Search

Tuesday, September 24, 2013

የከተማ አስተዳደሩ በሚቀጥሉት 2 አመታት 130ሺ ቤቶችን ሊገነባ ነው

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ህዝቡን በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስክ የላቀ ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ከንቲባ ድሪባ ኩማ አስታወቁ፡፡

አስተዳደሩ ባለፉት ዓመታት ያከናወናቸውን የልማት ስራዎች በመገምገም ለቀጣዩቹ 2 ዓመታት ለሚተገብራቸው የልማት እቅዶች አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

ከንቲባ ድሪባ ኩማ እንደገለጹት አስተዳደሩ ለስራ እድል ፈጠራ፣ ለመኖሪያ ቤት ግንባታ፣ ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ፣ ለማስፈጸም አቅም ግንባታና ለመልካም አስተዳደር ስራዎች ቅድሚያ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በከተማዋ የሚታየውን ሰፊ የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለማሟላት በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ የተያዘውን 70ሺህ የመኖሪያ ቤት ግንባታ እቅድ ወደ 130ሺህ ከፍ በማድርግ የህብረተሰቡን የቤት ችግር ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ከንቲባ ድሪባ አስረድተዋል፡፡

አስተዳደሩ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት በጨርቃጨርቅ፣ በአግሮ ኢንዱስትሪ፣ በብረታብረትና በሌሎችም የማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፎች ሰፋፊ ኢንዱስትሪዎችን ከመካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ጋር በማስተሳሰር ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ እንደሚሰራም አመልክተዋል፡፡

አስተዳደሩ በትምህርት ፣በጤናና በሌሎችም የማህበራዊና መሰረተ ልማት ዘርፎች የከተማዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ለሚያስችሉ ስራዎች ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ነው የገለጹት፡፡

ከንቲባ ድሪባ እንዳሉት በመልካም አስተዳደር ረገድም የከተማዋ ነዋሪዎች በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በየዘርፉ ደረጃውን የተጠቀ አገልግሎት ማግኘታቸውን የሚያረጋግጥ ደረጃ ተዘጋጅቶ ባልተፈቱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ዙሪያ የተጠያቂነት አሰራር ተግባራዊ ለማድረግም ዝግጁ ነው፡፡

የከተማው አስተዳደር የኑሮ ውድነትን ለመፍታት በዋነኛነት ለስራ እድል ፈጠራ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው መንግስት በየዓመቱ በብዙ ሚሊዮን ብር ወጪ ወደሀገር ውስጥ የሚያስገባቸው የፍጆታ ዕቃዎች ስርጭትን ህብረተሰቡ በቅርበት እንደሚከታተላቸው በማድረግ የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎች ይሰራሉ ብለዋል፡፡

በአስተዳደሩ በማዕከል፣ በክፍለ ክተማና በወረዳ በየደረጃው የሚገኙ የአስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ተሳታፊ የሆኑበት የእቅድ ውይይት በየደረጃው ያሉ ሀላፊዎች፣ የመንግስት ሰራተኞችና ህዝቡ እንዲወያበት በማድረግ ወደ ተግባር እንደሚገባም አስታውቋል፡፡
Source - ERTA

Monday, September 23, 2013

የኬኒያ የፀጥታ ሀይሎች በዌስትጌት ታጋቾችን ለማስለቀቅ ዘመቻ ጀምሩ

ኬኒያ  መዲና ናይሮቢ የፀጥታ ሀይሎች በዌስትጌትየገበያ ማዕከል ውስጥ በአሸባሪ ቡድኑ አልሸባብ ታጣቂዎች ተይዘው የሚገኙ  ታጋቾችን ለማስለቀቅ ዘመቻ ጀምሩ ።
በአሁኑ  ወቅት  የፀጥታ ሀይሎቹ የገበያ ማእከሉን  የወረሩ ሲሆን ፥  ከስፍራውም የተኩስ ድምፅ  እየተሰማ ነው ።
ከ10 እስከ 15 የሚጠጉ የአልሸባብ ታጣቂዎች እስካሁን ከገበያ ማዕከሉ እስካሁን እንዳሉ ነው የተመለከተው።
ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ ጥቃት ፈፃሚዎቹን መንግስታቸው የገቡበት ገብቶ እንደሚይዛቸው ተናግረዋል።
አል ሸባብ  ለጥቃቱ  ሀላፊነቱን እንደሚወስድ አስታውቋል ።
ከከተማዋ  እየወጡ ያሉ ዘገባዎች  እንደሚያመለክቱት  እስካሁን  በሽብር ጥቃቱ 69 ዘጠኝ ሰዎች ተገድለዋል ።

በሶማሊያ  የሚገኘው የኬንያ ወታደራዊ ሀይል ጥቃትን ተከትሎ አልሸባብ በኬንያ ጥቃት ሊያደርስ እንደሚችል ለቢቢሲ መናገሩንም ዘገባው  አስታውሷል።
በደቡብ ሶማሊያ እ.እ.አ ከ2011 ጀምሮ አሸባሪውን አልሸባብ ለመታገል ከ4000 የማያንሱ የኬንያ ወታደራዊ ሀይል አባላት መሰማራታቸውንም ዘገባው አስታውሷል።

Thursday, September 19, 2013

ዋሊያዎቹ የአቋም መለኪያ ጨዋታ ሊያደርጉ ነው

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለብራዚሉ የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በጥቅምት 3 እና በህዳር መጀመሪያ ለሚጠብቀው የናይጀሪያ ወሳኝ ጨዋታ ለዝግጅት የሚረዳውን የአቋም መለኪያ ጨዋታ ከጋናና ካሜሮን ጋር ሊያደርግ እንደሚችል ተገልጿል፡፡
ሁለቱ ሀገሮች  ከኢትዮጵያ ጋር ለመጫወት ፈላጎት ማሳየታቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምክትል አሰልጣኝ አቶ ታረቀኝ አሰፋ ተናግረዋል፡፡
ጋናና ካሜሮን ወቅታዊ ብቃታቸው ጠንካራ የሚባል በመሆኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ላለበት ወሳኝ ጨዋታ ክፍተቱን ለመሙላት  ወሳኝ አጋጣሚ ይሆናል፡፡
ለወዳጅነት ጨዋታ የተመረጡት ሀገራት ከምዕራብ አፍሪካ መሆናቸው በአብዛኛው ከናይጀሪያ ጋር ተመሳሳይ የአጨዋውት ይዘት በመተግበር ለብሔራዊ ቡድኑ ሰፊ ልምድ እንደሚያካፍሉ ታምኖበት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከዛምያ ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ ሊያደርግ እንደሚችልም ተገልጿል፡፡     
የአቋም መለኪያ ጨዋታው መቸ እንደሚደረግ በትክክል ባይታወቅም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ልምምዱን ነገ  እንደሚጀምር ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አባላት ከድልድሉ በኋላ ናይጀሪያን አሸንፈው ታሪክ ለመስራት መነሳሳታቸውን እየገለጹ ነው፡፡
በአንጻሩ የናይጀሪያ ብሔራዊ ቡድን አባላት ኢትዮጵያን በቀላሉ አሸንፈው እንደሚያልፉ ቢናገሩም ንግግራቸው በአሰልጣኝ ስቴፈን ኬሽ አልተወደደላቸውም፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን አቅለን ወደ ሜዳ አንገባም፣ እነርሱ እዚህ የደረሱት ጠንክረው በመስራታቸው እንጅ በስህተት አይደለምሲሉ ስቴፈን ኬሽ ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡
በአዝመራው ሞሴ

ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገቡ ተማሪዎች ድልድል ይፋ ሆነ

በ2005 የትምህርት ዘመን የ12  ክፍል  የመሰናዶ  ፈተናን  ካለፉት 163ሺህ 406  ተማሪዎች መካከል  103 ሺህ 394 ተማሪዎች በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበዋል ።
ምደባው ዛሬ  በአገር አቀፍ የትምህርት ምዘና  ኤጀንሲ  የተማሪዎቹ  የዩኒቨርሲቲ  ድልደላ  ተካሂዷል ።
ተማሪዎችም የተመደቡበትን ዩኒቨርሲቲ  በኤጀንሲው ድረ ገፅ www.nae.gov.et በመግባት “placement result” የሚለውን  በመጫን መመልከት ይችላሉ ።
ወይም በአጭር የፅሁፍ መልዕክት plr ፅፎ  የመለያ  ቁጥርን በማስከተል ለ8181 በመላክ የተመደቡበትን ዩኒቨርሲቲ  ማወቅ  የችላሉ ብሏል ኤጀንሲው ።
ምደባው የተከናወነው የ70/30 ቀመርን ባሟላ  መልኩ ከጠቅላላ  ተፈታኞች  ደግሞ  40  በመቶዎቹ  በምህንድስና  ሳይንስ ዘርፍ እንዲገቡ ተደርጓል ።
በምደባው የሴቶችን ተሳትፍ  38 በመቶ  እንዲሆን ታሳቢ  ተደርጎ የተከናወነ ሲሆን ፥ የህክምና  ሳይንስን ምርጫቸው ያደረጉ  ተማሪዎች ደግሞ የመቁረጫ  ነጥብን  ለወንዶች 482  ለሴቶች ደግሞ 477 እንዲሆን  ተደርጓል ።
የምደባ  መመሪያው  በሚፈቅደው መሰረትም  የከፍተኛ  ትምህርት ተቋማትን የቅበላ  አቅምን ታሳቢ ተደርጎ ሴት ተማሩዎች ከወንዶች ጋር ተወዳድረው ከሚያገኙት በተጨማሪ 3 በመቶ እርስ በርሳቸው  ተወዳድረው ወደሚፈልጉት የትምህርት መስክ እንዲገቡ መደረጉን ነው  ኤጀንሲው የገለፀው ።
የሚያጠቡ እናቶች በአቅራቢያቸውና   ተመሳሳይ  ፆታ  ያላቸው  መንትያዎች በአንድ ቦታ እንዲመደቡ እንዲሁም ፥  የጤና  ችግር ያለባቸው  ባቀረቡት  ማስረጃ  መሰረት  ምላሽ  እንዲያገኙ  ተደርጓል ።
በዘንድሮው ድልደላ  በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የሴቶች  ቁጥር ተመጣጣኝ  እንዲሆን  ተደርጓል ።
በኮምፒውተር ታግዞ የተከናወነው ምደባ  የተማሪዎችን ውጤት ፣ የትምህርት መስክንና  የዩኒቨርሲቲ ምርጫን መሰረት በማድረግ  በውድድር ብቻ ተከናውኗል  ብሏል ኤጀንሲው ።
መቀሌ  ዩኒቨርሲቲ  7 ሺህ 312  ተማሪዎቸን  በመቀበል  ቀዳሚው  ሲሆን ፥ አዳማ   ዩኒቨርሲቲ 5 ሺህ 134  ተማሪዎች በመቀበል በሁለተኝነት ሲቀመጥ ፥  4 ሺህ 495 ተማሪዎችን የተቀበለው ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ  ሶስተኛ  ነው ።
ዝቅተኛ  ቁጥር  ያለው ተማሪ  የተቀበለው  ኮተቤ  መምህራን  ትምህርት  ኮሌጅ 955  ተማሪዎች  ተመድበውለታል ።

Tuesday, September 17, 2013

ስለሺ ደምሴ ጋሽ አበራ ሞላ "ያምራል ሀገሬ"ን የሙዚቃ አልበም በብሄራዊ ቴአትር አስመረቀ

ስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ) "ያምራል ሀገሬ"ን በብሄራዊ ቴአትር አስመረቀ
አዲሱ የስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ)"ያምራል ሀገሬ"የሙዚቃ አልበም ጋሽ ሙላቱ አስታጥቄ፤የትዝታው ንጉስ ሙሃሙድ አህመድ፤አብርሃም ወልዴ እና በርካታ የሙዚቃ ባለሙያዎች፤አድናቂዎች በተገኙበት በብሄራዊ ቴአትር ትናንት ምሽት ተመርቋል፡፡የምርቃት ስነ ስርዓቱ በግብዣ ለተጠሩ እንግዶች ብቻ በመሆኑ በርካቶች በቴአትር ቤቱ መግቢያ ላይ ለመግባት አሰፍስፈው አምሽተዋል፡፡
የምርቃት ስነ ስርዓቱን ድምፃዊት ዘሪቱ ጌታሁን ‘’እንቁጣጣሽ’’ በተሰኘ የአዲስ አመት ዜማዋ ከፍታዋለች፡፡ዘሪቱ ከአርባ አመታት በፊት ያቀነቀነችውን ዜማ ዛሬም ከባህላዊ የሙዚቃ ባንድ ጋር በመድረክ ስትጫወት ለታዳሚው የተለየ ደስታን ፈጥራለች፡፡ዛሬም ድረስ ሙሉ የመጫወት አቅሟ አብሯት መኖሩን አሳይታለች፡፡
የ ‘’ኢትዮ ጃዝ’’ አባት እየተባለ የሚጠራው ሙላ አስታጥቄ በመክፈቻ ንግግሩ ስለሺ ደምሴ የኢትዮጵያን ማህበረሰባዊ ሙዚቃ እና የሙዚቃ መሳሪያዎች ጠብቆ ለማቆየት የሚያደርገውን ጥረት አመስግኗል፡፡
በመድረኩ ነግሶ ያመሸው ስለሺ ደምሴ ከአዲሱ የሙዚቃ አልበሙ በርከት ያሉ ስራዎችን ከ"ያምራል ሀገሬ" ባህላዊ የሙዚቃ ቡድን ጋር ተጫውቷል፡፡ስራዎቹ በባህላዊ ጭፈራ እና ክዋኔ የታጀቡ በመሆናቸው ማራኪ ትዕይንት ሆኖ አምሽቷል፡፡
ስለሺ ደምሴ በሙዚቃ ስራው በክራር አጨዋወቱ፤በዜማዎቹ እና ግጥሞቹ እጅጉን የተለየ አቀራረብ እና አጨዋወት የሚከተል የሙዚቃ ሰው ነው፡፡በብሄራዊ ቴአትር ከአዲሱ አልበሙ ባቀረባቸው ስራዎቹ እንቁጣጣሽን እና የሰርግ ዜማን ከተለመደው ለየት ባለ መንገድ በማቅረብ የአድናቂዎቹን ቀልብ ገዝቶ አምሽቷል፡፡

Monday, September 16, 2013

በአንበሳ ግቢ አንበሳ ሰው ገደለ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 6 ፣ 2005 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ በአንበሳ ግቢ የአንበሶች ማቆያ ማዕከል ውስጥ ዛሬ ከጠዋቱ 1:30 ላይ የሞት አደጋ ተከሰተ።

አደጋው የተከሰተው አቶ አበራ ሲሳይ የተባሉት የአንበሶቹ መጋቢ የአንበሶቹን ማደሪያ እያጸዱ ባሉበት ወቅት ከጥንቃቄ ጉድለት ባልተዘጋው በር የገባው ቀነኒሳ የተባለው አንበሳ ለህልፈተ ህይወት ዳርጓቸዋል።

የግለሰቡን ህይወት ለማትረፍ በወቅቱ በስራ ላይ የነበሩ የግቢው ሰራተኞች ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካ መቅረቱ ለማወቅ ተችሏል።

የሟች አስከሬን ከአንበሶቹ ማደሪያ ወጥቶ ወደ ምኒሊክ ሆስፒታል ተወስዷል።

ተመሳሳይ አደጋ ከዚህ በፊት በ19 89 ዓ.ም መከሰቱ የሚታወስ ነው።

Soucre : FanaBC

Tuesday, September 10, 2013

ከኢትዮጵያ በማደጎ የወሰዷትን ልጅ ለሞት የዳረጉት አሜሪካውያን ቤተሰቦቿ ጥፋተኛ ተባሉ

 ኢትዮጵያዊቷን ሐና ዊሊያምስን በማደጎ ወደ አሜሪካ የወሰዳት ላሪ ዊሊያምስ በቀረበበት ሐናን የመግደል ክስ ጥፋተኛ ተባለ።
በ2008 ከኢትዮጵያ በማደጎነት የተወሰደችው ሐና ከፍተኛ ቅዝቃዜ ቦታ ላይ ተቆልፎባት በደረሰባት የጤና መታወክ ለሞት ሊዳርጋት እንደቻለ ፍርድ ቤቱ አረጋግጧል።
ከጤና መታወክም ባለፈ ለቀናት ያለምግብ ከምድር በታች ባለ ቤት ውስጥ ተዘግቶባት በመቆየቷ ረሃብ ለሞቷ አንድ ምክንያት እንደሆነም ለፍርድ ቤቱ  አቃቤ ህግ ያቀረበው ማስረጃ ያመለክታል።
በዚህም መነሻነት አቃቤ ህግ ለፍርድ ቤቱ የ13 ዓመቷ ሐና ዊሊያምስን ተከሳሾቹ  አባቷ ላሪና ዊሊያምስና እናቷ ካሪ ዊሊያምስ  ከኢትዮጵያ በማደጎ በ2008 ያመጧት መሆኑን በማስረዳት ሰው በመግደል ክስ መስርቶባቸው ነበር።
ሐና በ2011 ግንቦት ወር ላይ  ቤተሰቦቿ መኖሪያ ጀርባ ባለ ምድር ቤት ለቀናት ተዘግቶባት መቆየቷና የቤቱ የቅዝቃዜ ምጣኔ 4 ዲግሪ ሴልሺየስ መሆኑ ለሞት ሊዳርጋት ችሏል።

ላሪ ዊልያምስና ካሪ ዊልያምስ ከሐና ሞት ከአራት ወራት በኋላ በቁጥጥር ስር ውለው ክሳቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ሲሆን ፥ ፍርድ ቤቱም ሰው በመግደል ወንጀል ጥፋተኛ ብሏቸዋል።
በተመሳሳይ ተከሳሾቹ  በማደጎ የወሰዱት የ10 ዓመቱ የሐና ወንድም በተመሳሳይ የመደብደብ ፣ የርሃብና በምድር ቤት ተቆልፎበት እንደነበረም መርማሪዎች ደርሰውበታል።
ለዚህም ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹን ህጻናት ላይ ጥቃት በማድረስና በአግባቡ ባለመንከባከብ ጥፋተኛ ብሏቸዋል።
በቀጣዩ ወር የጥፋተኝነት ቅጣት ውሳኔ ፍርድ ቤት እንደሚያሳልፍባቸው ቀጠሮ የያዘ ሲሆን ፥ በተከሰሱበት የዋሽንግተን ግዛት ህግ መሰረት እስከ እድሜ ልክ እስራት ድረስ ሊቀጡ ይችላሉ።