Search

Friday, April 17, 2015

ከደቡብ አፍሪካ ወደ አገራቸው መመለስ ለሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ ለማድረግ መንግስት ዝግጁ ነው - ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም


በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ በዚያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ከጥቃት ለመጠበቅ ሙሉ ጊዜውን ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የውጭ  ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ገለፁ።
ሚኒስትር እንዳሉት ኢምባሲው ጉዳዩ እልባት በሚያገኝበት ሁኔታ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል።

ዶክተር ቴድሮስ ከደቡብ አፍሪካ ወደ አገራቸው መመለስ ለሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ ለማድረግ መንግስት ዝግጁ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የውጪ ጉዳይ ሚንስትሩ የደቡብ አፍሪካ አቻቸውን ጨምሮ ከሌሎች የደቡብ አፍሪቃ አመራሮች ጋር መምከራቸውን እና ችግሩን ለመቅረፍም እየተሰራ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት።

“የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር በተፈጠረው ሁኔታ በጣም ማዘናቸውን እና አገሪቱ በድርጊቱ ሀፍረት እንደተሰማት ገልፀውልኛል” ነው ያሉት ዶክተር ቴድሮስ።

“ኢትዮጵያውያን ደቡብ አፍሪካ ቤታቸው እንደሆነች እና በነፃነት ትግላችን ወቅት ከኢትዮጵያውያን የተደረገልን ድጋፍም መቼም ቢሆን አንረሳም” ብለዋል ሚኒስትሯ።

በመሆኑም የደቡብ አፍሪካ መንግስት ለኢትዮጵያውያንና ለሌሎች የውጪ አገራተ ዜጎች ተገቢውን ከለላ እና ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም እና የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሚ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በደቡብ አፍሪካ ውስጥ በአፍሪካውያን ስደተኞች ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት ማውገዛቸው እና የደቡብ አፍሪካ መንግስትም ጥብቅ እርምጃ እንዲወስድ መጠየቃቸው ይታወሳል።


በሳሙኤል ዳኛቸው

No comments:

Post a Comment