Search

Wednesday, April 29, 2015

የቤት ዕድለኞች ውል ለመዋዋል ሊያሟሉ የሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21፣ 2007(ኤፍ.ቢ.ሲ) በ10ኛው ዙር የቤት ዕጣ የወጣላቸው ባለዕድለኞች ከዛሬ ጀምሮ ውል መዋዋል እንደሚጀምሩ የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ አስታውቋል።
የቤት ባለእድለኞቹ ውል ለመዋዋል ሲሄዱም ማሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎችን ኤጀንሲው አስታውቋል።
ወል ለመዋዋል የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችም፦ የቤት ፈላጊነት ምዝገባ ያካሄዱበት ማረጋገጫ፣ ወቅታዊ ወይም የታደሰ መታወቂያ፣ ባለትዳር ከሆኑ ያገባ የምስክር ወረቀት፣ ባለትዳር ካልሆኑ ያላገባ የምስክር ወረቀት፣ ትዳራቸው በፍቺ የተቋጨ ከሆነም ህጋዊ የፍቺ ወረቀት፣ የትዳር አጋራቸው በመጥፋት ወይም በተለያዩ ምክንያት በአካባቢው ላይ የሌሉ ከሆነ ደግሞ በፍርድ ቤት አሳውጀው ማረጋገጫ ማምጣት ይጠበቅባቸዋል ተብሏል።
የትዳር ሁኔታ የሚያሳይ የምስክር ወረቀት ወይም ማረጋገጫ ያስፈለገው የቤት ባለእድለኞቹ የባንክ ብድር በሚበደሩበት ጊዜ ሁለቱም የትዳር አጋሮች እኩል መብት ስላላቸው እንደሆነ ኤጀንሲው አስታውቋል።
ክፍያውን ሙሉ በሙሉ በአንድ ጊዜ የሚከፍሉ የቤት ባለእድለኞች ግን ይህንን የማሟላት ግዴታ የለባቸውም።
አንድ ሰው የቤት ባለመብት የሚሆነው እጣ ስለወጣለት ብቻ ሳይሆን የሚጠበቅበትን ቅድመ ሁኔታዎች አሟልቶ ውል ሲዋዋል ስለሆነ የቤት እድለኞች በንቃት ሊሳተፉበት ይገባልም ተብሏል።
ዕድለኞች ውል የሚዋዋሉት ዕጣው በወጣላቸውና ቤቱ በሚገኝበት ክፍለ ከተማ መሆኑንም ኤጀንሲው አስታውቋል።
ኤጀንሲው በአስሩም ክፍለ ከተሞች ውል መፈራረሚያ ጣቢያዎችን ያቋቋመ ሲሆን፥ በእያንዳንዱ ጣቢያም ከ30 በላይ ባለሙያዎች የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲሰጡ ተመድበዋል።
የቤት እጣ የወጣላቸው ባለእድለኞችም የሚጠበቅባቸውን መረጃዎች አሟልተው ከተገኙ ውሉን በ15 ደቂቃ ውስጥ እንደሚፈራረሙ የኤጀንሲው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ መስፍን መንግስቱ ተናግረዋል።
ውል የማሰሩ ስራ ለተከታታይ 60 የስራ ቀናት የሚቀጥል ሲሆን፥ በማንኛውም ምክንያት ውል ሳይፈጽሙ ለቀሩ ዕድለኞች የሚራዘም ቀን አለመኖሩን ዋና ስራ አስኪያጁ ገልፀዋል።
ዕድለኞች ውል በፈጸሙ በአጭር ጊዜ ውስጥ የቤት ቁልፋቸውን ይረከባሉ ተብሏል።
በአስታርቃቸው ወልዴ

የተጫነው፦ በሙለታ መንገሻ
source : FBC

No comments:

Post a Comment