Search

Wednesday, May 29, 2013

ኢትዮጵያዊቷ ወጣት በአትላንታ 25 ዓመት እስር ተፈረደባት

ኢትዮጵያዊቷ ወጣት ሮዳስ ተክሉ እዚህ አትላንታ ከተማ በዋለው የወንጀል ጉዳዮች ችሎት ቀርባ ጉዳይዋ ሲታይ ከቆየ በኋላ ባለፍው ሰኞ MAY 20/2013 ….. 25 ዓመት እስር ተፈረደባት። ሮዳስ ተክሉ ይህ የተፈረደባት የሰው ነፍስ በማጥፋቷ ወንጀሉንም መፈጸሟን በማመኗ ነው።
የኋላ ታሪኩ እንዲህ ነው። ፌብሩዋሪ 5 ቀን 2009 አመሻሽ ላይ በአትላንታ የተፈጸመው ወንጀል መላው የአትላንታ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን በቅርብ፣ ነገሩን የሰሙና በሌሎች ከተሞች ያሉትን ደግሞ በሩቅ ያስደነገጠ ነበር። 3754 ቢፈርድ ሃይዌይ የሚባለው የአትላንታ መንገድ ላይ የጸጉር መከርከሚያ ሱቅ ከፍቶ በመስራት ላይ የነበረው ኤርሚያስ አወቀ ፣ ማምሻውን ጭምር አምሽቶ እየሰራ ነበር። ከምሽቱ 8 ፒ ኤም አካባቢ ሮዳስ ተክሉ ሱቁ ድረስ መጣች።
የፖሊስ ሪፖርት እንደሚያሳየው ሮዳስ ሱቁ ድረስ ከመጣች በኋላ ጭቅጭቅ ተጀመረ። እሱ እንድትወጣለት ቢጠይቃትም አልወጣችም። ይልቁኑ በእጇ ሽጉጥ ይዛ ስለነበር ፣ ስልኩን አንስቶ 911 ደወለ፣ ስልኩን ላነሳችው ኦፕሬተር “አንዲት ሴት ሱቄ ድረስ መጥታ ልትገለኝ እያስፈራራችኝ ነው፣ መሳሪያ ይዛለች .. እያለ ገና ተናግሮ ሳይጨርስ ስልኩ ተቋረጠ። ከዚያ በኋላ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች የጥይት ድምጽ መስማታቸውን ይናገራሉ።
ፖሊስ ካለበት፣ ነገሩን የሰሙም በጸጉር ቤቱ አካባቢ ሲደርሱ ኤርሚያስ በደም ተነክሮ ወድቋል፣ ወዲያው ወደ ሆስፒታል ተወሰደ ፣ ሆስፒታል ሲደርስም ህይወቱ አለፈ። በወቅቱ አንዲት ሴት ከቤቱ ወጥታ ስትሄድ አይተናል ከሚል ጥቆማ ውጪ ማን ገደለው የሚለው ጥያቄ እንቆቅልሽ ሆነ።
በማግስቱ ፌብሩዋሪ 6 ግን ፖሊስ ሮዳስ ተክሉ የተባለችና የቀድሞ ፍቅረኛው ነች የተባለች ሴት በጥርጣሬ መያዙን አስታወቀ። እሷም ወደ እስር ቤት ተወሰደች። ኤርሚያስም የፖሊስ ምርመራ ከታወቀና ዶክተሮች የሞቱን መንስኤ ካስታወቁ በኋላ ፌብሩዋሪ 11 ቀን በርካታ የአትላንታ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት በጸጉር ቤቱ ደጃፍ የሻማ ማብራት ሰነ ስር ዓት ተካሄደ፣ በማግስቱ ፌብሩዋሪ 12 ጸሎተ ፍትሃት ከተደረገለት በኋላ አገር ቤት ተወስዶ እንዲቀበር በተያዘለት ፕሮግራም ይሄዳል ሲባል ፣ ፖሊስ ተጨማሪ ምርመራ ያስፈልገኛል በማለቱ እስከ ፌብሩዋሪ 24 ሳይላክ ቆየ። ፌብሩዋሪ 24 ቀን ግን አስክሬኑ ወደ አገር ቤት ለቀብር ተላከ።
ከዚያ በኋላ ዜናው በአድማስ ሬዲዮም ሆነ አትላንታ ባለው ድንቅ መጽሔት ከወጣ በኋላ በወቅቱ የወጣት ሮዳስ ተክሉ ቤተሰቦች “እሷ በግድያው የለችበትም፣ ይህንን ድርጊት እሷ ትፈጽማለች ብሎ ማሰብ ትክክል አይደለም” ሲሉ ተናግረው ነበር። ሆነም ቀረ ላለፉት አራት ዓመታት ነገሩ ከፍርድ ቤት እስር ቤት ፣ ከ እስር ቤት ፍርድ ቤት ሲንከባለል ቆየ፣ የ ኤርሚያስ አወቀ የቅርብ ቤተሰብ የሆኑት አቶ ላቀው ለአድማስ ሬዲዮ እንደገለጹት በመካከል ተጠርጣሪዋ ልጅ፣ በጠበቆቿ አማካኝነት “አእምሮዋ ትክክል አይደለምና ለፍርድ ልትቀርብ አይገባም” ብለው ሲከራከሩ የቆዩ ሲሆን፣ ዳኞቹም የ አ ዕምሮዋ ነገር በሃኪሞች እንዲታይ ፈቅደው ቆይተዋል። በኋላ ግን ችሎት መቆም እንደምትችል በመታመኑ ፣ ጉዳዩ በከሳሽ አቃቤ ህግ እና በተከሳሽ ሮዳስ ተክሉ ጠበቆች መካከል ክርክሩ ቀጥሎ አራት ዓመት ከፈጀ። እንደ አቶ ላቀው ገለጻ ፣ በመጨረሻ ላይ ሮዳስ ወንጀሉን መፈጸሟን እንድታምን ተጠይቃ “አዎ ፈጽሜያለሁ፣ ነገር ግን በደም ፍላትና ሳላስበው ያደረኩት ነው” ስትል በማመኗ ዳኛዋ 25 ዓመት ጽኑ እስራት ፈርደውባታል። ምናልባት ጥፋቷን ባታምን እና ነገሩ በክርክሩ ብትሸነፍ የሞት ፍርድ ሊጠብቃት ይችልም ነበር ብለዋል።
ዳኛዋ በፍርድ ውሳኔያቸው እንደገለጹት “ ኤርሚያስ ገበየሁን በ 10 ጥይት መግደል ሳይታሰብ፣ ባጋጣሚ የተደረገ አይደለም” ሲሉ ውሳኔያቸውን አጽንተዋል።
በተያያዘ ሁኔታ ሮዳስ ተክሉ እዚያው እስር ቤት እያለች አንዲት ሴት ልጅ መውለዷም ታውቋል። የወለደችው ግሬዲ ሆስፒታል በፖሊስ ታጅባ ሄዳ ሲሆን፣ ባሁኑ ሰአት ህጻኗን አንዲት ነርስ እዚያው ግሬዲ እያሳደገቻት መሆኑ ሲታወቅ፣ የህጻኗን አባት በተመለከተ ዳኛዋ “የቀረበልኝ የዲ ኤን ኤ ምርመራ ስለሌለ፣ በልጅቷ አባት ጉዳይ የምሰጠው አስተያየት የለም” ሲሉ መናገራቸውም ታውቋል። (ምንጭ አድማስ ሬዲዮ አትላንታ)

No comments:

Post a Comment