Search

Wednesday, January 16, 2013

ከአልሸባብና ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ተከሳሾች በፅኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጡ

በሶማሊያ ሞቃዲሾ በተለያዩ አካባቢዎች ወታደራዊ ሥልጠና በመውሰድ የጅሀድ ጦርነት እንዴት እንደሚካሄድ፣ የመሣሪያ አፈታትና አገጣጠም ሥልጠናዎችን ከወሰዱ በኋላ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ፣
ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሰላም ለማወክ፣ እንዲሁም ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማፈራረስ ሲንቀሳቀሱ ተገኝተዋል በሚል ተከሰው የነበሩ አሥር ግለሰቦች፣ ጥር 7 ቀን 2005 ዓ.ም. በፅኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጡ፡፡

የወንጀሉ ጠንሳሽና የአልሸባብ ወታደር እንደነበር የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት ባቀረበው ክስ አንደኛ ተከሳሽ ያደረገው ኬንያዊውን ሐሰን ዳርሶ ሲሆን፣ ግለሰቡ በሐሰተኛ መታወቂያ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት፣ ሌሎቹን ተከሳሾች መመልመሉን ፍርድ ቤት ቀርቦ ከማመኑም በተጨማሪ፣ ዓቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃ በማቅረብ አረጋግጦበታል፡፡ ባለመከላከሉም የወንጀል ድርጊቱና የቅጣት ደረጃው ከፍተኛ ሆኖ በ17 ዓመታት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኖበታል፡፡

ከ2000 ዓ.ም. መጨረሻ ጀምሮ በህቡዕ በመደራጀት የአልሸባብንና የአልቃይዳን ተልዕኮ ለመፈጸም በተያዩ ስሞች በመጠቀምና በሐሰት መታወቂያ ወደ ኢትዮጵያ በገባው ኬኒያዊው ሐሰን ጃርሶ ተመልምለዋል የተባሉት መሐመድ ቃሲም፣ ዑመር ሙሳና አብዲሺኩር ዳውድም በዓቃቤ ሕግ የቀረበባቸውን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች ማስተባበል ባለመቻላቸው ጥፋተኛ ተብለው ቅጣት ተወስኖባቸዋል፡፡

በመሆኑም በቅደም ተከተላቸው መሐመድ ቃሲም በ13 ዓመታት ፅኑ እስራትና በ5,000 ብር፣ ዑመር ሙሳ በ12 ዓመታት ፅኑ እስራትና በ5,000 ሺሕ ብር፣ አብዲሽኩር ዳውድ በሦስት ዓመታት ከሦስት ወራት ፅኑ እስራት ተቀጥተዋል፡፡

በሌሉበት ክሳቸው የታየው የሱፍ ሐሰን፣ መሐሙድ ሳፊና ከድር ወይም ሙስጠፋ ዑመር የተባሉት ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በ14 ዓመታት ፅኑ እስራት ተቀጥተዋል፡፡ አብዱራህማን ሁሴን የተባለው ተከሳሽ ደግሞ በ20 ዓመታት ፅኑ እስራትና 10 ሺሕ ብር ተቀጥቷል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ፍርደኞች በሦስት ክሶች የተከሰሱ ሲሆን፣ በሁለት ክሶች ጥፋተኛ የተባሉት አብዱለጢፍ አብዱራህማንና አብደላ ሁሴን የተባሉት ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በ14 ዓመታት ፅኑ እስራት ተቀጥተዋል፡፡

በሽር ሐጂ እስማኤል የተባለ ተጠርጣሪ ተከላክሎ ነፃ በመሆኑ ከእስር ሲለቀቅ፣ ቅጣት ከተጣለባቸው ውስጥ ዘጠኙ በፅኑ እስራት ስለተቀጡ፣ ከማንኛውም ሕዝባዊ መብቶቻቸው ለሁለት ዓመታት ታግደዋል፡፡ አብዲሽኩር ዳውድ ለአንድ ዓመት ከሕዝባዊ መብቱ ታግዷል፡፡ በሌሉበት ቅጣት የተወሰነባቸውን ፍርደኞች የፌዴራል ፖሊስ ይዞ ለማረሚያ ቤት ፖሊስ እንደያስረክብ ትዕዛዝ ተሰጥቶ መዝገቡ ተዘግቷል፡፡
ምንጭ ሪፖርተር

No comments:

Post a Comment