Search

Friday, January 18, 2013

አባባ ተስፋዬ(Ababa Tesfaye interview)

Ababa Tesfaye interview

ከአባባ ኮሚኩ እስከ አባባ ተስፋዬ
ባውዛ፡- አባባ ተስፋዬ በመጀመሪያ ለቃለ መጠየቃችን ፈቃደኛ በመሆንዎ በባዉዛ
ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በጣም እያመስገንኩ ወደ ጭዉዉት ልግባና

የት አካባቢ ነበር የተወለዱት?
አባባ ተስፋዬ- የተወለድኩት ከዱ የሚባል ሀገር ነው ባሌ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡
ባውዛ፡- ወደ አዲስ አበባ እንዴት መጡ?
አባባ ተስፋዬ፡- አባቴ ነው ሊያስተምሩኝ ያመጡኝ በኋላም ቀበና አካባቢ በአንድ የፈረንሳይ /ህርት ቤት ውስጥ ገባሁ አሁን ኮከበጽባህ ይባላል፡፡ አባቴ አቶ መንበረ ወርቅ ለሚባሉ ሰው አደራ ሰጥተውኝ ሄዱ በኋላ ጣሊያን ወደ
ሀገራችን ገባ፡፡
ባውዛ፡- አባትዎም በወቅቱ ለትምህርት ንቃት ነበራቸው ማለት ነው?
አባባ ተስፋዬ፡- እኔም የሚገርመኝ ይሄ ነው አባቴ በዚያን ጊዜ ምን አሰበው ወደ አዲስ አበባ እንዳመጡኝ በእውነት ይገርመኛል፡፡ በዚያን ጊዜ ለትምህርት ምን ያህል ጥሩ አመለካከት እንዳላቸው አስካሁን ይገርመኛል፡፡
ባውዛ፡- ስንት ዓመት ይሆኖት ነበር ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ?
አባባ ተስፋዬ፡- 12 ዓመት ቢሆነኝ ነው፡፡ ነገር ግን ገና 7 ዓመቴ ፊደል ጨርሼ ዳዊት መድገም ጀምሬ ነበር ጎበዝ ነበርኩ ቀልድም እይዝ ነበር፡፡
ባውዛ፡- በዚህ የሆናል አባትዎ ወደ አዲስ አበባ ያመጡዎት?
አባባ ተስፋዬ፡- ይሆናል፡፡
ባውዛ፡- ከዚያ በኋላ ጣሊያን ገባ እርስዎስ ትምህርትዎን ቀጠሉ?
አባባ ተስፋዬ፡- የለም----የለም--- የጣሊያን ባሪያ ሆንኩ አለቀ፡፡ ታሪኩ ብዙ ስለሆነ ጽፈህ አትጨርሰውም፡፡ ለጣሊያን ባሪያ ብሆንም በኋላ ጣሊያኑን ፈንክቼ ወደ ሐረር
አመለጥኩ ሳቅ-----
ባውዛ፡- ታዲያ ወደ ቴአትሩ ዓለም እንዴት ተቀላቀሉ?
አባባ ተስፋዬ፡- ጣሊያኑን ፈንክቼ በባቡር ወደ ሀረር ከሄዱኩም በኋላ ጣሊያኖች ያሰሩት ራስ ሆቴል ገብቼ ስራ ጀመርኩ በኋላም ልዑል መኮንን ሆቴሉን ስለገዙት የሆቴሉ ኃላፊ ሆንኩ፡፡ እዛ ሆቴል እየሰራሁ ሳለሁ እንግሊዞች (ሱድ አፍሪካውያን) ወደ ሀገራቸው ሲሸኙ የሀገራቸውን ማርሽ አሰሙ፡፡ በኋላ የእኛ ሀገር ሕዝብ መዝሙር የሚያሰማ ባለመኖሩ ቆጨኝና በቃሌ የሀገራችንን ሕዝብ መዝሙር ዘመርኩ በዚህ ጊዜ
ጃንሆይ ‹‹ማነው?›› ብለው ጠየቁ የእነ ግራዝማች ጥግነህ፣ የእነቀኝ አዝማች ቤተሰብ
መሆኔ ተነገራቸውና ወደ አዲስ አበባ እንድመጣ አስደረጉ በነገራችን ላይ አባቴና የአባቴ
ቤተሰቦች ያለቁት ኦጋዴንና ባሌ ውስጥ ነው፡፡

ባውዛ፡- አባትዎ አሳሽ (አስገባሪ) ነበሩ ይባላል?
አባባ ተስፋዬ፡-አዎ አሳሽ ናቸው፡፡ በዚያን ጊዜ አሳሽ ማለት አልገብርም ያለውን
ቦታ ለራስ መኮንን ያስገብሩ ነበር፡፡ (የአፄ ኃይለሥላሴ) አባት እና ወደ ሐረርና ጨርጮ
አካባቢዎች ብዙ ዘመቻ አድርገዋል፡፡ ይሄን ብቻ ባወራህ 1 ሰዓትም አይበቃህም፡፡
ባውዛ፡- እንግዲህ የኢትዩጰያን ሕዝብ መዝሙር ዘመሩና አዲስ አበባ እንዲመጡ
ተደረገ ከዛስ ምን ሆነ?
አባባ ተስፋዬ፡- ተማሪ እያለሁ ጀምሬ የኢትዩጵያን ሕዝብ መዝሙር አውቅ ነበር
ጣሊያንም ከገባ በኋላ አሮጌ ፒያኖ አግቼ ተለማምጄአለሁ፡፡ በሆቴሉም ውስጥ ሙዚቃ
እሞክር ነበር፡፡ ከዛ 1937 . እንደ ኢትዩጵያ አቆጣጠር በሀገራችን ኪነጥበብን
ለማቋቋም አዋጅ ተነገረ፡፡ በኋላም ማዘጋጃ ቤት ተቋቁሞ ስለነበረ እዚያ ገባሁ፡፡ አስራ አንድ ወር ያለ ደመወዝ ሰራሁ፡፡ ደመወዝ
ያልጠየኩበት ምክንያት በንጉሱ ትዕዛዝ
መምጣቴን በማሰብ ነበር፡፡ መብልና
መጠለያ ግን ተመቻችቶልኝ ነበር፡፡
የሙዚቃ ትምህርቴን ከተማርኩ በኋላ
በዚያው ቴአትር ቤት አክተር ሆንኩ፡፡
ባውዛ፡- የሴት ገጸ ባህሪ ወክለው ይጫወቱ
ነበር፡፡ በዛን ጊዜ ደግሞ 18 ዓመት
ጎረምሳ ነበሩና እንዴት አድርገው ነው
የሴት ድምጽ ማውጣት የቻሉት?
አባባ ተስፋዬ፡- ቀላል ነው እንደሴት
መሆን አሁንም የሴት ድምጽ ማውጣት
እችላለሁ፡፡ ልበልልህ----ሳቅ-----የሴት
ድምጽ ብቻ ሳይሆን መንጎራደዱንም
እችልበታለሁ ላሳይህ----ሳቅ-----
ባውዛ፡- ከዛስ በቴአትሩ እንዴት ቀጠሉ?
አዲስ ተስፋዬ፡- ከዛማ 1944 . ወደ
ኮሪያ ሄድኩ ኮሪያም ሄጄ ‹‹ጠላቤቷን››
የተሰኘውን ቴአትር የሴት ገጸ ባህሪ
ተላብሼ በደንብ ሰራሁ፡፡ ቀሚስ ለብሼ
ብታየኝ ምኔም ወንድ አይመስልም ነበር
‹‹
ምናልሸኝ----!›› ያልኩ እንደሆን ሴትም
አስንቀ ነበር፡፡ በኋላም ብሔራዊ ቴአትር
1948 . ተከፈተ ድሮ መጀመሪያ
ማዘጋጃ ቤት የነበርን አክተሮች በሙሉ
ወደዚያ ተዛወርን የጃንሆይ ኢዩቤልዩ
በዓል ነበር፡፡ በደመቀ ስነ-ስርዓት ነበር
የተከፈተው ከዚያ በኋላ አክተር ሆኜ ስሰራ
ቆየሁ፡፡
ባውዛ፡- ከዛ በኋላ ወደ ኢትዩጵያ
ቴሌቭዥን እንዴት ገቡ?
አበባ ተስፋዬ፡- 1957 . በማዘጋጃ
ቤት ውስጥ የኢትዩጵያ ቴሌቭዥን
ሲመሰረት ነው የገባሁት በወቅቱ
የእንግሊዟ ንግስት ኤልሳቤት ትመጣለች
ተብሎ ነው።
ባውዛ፡- የቴሌቭዥን ዝግጅቱ
የተጧጧፈው ሙዚቃም ስናጠና ነበር፡፡
በኋላም 1957 ህዳር 1 ቀን የኢትዩጵያ
ቴሌቪዥን የልጆች ኘሮግራም ተጀመረ፡፡
ኘሮግራሙ የተጀመረው ደግሞ በእኔ
ጠያቂነት ነበር፡፡ በወቅቱ የቴሌቭዥን
ኃላፊ ሆነው ሲሰሩ የነበሩት ብላታ
ግርማቸው ተክለሀዋሪያት ነበሩ፡፡ በወቅቱ
ቴክኒሻኖቹ ፈረንጆች ነበሩ፡፡ ብላታ
ግርማቸው የሕፃናት ኘሮግራም አሰፈላጊ
መሆኑን ስነግራቸው ይሄም አለ እንዴ
‹‹
ብለው ፈረንጁን አማከሩት ፈረንጁም
‹‹
ሰው አላችሁ›› ብሎ ጠየቀ በኋላ እኔ
ተመርጬ ስቱዲዮ ገባሁ፡፡
ባውዛ፡- የልጆች ኘሮግራም እንደጀመሩ
ሲያቀርቡ የነበሩት የኘሮግራም ይዘት ምን
ነበር?
አባባ ተስፋዬ፡- ተረት ነበር
የማቀርበው፡፡
ባውዛ፡- ተረቱን ከየት ነበር የሚያገኙት?
አባባ ተስፋዬ፡- ድሮ በልጅነቴ አባቴና
አያቴ ብዙ ተረት ይነግሩኝ ነበር፡፡ እኔ
ደግሞ የማስታወስ ችሎታዬ ከድሮ ጀምሮ
ትልቅ ነበር፡፡
ባውዛ፡- መቼ መቼ ነበር ኘሮራሙን
የሚያቀርቡት?
አባባ ተስፋዬ፡- ቅዳሜ፣ እሁድና ሰኞ
ነበር፡፡
ባውዛ፡- 1957 የተወለደ ሕፃን ዛሬ
ትልቅ ሰው ነውና በዛን ጊዜ የነበሩ ልጆች
ለኘሮግራሙ ያላቸው አስተያየት ምን
ይመስል ነበር?
አባባ ተስፋዬ፡- ዛሬ ወደ ውጭ አሜሪካ
የጋበዙኝ ሁሉ በዛን ጊዜ ሕፃን ነበሩ፡፡ከዛ
ጊዜ በኋላ የተወለዱ ብዙ ናቸው በዛሬ ጊዜ
በጣም እየረዱኝ ያሉት እነሱ ናቸው፡፡
ገንዘብ ይሰጡኛል ስልክ እየደወሉም
ያጽናኑኛል ወደ ኢትዩጵያ በሄዱ ቁጥር
ተረቶቼን ይገዛሉ በብዙ ነገር ያስቡኛል፡፡ የእኔን ተረቶችና ምክር እንደውለታ
ቆጥረው ያስቡኛል፡፡ ወላጆቻቸውም
እንዲሁ ያከብሩኛል፡፡ ልጆቻችንን
ከአልባሌ ስፍራ እንዲርቁ በማድረግዎት
እናመሰግንዎታለን ይሉኛል፡፡
ባውዛ፡- ለምን ያህል ጊዜ ነው በኢትዩጰያ
ቴሌቪዥን የልጆች ኘሮግራም የቀረቡት?
አባባ ተስፋዬ 42 ዓመት ያህል
ነው እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ የአክተርንት
ስራዬንም ደርቤ ነበር የምሰራው እና ለዚህ
ሁሉ ዓመት ልጆችን በተረት ስመክርና
ሳዝናና ቆይቼአለሁ፡፡
ባውዛ፡- መቼም በወጣትነትዎ ነው
ይሄንን ስራ የጀመሩትና ሲጀምሩም ‹‹አባባ
ተስፋዬ›› ነበር የሚባሉት ወይስ ሌላ ስም
ነበርዎት?
አባባ ተስፋዬ፡- በፊት ጭምብል (ማክስ)
አድርጌም እሰራ ነበር መጠሪያዬም ‹‹አባባ
ኮሚኩ ነበር›› የሚባለው በኋላ በራሴ ስም
እንዲሆን ተደረገ፡፡
ባውዛ፡- ህፃናትን ለማዝናናት ሳይንሳዊ
ትምህርት ቀስመዋል እንዴ?
አባባ ተስፋዬ፡- በፍጹም በተፈጥሮዬ
ነው ፊቴን የምቀያይረው ደግሞም መርሳት
የሌለብህ አክተርም ጭምር ነኝ፡፡ ልጅም
ለመምከር እንደዚያ ፊትን መቀያየርም
ያስፈልጋል፡፡ የምናገረው በስሜት
በእንቅስቃስና ድራማቲክ በሆነ ነገር
ካልደገፍኩት ልጆች ይሰለቻሉ፡፡ ስለዚህ
ፊቴን በመቀያየር ተረቴን አቀርባለሁ
እንጂ ማንም አላስተማረኝም እግዚአብሔር
ነው የሰጠኝ የአባቴ ምክር የአያቴ ተረት
ነው ለዚህ ያበቃኝ ተማሪም እያለሁ
መሸለል መፎከር እወድ ስለነበር የቁጣ
የደስታና የሐዘን የፊት ቅርጽ ማሳየት
እችላለሁ፡፡
ባውዛ፡- 42 ዓመታት ያህል ከሰሩበት
የኢትዩጵያ ቴሌቭን የልጆች ክፍለ ጊዜ
ኘሮግራም ለምን ለቀቁ?
አባባ ተስፋዬ፡- መቼም ከልጅ የዋለ
ልጅ ነው ይባል የለ አንዲት ልጅ ተረት
ስተርት ያንን ምክንያት አደረጉና ‹‹ከዛሬ
ጀምሮ ኮንትራታችን አልቋል አሉኝ›› እሺ
ብዬ ወጣሁ፡፡
ባውዛ፡- በቃ በዚህ ምክንያት ስራዎትን
ለቀቁ ማለት ነው?
አባባ ተስፋዬ፡- እኔ የማውቀው
ይህንን ነው፡፡ የቀረውን ደግሞ ‹‹ለምን
ኮንትራቱን አቋረጣችሁበት›› ብለህ
እነሱን ጠይቃቸው እኔ በበኩሌ ምንም
የማውቀው ነገር የለም በወቅቱ ልጅቷ
ተረት ስትናገር ጠይቄአታለሁ ‹‹አንድ
ጋና እና አንድ ፈረንጅ ነበሩ ስትል አንድ
ጋና ነው ያለችው የዩኒሴፍ ተረት ነበር፡፡
እነርሱ ምን እንደተሰማቸው አላውቅም
ብቻ ይሄ ተረት እንደተላለፈ የስንብት
ደብዳቤ ሰጡኝ ‹‹ከዛሬ ጀምሮ ኮንትራትዎ
አብቅቷል›› አሉኝ እሺ ብዬ እጅ ነስቼ
ወጣሁ፡፡
ባውዛ፡- እርስዎ ግን በስራው መቀጠል
ይፈልጉ ነበር?
አባባ ተስፋዬ፡- እንዴ እኔ የተፈጠርኩት
ለልጆች ነው በመጣሁ ጊዜ ሀገሩ በጋዜጣ
በስልክ ተጨናንቆ ነበር ምንም እንኳ
የስንብት ደብዳቤውን ሲሰጡኝ እጅ ነስቼ
ብቀበልም ህፃናቱ ለእኔ ካላቸው ፍቅርና
አክብሮት አንፃር ግን ሀዘን ይሰማኛል፡፡
ባውዛ፡- አሜሪካንን እንዴት ያይዋታል?
አባባ ተስፋዬ፡- አሜሪካ ሀያል ናት፡፡
የዓለም ንጉሥ ናት ሁሉ ነገር እጃ ላይ
ነው፡፡ እኔ ግን ሀያል ሀገር የምለው
ሀገሬን ነው፡፡ ኢትዩጵያን እወዳታለሁ፡፡
‹‹
ወፍ የሚጮኸው እንዳገሩ ነው›› ይባል
የለ ከዚህ ውጭ በልጅነታቸው እኔ
የመከርኳቸው በዚሁ በአሜሪካ ይገኛሉ፡፡
እነዚህ ሰዎች ዛሬ ታላላቅ ሰዎች ሆነዋል፡፡
ስለዚህ እኔም ከኢትዩጵያ መጥቼ
ከእነርሱ ጋር በመገናኘቴ ደስታዬ ወደር
የለውም፡፡ ወደ አሜሪካ ስመጣም ባዶ
እጄን አልመጣሁም፡፡ ከአራት መቶ በላይ
መጽሐፍት ይዤ ነው የመጣሁት፡፡ በሲዲ
የተዘጋጀ ተረት ይዤአለሁ፡፡ እና ጥሩ ጊዜ
እንደማሳልፍ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ባውዛ፡- ኢትዩጵያውያን ህፃናትን
እየመከሩ ያሳደጉት አባባ ተስፋዬ እርሶ
ግን ልጆች አልዎት?
አባባ ተስፋዬ፡- አዎ አሉኝ፡፡ ሶስት
ልጆች ወልጄ ነበር፡፡ ሁለቱ ሞቱብኝ
አንዱ ግን አድጎ ልጅ ወልዶአል፡፡
እግዚአብሔር ይመሰገን ልጅ ከስሬ
አይጠፋም፡፡ አሁን አሥራ አንድ ቤተሰብ
አብረን እንኖራለን በዚህም ደስ ይለኛል፡፡
ባውዛ፡- በመጨሻ ምን የሚሉት ምን
የሚያስተላልፉት መልክት አልዎት?
አባባ ተስፋዬ፡- ወደዚህ ወደ አሜሪካ
በዚህ እድሜዬ በመምጣቴ ደስተኛ ነኝ
እኔን ለመርዳት ብዙ ሰዎች ሲጥሩ
አያለሁ፡፡ ለእነሱም የላቀና የከበረ ምስጋና
እንዳለኝ በዚህ አጋጣሚ ንገርልኝ፡፡
አብዛኛውን ጊዜዬን ህፃናትን እየመከርኩ
በማሳለፌ ከምንም ባልተናነሰ ደስተኛ
ነኝ፡፡ የሚወዱኝ ልጆች ብዙ ናቸው፡፡
ወላጆቻቸው ቢሆንም ለእኔ ትልቅ
አክብሮት አላቸው፡፡ ባለፈው ታምሜ
ከሞት ላዳኑኝ ምስጋና ይድረሳቸው፡፡
በዚህ በአሜካ ተወልደው ያደጉ ህፃናትም
ሀገራቸውን እንዲያውቁ እንዲወዱ እና
ስለሀገራቸው የሚቆረቆሩ እንዲሆኑ
እንደምፈልግ ንገረልኝ፡፡ ሁሉምንም
እወዳቸዋለሁ፡፡ በተለይ በዚህ በአሜሪካ
የሚኖሩ ወላጆች ለልጆቻው የኢትዩጵያን
ተረት እንዲያስተምሩ በዚህ አጋጣሚ
እጠይቃለሁ፡፡ የአገራቸውን አኢትዮጵያን
ቋንቋ፣ባህልና ታሪክ እንዲያውቁ ማስተማር
ይኖርባቸዋል። ለዚሕም ወላጆቻቸው
ትልቅ አላፊነት አለባቸው፡፡
ባውዛ፡- ለኢትዩጵያ ቴሌቭዥን የልጆች
ክፍለ ጊዜን እንደሚሰናበቱ ሁሉ እኛንም
አሰናብቱን?
አባባ ተስፋዬ፡- አዎ አስታወስከኝ፡፡
‹‹
ደህና ሁኑ ልጆች----የዛሬ አበባዎች የነገ
ፍሬዎች----ደህና ሁኑ ልጆች----ደህና ሁኑ››
ባውዛ፡- አመሰግናለሁ አባባ ተስፋዬ
መልካም የአሜሪካ ቆይታ ይሁንልዎ፡፡
አባባ ተስፋዬ- እግዚአብሔር ይስጥልኝ
አመሰግናለሁ፡፡

No comments:

Post a Comment