Search

Friday, April 3, 2015

Health: ‹‹በአውቶብስ በተጓዝኩ ቁጥር የሚያመኝ ለምን ይሆን?”

ሥራዬ ንግድ ሲሆን በየጊዜው ከከተማ ከተማ እመላለሳለሁ፡፡ በዚህም ሳቢያ በትራንስፖርት ረዥም ጉዞ በተጓዝኩ ቁጥር እየታመምኩ ተቸግሬያለሁ፡፡ ማቅለሽለሽ፣ ማላብ፣ ትውከት፣ ድካም በተጓዝኩ ቁጥር የሚያስቸግሩኝ ስሜቶች ናቸው፡፡ አሁን አሁን በመጠኑ እየቀነሰልኝ መጣ እንጂ ንግዱን የጀመርኩ ሰሞንማ ደጋግሞ ያስታውከኝ ስለነበር፡፡ ተጓዥ የሆንኩ ቀን በፍራቻ ምግብም አልበላም ነበር፡፡ እናም በሽተኛ መስዬ ነበር ጉዞውን የማገባድደው፡፡ አንዳንድ ተሳፋሪዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ ሲቸገሩ አይቻለሁ፡፡ ህመሙ መድሃኒት አለው ሲሉ ብሰማም ተጠራጠርኩ፡፡ ያለ ሐኪም ትዕዛዝ መውሰድም ፈራሁ፡፡ አሁን ግን ጉዳዩን ለእናንተ ማማከር አይነተኛ መፍትሄ ሆኖ ታየኝ፡፡ ለሚከተሉት ጥያቄዎቼ ሙያዊ ትንተና ስጡኝ፡፡
ለመሆን ይህ ችግር በህክምናው ዓለም የሚታወቅ በሽታ ነው? ከሆነስ መንስኤውና መፍትሄው ምን ይሆን? ለመሆኑ አንዳንዶቹን ብቻ የሚያጠቃበት ምክንያትስ ምንድነው? ችግሩን የሚያባብሱ ነገሮች ካሉ ብትጠቁሙኝ? መድሃኒት አለው የሚባለውስ ምን ያህል እውነት ነው? እባካችሁ በቂ ማብራሪያ በመስጠት እኔንና መሰሎቼን ታደጉን፡፡ አሊያም በጉዞ ሽሽት ስራ መቀየሬ ነው፡፡
የዘወትር አንባቢያችሁ አብደላ ያሲን ነኝ
auto bus
መልስ: ውድ አንባቢያችን እንኳን ከአንባቢነት ወደ ተሳታፊነት ተሸጋገርክ፡፡ እስካሁንም ይህን ያክል እየተቸገርክ መቆየት አልነበረብህም፡፡ በአቅራቢያህ ወደሚገኝ የጤና ባለሙያ ሄደህ ችግርህን ብታማክር ኖሮ ድሮውኑ መፍትሄ ታገኝ ነበር፡፡ ወይም እኛን ለማማከር ቀደም ብትል ኖሮ ጉዞህን አዝናኝ ባደረግክ ነበር፡፡ የዘወትር አንባቢያችን በመሆንህ በተመሳሳይ የጤና ችግሮች ዙሪያ መፍትሄ ስንሰጥ መቆየታችንን ታውቃለህና፡፡ ‹‹ላለፈ ክረምት ቤት አይሰራምና›› አሁንም ዘይደሃል፡፡
ከገለፃህ እንደተረዳነው በመጓጓዣ ረዥም ጉዞ በሚደረግበት ወቅት የሚያጋጥም የጉዞ ህመም/በሽታ እየተሰቃየህ መቆየትህን ነው፡፡ በህክምናው ዓለም በደንብ የሚታወቅና መፍትሄም ያለው ችግር ነው፡፡ ፈረንጆቹ (Motion Sickness) ይሉታል፡፡ የጉዞ ህመም እንደማለት፡፡ ስለ በሽታው መንስኤና ምንነት ከመዘርዘራችን በፊት የሰውነታችንን እንቅስቃሴና ሚዛን የሚቆጣጠሩ የአካል ክፍሎችና አሰራራቸውን በተመለከተ ጥቂት ማለትን ወደድን፡፡
የአካል ክፍሎቻችንም ሆኑ አጠቃላይ ሰውነታችን እርስ በርሳቸውም ሆነ በአካባቢው ውስጥ (Special position) ያሉበት ቦታ፣ የእንቅስቃሴ አቅጣጫ፣ ፍጥነትና ሁኔታ ሚዛኑን የጠበቀ ለማድረግ (body equilibrium) የሚሰራ ራሱን የቻለ አካላዊ ስርዓት አለ፡፡ “Vestibular system” ይባላል፡፡ በዚህ ስርዓት ውስጥ ዋነኞቹ ተሳታፊዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡ በፈሳሽ የተሞሉና የተጠላለፉ ትናንሽ ቱቦዎች ያሉት የጆሮአችን የውስጠኛው ክፍል (Vestibular/Labyrinthine system) አንዱና ዋነኛው ሲሆን ተግባሩም የአካል ክፍሎቻችንን በተለይም የጭንቅላታችንን የእንቅስቃሴ አቅጣጫ መጠቆም ነው፡፡ አይኖቻችን ደግሞ ሰውነታችን ያለበትን ቦታና ከቦታው አንፃር የምናደርገውን የእንቅስቃሴ አቅጣጫ ይዘግባል፡፡ ለማን? ለዋናው ተቆጣጣሪ አለቃ አንጎል፡፡ በቆዳ፣ በጡንቻና በአጥንት መገጣጠሚያዎች ላይ የሚገኙ የቦታና የግፊት ተቀባይ ጣቢያዎች (Position and pressure rectors) በበኩላቸው የትኛው የአካል ክፍል መሬት ላይ እንዳለ እና የትኛው እንቅስቃሴ ላይ እንዳለ ሪፖርት የሚያደርጉ ናቸው ለበላያቸው፡፡ ከእነዚህ ንዑስ ክፍሎች የሚመጡለትን መረጃዎች በማዋሃድ አጠቃላይ መልዕክቱ ትክክለኛ ስዕል እንዲኖረው የሚያቀናጀው ዋነኛ ክፍል ያለው አንጎል ነው፡፡ ዋናው አለቃ በአንጎል ውስጥ ለዚህ ስራ የተመደቡ ልዩ ጣቢያዎች ሲኖሩ ዋነኛው (Basis points Cerebellum) በመባል ይታወቃል፡፡ ይህም ክፍል ከሌሎች ንዑስ ክፍሎች ጋር የጠበቀ ግንኙነት አለው፡፡ የእነዚህ ንዑስ ክፍሎች ተቀናጅቶ አለመስራት እና የስርዓቱ መፋለስ ሰውነት ሚዛንን ጠብቆ መንቀሳቀስ እንዳይችል ያደርጋል፡፡ እንዲሁም የአካል ክፍሎች ያሉበትን ቦታ፣ እንቅስቃሴያቸውንና ከሰውነት ሚዛን ጋር ያላቸውን መስተጋብር ያፋልሳል፡፡ በዚህም “Body Disequilibrium” ይከተላል፡፡ መገለጫዎቹም የራስ ማዞር ስሜት፣ ሚዛንን ስቶ መውደቅ፣ ዙሪያችን የሚሽከረከር መምሰል (Illusion) ብዥታ፣ የጆሮ ውስጥ መጮህ ስሜት፣ ማቅለሽለሽ፣ ራስ ምታት፣ ትውከት፣ ማላብ፣ ድካም፣ በአጠቃላይም ያለመመቻቸትና የህመም ስሜት፣ መጨናነቅ የመሳሰሉት ናቸው፡፡
ለዚህ የሚዳርጉ ብዙ የጤና ችግሮች አሉ፡፡ በአጠቃላይ ግን ከላይ የተጠቀሱት ንዑስ ክፍሎች ላይ የሚከሰቱ ኢንፌክሽኖች፣ ለእነዚህ የአካል ክፍሎች የሚደርሰው የደም አቅርቦት ዝውውር ማነስ፣ ‹‹አለርጂ›› እና የነርቭ በሽታዎች ዋነኛ መንስኤዎች ናቸው፡፡ የጉዞ ህመምም የአካል ክፍሎችን እንቅስቃሴና አንፃራዊ ሚዛን የሚጠብቀውን የዚህ ስርዓት መዛባት ሳቢያ የሚከሰት ህመም ነው፡፡ የሚከሰተውም በረጅም ጉዞ ወቅት ወይም በማይመቹ ፈጣን እንቅስቃሴዎች (ለምሳሌ ሰውነትን ወይም ጭንቅላትን በተደጋጋሚና በፍጥነት ማሽከርከር) አማካይነት ሲዛባ የሚመጣ በሽታ ነው፡፡
ውድ ጠያቂያችን አብደላ ታዲያ ጉዞ እንዴት አድርጎ ነው ይህን መፋለስ የሚያስከትለው? ማለትህ አይቀርም፡፡ ጥሩ ብለሃል፡፡ ወይስ አላልክም? ለማንኛውም ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ከላይ እንደተብራራው ካለንበት አካባቢ አንፃር እያንዳንዱ የአካል ክፍሎቻችንም ሆኑ መላው ሰውነታችን ያለበትን ቦታ፣ እየተንቀሳቀሰ መሆን አለመሆኑን፣ እንዲሁም የእንቅስቃሴው አቅጣጫ፣ ፍጥነት እና አይነት በተመለከተ ከየክፍሎቹ የሚመጣለትን መረጃ በማቀናጀት ትርጉም እንዲኖረውና ሚዛናዊ እንዲሆን የሚያደርገው አንጎል ወይም ማዕከላዊ የነርቭ ስርዓት ነው ብለናል፡፡ ሆኖም ግን አንጎል ከየንዑስ ክፍሎቹ የሚደርሰው መረጃ የተዛባና አንዱ ከአንዱ ጋር የሚጋጭ ከሀነ፣ አቀናብሮ ትክክለኛው ትርጉሙ የመስጠትና ትክክለኛውን አካላዊ ሚዛና የማስጠበቅ ኃላፊነቱን መወጣት ይሳነዋል፡፡ የተዛባ መረጃ የተዛባ ውጤት ያስከትላልና፡፡ ወደ ጉዞው ልመለስ፡፡
ለዚህ የመረጃ መጣረስ ዋነኛው መንስኤ የማይመች ረጅም ጉዞ ወይም ተደጋጋሚ ፈጣን እንቅስቃሴ መሆኑን ይበልጥ ግልፅ ለማድረግ በምሳሌ እንየው፡፡ እንበል ሴትየዋ በመኪና ውስጥ እየተጓዘች መጽሐፍ ታነባለች፡፡ የሰውነት ክፍሎቿ ያሉበትን ቦታና እንቅስቃሴያቸውን በሚመለከት ለይተው መረጃ የሚሰጡት የጡንቻና የመገጣጠሚያ ንዑስ ጣቢያዎች ሴትየዋ በመኪናው ውስጥ እየተንቀሳቀሰች/እየተከዘች መሆኑን ይዘግባሉ፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ከዓይኖቻችን ወደ አንጎል የሚደርሰው መልዕክት እንቅስቃሴ ላይ መሆኑን ሳይሆን ቁጭ ብላ እያነበበች መሆኑን ነው፡፡ እነዚህ ተጻራሪ መረጃዎች የደረሱት የአንጎል ክፍልም ግራ በመጋባት የሚዛን መዛባት ያስከትላል፡፡ በተመሳሳይም ተጓዡ ዓይኑ የሚያይበት አቅጣጫና መጓጓዣው የሚጓጓዝበት አቅጣጫ የተለያየ መሆንም (ለምሳሌ ተሽከርካሪው ወደፊት ሲጓዝ መንገደኛው ግን በመስተዋት ወደ ጎን ወይም ወደኋላ የሚያይ ከሆነ) ተመሳሳይ ውጤት ያስከትላል፡፡ ውጤቱም የጉዞ በሽታን ያስከትላል፡፡
በሽታው በየትኛውም መጓጓዣ ብንጓጓዝ ሊከሰት ይችላል፡፡ ማለትም በመኪና፣ በአውሮፕላን፣ በመርከብ፣ በባቡር ብሎም በጋማ ከብትም ቢሆን ረጅም ርቀት ስንጓዝ ሊከሰት ይችላል፡፡ ችግሩ በጣም የተለመደ ከመሆኑም በላይ ማንኛውም ሰው ላይ ሊከሰት ይችላል፡፡ በተለይም ከ5-12 ዓመት የዕድሜ ክልል ላይ ያሉ ህፃናት፣ ሴቶችና በዕድሜ ጠና ያሉ ሰዎች ይበልጥ ተጋላችነት አላቸው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ግን ጭራሽ ችግሩ ላያጋጥማቸው ይችላል፡፡
ውድ ጠያቂያችን በአንተም ላይ እንደተከሰተው የዚህ በሽታ ዋነኛ መገለጫዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡ የበሽታው ምልክቶች ከላይ የተዘረዘሩት ናቸው፡፡ እንደ ተጓዡ የእነዚህ ምልክቶች መጠንና ተፅዕኖ ሊለያይ ይችላል፡፡ ብዙዎች ቀለል ያሉ ምልክቶች ሊታገስላቸው ይችላል፡፡ በተደጋጋሚ ረጅም ጉዞ በማድረግም አንጎላችን ከሁኔታው ጋር ሲላመድ ችግሩ ሊቃለል ብሎም ሊጠፋ ይችላል፡፡ ጠያቂያችንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ችግሩ እየቀለለልህ መሄዱም ይህን ይጠቁማል፡፡ በአንፃሩ አንዳንዶች ችግሩ ሊጠናባቸው እና ለተደጋጋሚ ትውከት፣ በዚህም ሳቢያ ለአሳሳቢ የሰውነት ፈሳሽ እጦት ብሎም ለደም ግፊት ዝቅ ማለት ሊዳርጉ ይችላሉ፡፡ እነዚህ አይነቶቹ ተሳፋሪዎች የባለሙያ እገዛ ያሻቸዋል፡፡ በተጨማሪም አንዴ እንዲህ በጠና የታመመ ተጓዥ በሌላ ጊዜ ገና ጉዞ ከመጀመሩ በፊት ለመጓዝ ሲያስብ ማቅለሽለሽ ይጀምረዋል፡፡ ‹‹እባብን ያየ ብልጥ በረየ!›› መሆኑ ነው፡፡ ከጉዞው በኋላ ለማገገም ሰዓታትን ከከፋም ቀናትን ሊፈጅ ይችላል፡፡ ፍርሃትና ጭንቀት መጥፎ ጠረን (የቤንዚንና የመኪና ጢስ ሽታ)፣ መተፋፈግ፣ የአልኮል መጠጥ፣ አነቃቂ መድሃኒቶች፣ ምግብ አለመብላት ወይም ከመጠን በላይ መብላት ችግሩን የሚያባብሱ ነገሮች ናቸው፡፡
ውድ አብደላ ስለ ችግሩ ይህን ያህል ካልን ወደ መፍትሄዎቹ እናምራ፡፡ ችግሩ በህክምና መፍትሄ አለው፡፡
የመጀመሪያው የመፍትሄ እርምጃ እንደማንኛውም የጤና ችግር መፍሄት ያለውና ልንከላከለው የምንችለው በሽታ መሆኑን መገንዘብና ራስን ማዘጋጀት ነው፡፡ በተጨማሪም የሚከተሉትን ተግብር፡፡
– አጋላጭና አባባሽ ሁኔታዎችን ማስወገድ ያሻል
– በተቻለ መጠን ብዙ እንቅስቃሴ የሌለበትና ምቹ የሆነ መቀመጫን ይምረጡ፡፡ መኪና ላይ ከሆነ ፊት ለፊት ተቀምጦ ቀጥታ ወደ ፊት ብቻ ይመልከቱ፡፡ እንዲያውም ከተጓዥ ይልቅ ሹፌር መሆን ይመረጣል፡፡ አውሮፕላን ከሆነ ደግሞ ክንፎቹ አካባቢ መሆን ይመረጣል፡፡
– በመስኮት ወደ ጎን ወይም ወደ ኋላ መመልከትን ያስወግዱ፡፡ ከተቻለ አይንን መሸፈንና መተኛት ብልህነት ነው፡፡ በሚንቀሳቀስ ወይም ቅርብ ባለ ነገር ላይ አያፍጥጡ፡፡
– ማንበብ፣ ፊልም ማየት፣ ጌም መጫወት፣ አንገት እያዞሩ ማውራትን ያስወግዱ፣
– በባዶ ሆድ አይጓዙ፣ በጣምም ጠግበው አይብሉ፡፡ እንዲሁም ቅባትና ቅመም የበዛበት፣ የሚከብድ ምግብን ያስወግዱ፣ አጭር ጉዞ ከሆነ ባይመገቡ ይመረጣል
– በጉዞው ዋዜማ ‹‹አይጨብሱ›› ይልቅስ ጥሩ እንቅልፍም ያግኙ
– መስኮቶችን በመከፋፈት ንፁህ አየር እንዲዘዋወር ያድርጉ፣ (ሹፌሮችም ትርፍ ለማጋበስ ስትሉ መደራረቡን ተው)
– በመጨረሻም ‹‹አይጓዙ›› ልል አሰብኩና፣ ከቦታ ቦታ የመጓጓዝ መብትን መዳፈር ስለሆነብኝ ትቼዋለሁ፡፡
ከላይ የተጠቀሱት የማይከፈልባቸውና በቀላሉ ልንተገብራቸው የምንችላቸው መፍትሄዎች ናቸው፡፡ በተጨማሪም ረጅም ርቀት ለሚጓዙ የጉዞ በሽታ ተጠቂዎች ከጉዞ በፊት የሚወሰዱ ብዙ አማራጭ ፍቱን መድሃኒቶችም አሉ፡፡ መድሃኒቶቹ የሚሰሩት በአጠቃላይ ከእንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ወደ ዋናው አንጎል ክፍል የሚደርሱት መረጃዎች እንዳይደርሱ በማድረግ፣ አሊያም ቢደርሱም የሚያስከትሏቸውን ምልክቶች እንዳይከሰቱ በማገድ ወይም በመቀነስ የሚረዱ ናቸው፡፡ መወሰድ ያለባቸውም ጉዞው ከመጀመሩ ከ10-30 ደቂቃዎች በፊት መሆን አለበት፡፡ ሆኖም በጉዞው ወቅት ቢወሰዱም ጠቃሚ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ያለ ሐኪም ትዕዛዝ በየትኛውም መድሃኒት ቤት ‹‹ለጉዞ ህመም የሚሆን ክኒን ይኖራል?›› ብለው ቢጠይቁ፣ ባለሙያዎቹ ከነአወሳሰዱ ነግረው ይሰጥዎታል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ በነርቭ ስርዓት ላይ ባላቸው አንፃራዊ ተፅዕኖ ሳቢያ ያለ ሐኪም ትዕዛዝ አይሰጡም፡፡
የትኛው መድሃኒት፣ ምን ያህል? ለማን? መቼ? እንዴት መወሰድ እንዳለበት እና መደረግ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች በአቅራቢያ ያለ ሐኪምን ወይም ፋርማሲስትዎን ያማክሩ፡፡
ይህን ካደረጋችሁ ጠያቂያችንም ሆኑ የጉዞ ህመም ሰለባ ከመሆናችሁ ስትቸገሩ የቆያችሁ አንባቢዎቻችን ከእንግዲህ ከችግርና ‹‹ከፌስታል›› የፀዳ ጉዞ እንደምታደርጉ እሙን ነው፡፡ መልካም ጉዞ፡፡

No comments:

Post a Comment