Search

Thursday, June 6, 2013

የጋራ መኖሪያ ቤቶች ምዝገባ በወረዳና በተመረጡ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ይካሄዳል

የጋራ መኖሪያ ቤቶች ፈላጊዎች በወረዳና በተመረጡ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ምዝገባ እንደሚያካሄዱ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዛሬ ግንቦት 28/2005 ዓ.ም በሰጠው መግለጫ በአዲስ አበባ በተለያዩ የጋራ መኖሪያ ቤቶች መርሃ ግብር የሚመዘገቡ የከተማዋ ነዋሪዎች በወረዳና በተመረጡ የመንግስት መስሪያ ቤቶች መሆኑን ገልጿል፡፡
ነባር ተመዘጋቢዎች ዳግም እንዲመዘገቡ የተፈለገው መረጃውን ለማጥራትና የቤት ፍላጎታቸውን መቀየር ለሚፈልጉ ለማመቻቸት ነው ብለዋል በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የመኖሪያ ቤቶች ልማትና የመንግስት ህንጻዎች ኮንስትራክሽን ዘርፍ ሀላፊ አቶ አማረ አስግዶም፡፡
የመንግስት ሰራተኞች 20 በመቶ ቅድሚያ የማግኘት እድል ተሰጥቷቸዋል፡፡ ለመመዝገብ ሲሄዱም የቀበሌ መታወቂያ ከሌላቸው የታደሰ የሰራተኛ መታወቂያ መያዝ እንዳለባቸው አቶ አማረ ተናግረዋል፡፡
በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በውክልና በ40/60ና በቤቶች ስራ ማህበራት መርሃ ግብር ብቻ መመዝገብ ይችላሉ፡፡
ከሰኔ 3 እስከ ነሐሴ 17/2005 ዓ.ም በ10/90፣ 20/80 አዲስና ነባር፣ በቤቶች ስራ ማህበራትና በ40/60 ቤት ፈላጊዎች ምዝገባ ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ቅጾች በአዲስአበባ ቤቶች ልማት ኤጀንሲ መዘጋጀቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ መስፍን መንግስቱ ተናግረዋል፡፡
በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ኤጀንሲው ከሚያቀርባቸው የመመዝገቢያ ቅጾች ውጭ ቅጾች እየተሸጡ በመሆኑ ቤት ፈላጊዎች በምዝገባ ወቅት በመመዝገቢያ ወረዳዎች በሚሰጣቸው ቅጾች ብቻ መጠቀም እንዳለባቸው አቶ መስፍን አሳስበዋል፡፡
ቤት ፈላጊዎች ለምዝገባ ከመምጣታቸው በፊት የቁጠባ ሂሳብ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መክፈት የግድ መሆኑንና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚታየውን መጓተት ለማስተካከልም እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ምዝገባው በከተማዋ በ116 ወረዳዎችና ከ177 በላይ የመንግስት መስሪያ ቤቶች እንደሚከናወን ተገልጿል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በዚህ የበጀት አመት 95 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እየተገነቡ ሲሆን 24 ሺህ ቤቶች ተጠናቀዋል፡፡

ከሰኔ 3/2005 ዓ/ም ጀምሮ በሚካሄደው ምዝገባ ከአንድ ነጥብ ሶስት ሚሊየን በላይ ቤትፈላጊዎች ይመዘገባሉ ተብሎ ይጠበቃል ፡፡
ሪፖርተር ፡-አዝመራው ሞሴ

No comments:

Post a Comment