ ስለዚህም የመጀመሪያው ሥራው ማዘን ቀጥሎም ኀዘኑንበወጉ መግለጥ ነው፡፡


ሰሞኑን የማያቸው መግለጫዎቻችንግን የኀዘን ወግ በሀገራችን የሌለ የሚያስመስሉ ናቸው፡፡ መሪዎቻችን ወደ አደባባይ ወጥተው ለሞቱት ወገኖቻችን እንደ ኢትዮጵያዊነትኀዘናቸው የሚገልጡት፣ ጥቁር ልብስ ለብሰው የምናያቸው፣ ነጠላ የሚያዘቀዝቁት ስንት ሰው ሲሞትብን ነው? የሚያስብሉ ናቸው፡፡ ኀዘንኮፖለቲካ አይደለም፣ ፓርቲ አይደለም፣ ርእዮተ ዓለም አይደለም፣ ሊብራልም አብዮታዊ ዲሞክራሲም አይደለም፡፡ ኀዘን ሰብአዊነት ነው፡፡የሚመራቸው ዜጎቹ፣ የሚያሠማራቸው በጎቹ ሲታረዱና ሲሞቱ ኀዘኑን በይፋ የማይገልጥ መሪና እረኛ መቼ ነው ኀዘኑን የሚገልጠው?


ዜጎቹ በሕገ ወጥ መንገድም ይሂዱበሕጋዊ፣ ድንበር ጥሰውም ይሂዱ በአውሮፕላን ተሳፍረው፤ መጀመሪያ ሰዎች፣ ቀጥሎም የዚህች ሀገር ዜጎች ናቸውና ኀዘን ይገባቸዋል፡፡ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ሰው አገኘዋለሁ ብሎ ከሚያስበው ክብር አንዱ በሞቱ ጊዜ የክብር ልቅሶና ኀዘን ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ከአካባቢያቸውላለመራቅ፣ ከራቁም ለመመለስ ከሚሰጧቸው ምክንያቶች አንዱ ‹በክብር ዐርፎ በክብር መቀበርን፣ የክብር የኀዘን ሥነ ሥርዓትን ማግኘትን›ነው፡፡
ካገሬ እንዳወጣህ አገሬ መልሰኝ
በሹም የታዘዘ አፈር አታልብሰኝ፤
እንኳን የሚቀብረው የሚያዝንለትአጣ
ምን ወግ ማረግ ያያል ካገሩ የወጣ፤
የሚሉት ለዚህ ነበረ፡፡


የመንግሥት አካላት ለምን ይኼንንለመዘንጋት እንደፈለጉ አልገባኝም፡፡ የደቡብ አፍሪካው ቃጠሎና ግድያ ሲመጣ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር ብቅ ብለው ‹‹በወገኖቻችንላይ እየደረሰ ባለው ነገር ከልብ እናዝናለን፣ ከደቡብ አፍሪካ መንግሥት ጋር ተነጋግረን አስፈላጊውን እናደርጋለን፤ ተመሳሳይ ችግርለወደፊቱ እንዳይከሰትም አንሠራለን› ዓይነት ሰውነት ያለበት መግለጫ ጠብቄ ነበር፡፡ የለም፡፡ ሲሆን በሀገራችን የልቅሶ ሥነ ሥርዓትመሠረት፡፡ አሁን ደግሞ ዓለም ያወቀው አሸባሪ ‹አይ ሲስ› ኢትዮጵያውያኑን በክርስትና እምነታቸው ብቻ ሲሠዋቸው የተሰጠው መግለጫስሜት የሌለበት፣ ማዘን መደሰታቸውን የማይገልጥ፣ እንኳን ሰው እንስሳ የሞተብን የማያስመስል ሆነ፡፡ ከማጣራቱም ከምኑም በፊትኮስሜቱ ይቀድማል፡፡፡ አዝናችኋል ወይ? ስትሰሙና ስታዩ ምን ተሰማችሁ? የአሜሪካ መንግሥት እንደዚያ ዓይነት መግለጫ ሲያወጣ ከኢትዮጵያመንግሥት ያንን ነው ወይ መስማት ያለብን? ለመሆኑ መሪዎቻችን ኀዘናቸውን የሚገልጡት ምን ስንሆን ነው? ለምንድን ነው ሁሉም ነገርፖለቲካ የሚሆነው?


ሁለተኛው የሚጎድለው ነገር ደግሞፍጥነት ነው፡፡ አትሌቶቻችን በኦሎምፒክ ሲያሸንፉ የባለሥልጣናቱ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልእክት ሯጮቹ ቆርጠውት ካለፉት ሪቫን ቀጥሎየሚመጣ ዜና ነበር፡፡ አትሌቶቹ ደክሟቸው ከመሬት ሳይነሡ የባለሥልጣናቱ መልእክት ለሚዲያ ይደርስ ነበር፡፡ በዚህ የሁላችንም ኀዘንበሆነው ጉዳይ ግን ለምን መዘግየት እንደተመረጠ ግልጽ አይደለም፡፡ ማጣረቱ፣ መረጃ መሰብሰቡ፣ ተጨማሪ የዲፕሎማሲ ሂደቶችን መሄዱጊዜ ይወስዳል፡፡ ማዘን ግን ጊዜ አይወስድም፡፡ ቪዲዮው ተለቅቋል፡፡ ሲሞቱ እያየን ነው፡፡ መልካቸው የኛው ነው፡፡ አይሲስ የገደላቸው‹ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች› ብሎ ነው፡፡ የዓለም ሚዲያዎች ያንኑ እያስተጋቡ ነው፡፡ ይኄ ለኀዘን ያንሳል? አፈፍ ብሎ ተነሥቶ‹በሆነው ነገር እናዝናለን፤ ልባችን ተነክቷል፤ ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን እንመኛለን፤ዝርዝሩን በየጊዜው እንነግራችኋለን› ለማለትስንት ሰዓት ይወስዳል? የደቡብ አፍሪካው ችግር ደረሰ እንደተባለ ሙጋቤን ለውግዘት የቀደማቸው የለም፡፡ የኛዎቹስ የት ሄዱ?


መንፈሳዊ መሪዎችስ የት ናቸው?አንዳንዶቹ ውጭ ሀገር መሆናቸው እየተሰማ ነው፡፡ ሲሆን ይህንን ሲሰሙ አቋርጦ መምጣት፤ ካልሆነም ባሉበት ሆኖ አባታዊ ኀዘንን መግለጥናበእምነቱ የሚገባውን ማድረግ ይገባ ነበር፡፡ ሲኖዶሱስ ምን እየሠራ ነው? አልሰማም ይሆን? ዛሬ ጠዋት ቢያንስ በአዲስ አበባ አብያተክርስቲያናት ጸሎት መደረግ አልነበረበትም? ባፈው ካይሮ ሄዳችሁ ከግብጽ ቤተ ክርስቲያን ምንድን ነው ያያችሁት? በጎቹ እረኛ የላቸውምማለት ነው? አባቶች የሚያዝኑት ምን ሲገጥማቸው ነው? እረኛው የሚያለቅሰው ስንት በጎች ሲታረዱ ነው?


ቤተ ክርስቲያኒቱ ነገሩን በዝምታየምታልፈው ከሆነ እኛ እንደ ጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን ትውፊታዊ ቀኖና እነዚህን በክርስትናቸው  ምክንያት የተሠው ክርስቲያኖች ‹ሰማዕታተ ሊቢያ› ልንላቸው ይገባል፡፡ የሰማዕትነታቸውንምበዓል ማክበር አለብን፡፡ በስንክሳሩ ማስገባት ባንችል ታሪካቸው በኅዳጉ ማስፈር አለብን፡፡ ማንም ይሁኑ ማን፣ በሚገባ የተማሩምይሁኑ ያልተማሩ፣ ከመካከላቸው የማያምኑም እንኳን ቢኖሩ የተገደሉበት ምክንያት ክርስትና ነውና ሰማዕታት ናቸው፡፡ ያውም ‹ኢትዮጵያውያንሰማዕታት›፡፡ በስንክሳሩ እንደምናነበው በዲዮቅልጥያኖስ ዘመን የክርስቲያኖች መንደርና ቤተ ክርስቲያን እየተወረረ ክርስቲያኖቹ ሲሠውገና ያልተጠመቁት፣ ነገሩ ያልገባቸው፣ ክርስትናን ለመቀበል ያልወሰኑት ሁሉ አብረው ተሠውተዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ግን የተሠውበትምክንያት ክርስትና በመሆኑ ሁሉንም ሰማዕታት ብላቸዋለች፡፡ የእነዚህም ክብር እንዲሁ ነው፡፡


እነርሱ በሰማይ ዋጋ አላቸው፡፡አክሊለ ሰማዕታትንም ተቀብለዋል፡፡ እኛ ግን ሰማዕታቱን ባለማክበራችን ክብር ይጎድልብናል፡፡ ‹በረከታቸው ይደርብን› እንጂ ‹ነፍስይማር› አንልም፡፡  


No comments:

Post a Comment