Search

Wednesday, January 9, 2013

የኮንደሚኒየም ተመዝጋቢዎች በድጋሚ ሊመዘገቡ ነው

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቀደም ሲል የተመዘገቡ የኮንደሚኒየም ቤት ፈላጊዎችን በድጋሚ ሊመዘግብ መሆኑን ምንጮች ገለጹ፡፡
በ40/60 ቤቶች ፕሮግራም ምዝገባ የሚካሄደው በአስተዳደሩ መዋቅር ነው ወይስ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሚለው ጉዳይ ላይ እስካሁን ውሳኔ ላይ አልተደረሰም፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮንደሚኒየም ቤቶች ግንባታ በጀመረበት በ1996 ዓ.ም. 453 ሺሕ ነዋሪዎች ቤቶች ለማግኘት ተመዝግበዋል፡፡ ባለፉት ስምንት ዓመታት በተካሄዱ የኮንደሚኒየም ቤቶች ግንባታ 80 ሺሕ የሚጠጉ ተመዝጋቢዎችና በልማት የሚነሱ ሰዎች የቤት ባለቤት ሆነዋል፡፡ ነገር ግን ምዝገባ ከተካሄደው ረዥም ጊዜ የተቆጠረ በመሆኑ ከተመዘገቡት ውስጥ በሞት የተለዩ፣ ወይም በተለያዩ ምክንያቶች ቤቱን የማይፈልጉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላል በሚል እሳቤ አዲስ ምዝገባ መካሄድ እንዳለበት አስተዳደሩ አምኗል ሲሉ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በዚህ ምክንያት የኮንዶሚኒየም ተመዝጋቢዎችን በድጋሚ መዝግቦ በማረጋገጥ፣ አስተዳደሩ ያሰባቸውን የ20/80 እና የ10/90 ቤቶች ፕሮግራም ምዝገባ ለመጀመር እየተዘጋጀ ነው፡፡

አስተዳደሩ በ116 ወረዳዎች ውስጥ ምዝገባ የሚያካሂዱ ባለሙያዎች ሥልጠና እየተሰጣቸው ነው፡፡ ነገር ግን በቅርቡ በይፋ ይጀመራል ተብሎ የተገለጸው የ40/60 ቤቶች ፕሮግራም ተጠቃሚ መሆን የሚፈልጉ ነዋሪዎችን የሚመዘገበው አካል በውል አልታወቀም፡፡ ቀደም ሲል በተሰጠው መግለጫ የፕሮግራሙ ዋነኛ ፋይናንስ አቅራቢ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደሚመዝግብ ተገልጾ ነበር፡፡

ነገር ግን በአስተዳደሩ ባለሥልጣናት ምዝገባውን ማካሄድ ያለበት የከተማው አስተዳደር መሆን አለበት የሚል ሐሳብ በማቅረባቸው እስካሁን ማን እንዳሚመዘግብ አልታወቀም፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ከ500 ሺሕ በላይ የቤቶች እጥረት አለ ተብሎ ይገመታል፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት በነዋሪዎች ዕድገት ልክ የቤቶች ግንባታ ባለመካሄዱ የቤት ፈላጊዎች ቁጥር ከዚህ ሊልቅ እንደሚችል በርካቶች ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡

No comments:

Post a Comment