Search

Monday, June 3, 2013

በአዲሱ የቤት ፈላጊዎች ምዝገባ ህገወጦችን ለጠቆመ 15 በመቶ ወሮታ ይከፈለዋል

የምዝገባ መረጃዎቹ በጠ/ሚኒስትሩ ቢሮ የመረጃ ማጠራቀምያ ቋት ይገባሉ
የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ባወጣው አራት አይነት የመኖሪያ ቤቶች ምዝገባ፤ ህገወጥ መረጃዎችን ያቀረቡና በህገወጥ መንገድ የተመዘገቡ ወገኖች ላይ ጥብቅ እርምጃ እንደሚወሰድ ያስታወቀ ሲሆን፣ ህገወጦችን ለሚጠቁሙ ዜጐች 15 በመቶ ወሮታ የሚከፈልበት አሠራር ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ የቤቶች ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መሥፍን መንግስቱ ከትናንት በስቲያ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በሰጡት ማብራሪያ፤ ከፍተኛ የመኖሪያ ቤት ችግር በሚታይባት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተጀመረው ፕሮግራም ይህ አብዛኛውን ነዋሪ ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ እንደሚታሰብ ገልፀዋል፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎች በእኩልና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ የቤት ችግራቸውን እንዲያቃልሉ ታስቦ በከፍተኛ ጥንቃቄ የቤት ፈላጊዎች ምዝገባው እንደሚካሄድ ጠቁመው፤ በህገወጥ መንገድ ለመመዝገብ በሚሞክሩና ከወጣው መስፈርት ውጪ ተመዝግበው በሚገኙ ዜጐች ላይ የማያዳግም ጥብቅ እርምጃም እንደሚወሰድ ተናግረዋል፡፡ እነዚህን ህገወጦች ለሚመለከተው አካል ለሚጠቁሙ ወገኖችም የ15% ወሮታ ለመክፈል የሚያስችል አሠራር ለማውጣት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አቶ መስፍን ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ምዝገባው በከፍተኛ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች የሚከናወን መሆኑን የተናገሩት ሃላፊው፤ መረጃዎቹ በኔትወርክ እንዲያያዙና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ በሚገኝ የመረጃ ማጠራቀሚያ ቋት ውስጥ እንዲገቡ ለማድረግ የሚያስችል አሠራር መደራጀቱንም ገልፀዋል፡፡
መስተዳድሩ የመኖሪያ ቤት ፈላጊዎች የመመዝገቢያ ቀናትን ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ቤት ፈላጊዎች በተሰጠው የጊዜ ገደብ ብቻ ቀርበው እንዲመዘገቡ አሳስቧል፡፡ በወጣው ፕሮግራም የ10/90 እና 20/80 ወይም የኮንዶሚኒየም ቤቶች ተመዝጋቢዎች ከሰኔ 3 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሰኔ 21 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ ምዝገባቸውን የሚያካሂዱ ሲሆን፣ በ1997 ዓ.ም ተካሂዶ በነበረው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ምዝገባ ተመዝግበው እስከ አሁን ድረስ እጣው ያልወጣላቸው ዜጐች በዚህ ምዝገባ እንደ አዲስ ሊመዘገቡ እንደሚገባም ተገልጿል፡፡ የቀድሞ የኮንዶሚኒየም ምዝገባ በአዲሱ ምዝገባ ተሻሽሎ የሚከናወን ሲሆን ከዚህ በኋላ የ1997 ዓ.ም ምዝገባ ዋጋ እንደማይኖረው ተጠቁሟል፡፡
ቤት ፈላጊዎች ከተመዘገቡ በኋላ በድጋሚ በሚካሄደው የማጣሪያ ምዝገባ የጣት አሻራ እንዲሰጡ እንደሚደረግና ለዚህም የሚያገለግሉ የመሣሪያዎች ግዢ እየተከናወነ እንደሆነ ዋ ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡ ተመዝጋቢዎች እንደየሚመዘገቡበት የቤት ልማት ዓይነት መቆጠብ የሚገባቸውን የገንዘብ መጠን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ በመቆጠብ የባንክ ደብተር መያዝ ይኖርባቸዋል፡፡ ነባር የኮንዶሚኒየም ተመዝጋቢዎች፣ በአዲሱ ምዝገባ ለባለ ሶስት መኝታ ቤት 685 ብር፣ ለባለ ሁለት መኝታ ቤት 561 ብር፣ ለባለ አንድ መኝታ ቤት 274 ብር እንዲሁም ለስቱዲዮ 151 ብር በቅድሚያ ሊቆጥቡ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡ ለአዲሱ የ20/80 ወይም የኮንዶሚኒየም ቤቶች ምዝገባ ለባለ ሶስት መኝታ ቤት 489 ብር፣ ለባለ ሁለት 401 ብር እንዲሁም ለባለ አንድ 196 ብር መቆጠብ ያስፈልጋል፡፡ በቀድሞ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ምዝገባ ተመዝግበው እጣ ያልወጣላቸውና በዚህ ምዝገባ እንደ አዲስ የሚመዘገቡ ነባር ተመዝጋቢዎች ከአዲሶቹ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እንደሚስተናገዱም ተገልጿል፡፡
ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች የተዘጋጀው የ10/90 የስቱዲዮ ቤቶች ደግሞ 187 ብር በቅድሚያ መቆጠብ የሚገባ ሲሆን፣ የእነዚህ ቤቶች ግንባታ በአብዛኛው እየተጠናቀቀ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡ የ40/60 ቤቶች ምዝገባ ተጠቃሚ የሚሆኑት የተሻለ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች አካላት እንደሆኑ የተናገሩት አቶ መስፍን፤ ሙሉ ክፍያ ለሚከፍሉ ተመዝጋቢዎች ቅደሚያ እንደሚሰጥም ጠቁመዋል፡፡ የእነዚህን ቤቶች ምዝገባ በተመለከተ በባንክ በኩል መመሪያዎች ወጥተው ተፈፃሚ እንደሚደረጉም ሃላፊው ገልፀዋል፡፡ የማህበራት ምዝገባም በቡድን እየተደራጁ በሚመጡ ወገኖች ተግባራዊ እንደሚደረግ ጠቁመው፤ በምዝገባ ወቅት የቤቱ ዋጋ 50% እና መሬት ተዘጋጅቶ የግንባታ ፈቃድ ከመሰጠቱ በፊት 50% በዝግ ሂሳብ የሚቀመጥ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡ ለ40/60 ቤቶች ምዝገባው ከነሐሴ 6 እስከ ነሐሴ 17 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ የሚከናወን ሲሆን ማህበራት ደግሞ ከሐምሌ 15 ቀን እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ ምዝገባቸውን እንደሚያከናውኑ ተጠቁሟል፡፡ በአዲሱ የቤት ፈላጊዎች ምዝገባ በቀን ከ100ሺ በላይ ሰዎች ይመዘገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አቶ መስፍን ተናግረዋል፡፡ የመንግስት ሠራተኞችን በተመለከተ በልዩ የምዝገባ አሠራር በየመ/ቤቶቻቸው በኩል እንዲከናወን መወሰኑም ተገልጿል፡፡

No comments:

Post a Comment