Search

Thursday, December 20, 2012

የትያትር መግቢያ ዋጋ ጭማሪ ውዝግብ

የትያትር ባለሙያዎቸ ወደ አዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አዳራሽ ለስብሰባ ሲገቡ
*በ15 ብር ማሳየት ለመንግሥት ትያትር ቤቶችም ያንሳል - የቢሮው ሃላፊ
*ቢሮው የግል ኢንተርፕራይዞችን ዋጋ የመተመን አግባብ የለውም - አርቲስት ገነት አጥላው
“ቁርጥ ያለ ምላሽ ስጡን፤ዋናው ማነቆ ያለው እናንተ ጋ ነው - አርቲስት ሽመልስ አበራ
በጐረቤት ሀገራት እንኳን አርቲስቶች በግል አውቶሞቢላቸው ይጓጓዛሉ እንጂ ታክሲ አይጠቀሙም የሚሉት የአገራችን የትያትር ባለሙያዎች፤እኛ ግን ስንሞት እንኳን የሬሳ ሳጥን መግዣ እየቸገረን በመዋጮ ነው የምንቀበረው ሲሉ ያማርራሉ፡፡ ባለፈው ሰሞን የትያትር ቤት መግቢያ ዋጋ ላይ የ100 ፐርሰንት ጭማሪ አድርገው ከትያትር ቤቶቹ ጋር በተፈጠረው አለመግባባት ተግባራዊ ሳይሆን የቀረባቸው የግል የትያትር ኢንተርፕራይዞች፤ከዘጠኝ አመት በፊት በነበረው የትያትር መግቢያ ዋጋ አሁን ማሳየት የሚሞከር አይደለም ባይ ናቸው፡፡ ከኑሮ ውድነቱ በተጨማሪ የትያትር ፕሮዳክሽን ዋጋ፣ የማስታወቂያ እና ተያያዥ ወጪዎች ከእጥፍ በላይ በመናራቸው ዋጋ ሳንጨምር መስራት አንችልም ይላሉ፡፡ በነፃ ገበያ ውድድር መርህም የሕዝቡን የመክፈል አቅም ያገናዘበ ጭማሪ አድርገን 15 ብር በሰው የነበረውን የትያትር መግቢያ 30 ብር አድርገናል ሲሉ በአዲስ አበባ አስተዳደር ስር ላሉት ሁለት ትያትር ቤቶች እና በፌደራል ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ለሚተዳደረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር ማሳወቃቸውን ይገልፃሉ፡፡ የመንግሥት አካላቱ ችግሩን እንደሚጋሩ ቢያምኑም በዚህ መልኩ ዋጋ መጨመሩን አልተቀበሉትም፡፡ በዚህም ሳቢያ በተከሰቱ አለመግባባቶች በግል ኢንተርፕራይዞች የሚታዩ ትያትሮች ተስተጓጉለዋል፡፡ ይህ ደግሞ ሁሉንም ወገን የሚጎዳ እንጂ የሚጠቅም እንዳልሆነ ባለፈው ማክሰኞ የግል ኢንተርፕራይዞች ከመንግስት ሃላፊዎች ጋር ባደረጉት ስብሰባ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ የትያትር ኢንተርፕራይዞችን ችግር እንደሚጋሩ የገለፁት የመንግስት ሃላፊዎች፤ ድንገተኛ የዋጋ ጭማሪውን ግን አልተቀበሉትም - “ዋጋ ለመጨመር ጊዜ ያስፈልጋል” በሚል፡፡
የማክሰኞውን ስብሰባ የመሩት የቢሮው ኃላፊ አቶ ገብረፃድቅ ሐጐስ፤ “የዋጋ ጭማሪ የጠየቃችሁት ሥራችሁን ቀጥላችሁ ቢሆን ኖሮ ጥሩ ነበር፣ ቢሮው እናንተ ከመጠየቃችሁ በፊትም ጥናት እያደረገ ነው የትያትር መግቢያ ዋጋ ከፊልም መግቢያ ዋጋ አንሷል፡፡ ከሥራው አድካሚነት አንፃር ዋጋው ከፊልም መግቢያ መብለጥ ነበረበት፤ጥያቄአችሁ ትክክለኛ ነው” ብለዋል፡፡
የትያትር መግቢያ ዋጋ 15 ብር ሲደረግ በህዝብ ተቋማት ደመወዝ ተከፍሏቸው የሚያዘጋጁ የትያትር ባለሙያዎችን እንጂ የግል የትያትር ኢንተርፕራይዞችን ታሳቢ ተደርጎ እንዳልሆነ የጠቆሙት የቢሮው ሃላፊ፤ በ15 ብር ማሳየት ለመንግሥት ትያትር ቤቶችም እንደሚያንስ ተናግረዋል፡፡
ሆኖም የግል ኢንተርፕራይዞች በእንዲህ ያለው መልኩ ዋጋ መጨመራቸው የመንግሥት ትያትር ቤቶችን አላማ እንደሚያንኮታኩት አቶ ገብረፃድቅ ገልፀዋል፡፡ በዚሁ ስብሰባ ላይ የተገኙት ሌላው የቢሮው ኃላፊ ደግሞ ትያትሮች ኪሳራ ላይ ናቸው የሚለው እንደማያስኬድ ጠቁመው፤ ጭማሪ ማድረግ ካስፈለገም ይሄን ማድረግ የሚችለው የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
ትያትር ፕሮዲዩስ አድርጐ እንዳከሰረው የተናገረው ጋዜጠኛና የማስታወቂያ ባለሙያ ሳምሶን ማሞ፤እዚህ ዋጋ አትጨምሩ እየተባለ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዋጋ በመጨመር ለአንድ የቴሌቪዥን ማስታወቂያ አስር ሺህ ብር ማስከፈሉ በአንድ ሀገር ሁለት ስርአት አለ ወይ ያሰኛል ብሏል፡፡ “ከያንያኑ ሲሞቱ የሬሳ ሳጥን መግዣ እንኳን የላቸውም --- አርቲስቱ ከማኪያቶ ዋጋ አንሷል” ያለው ሳምሶን፤ ኢህአዴግ ላለፉት ሃያ አመታት ለችግሩ መፍትሄ ባለመስጠቱ የሕዝብ አደራ አልተወጣም ያሰኛል ሲል ወቅሷል፡፡
ቢሮው የግል ኢንተርፕራይዞችን ዋጋ የመተመን አግባብ እንደሌለው የገለፀችው አርቲስት ገነት አጥላው በበኩሏ፤የመንግሥት ትያትር ቤቶች እና የግል ትያትር ኢንተርፕራይዞች የዋጋ አሀድ (Cost component) እንዲሁም የአንድ ትያትር ከሌላ ትያትር የዋጋ አሀድ አንድ አለመሆኑን ጠቅሳ፤ ብዙ ሰዎች የሚተውኑበትን ‘ሕንደኬ’ ትያትርንና አራት ወይም አምስት ሰዎች የሚተውኑበትን ሌላ ትያትር በአንድ የዋጋ ሚዛን ማየት ይቻላል ወይ በማለት ጠይቃለች፡፡ አርቲስት አለማየሁ ታደሰ ደግሞ የትያትር ባለሙያዎች ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ሲወጡ ምን ይስሩ የሚል ጥያቄ ካቀረበ በኋላ “ሕዝብን ማገልገል ሌላውን ሕዝብ መበደል ነው እንዴ?” ሲል አስተያየቱን በጥያቄ ገልጿል፡፡
የመንግሥትና የግል ትያትር ኢንተርፕራይዞች በእኩል መታየት የለባቸውም ያለው አርቲስትና ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ተክለአረጋይ፤ የግል ኢንተርፕራይዞች ደግ አባት ስላላቸው ደመወዝ በነፃ ከሚከፈላቸው በርካታ የመንግሥት ትያትር ቤቶች ባለሙያዎች ጋር ሊነፃፀሩ አይገባም ብሏል፡፡ ትያትር በግል ፕሮዱዩስ ማድረግ እንደማያዋጣም ሲገልፅ፤ ሙስናና መጓተት ባይኖር ኖሮ የትያትር ፅሁፎችን ከግል ትያትር ኢንተርፕራይዞች ይልቅ ለመንግሥት ትያትር ቤቶች መስጠት እንደሚመርጥ ተናግሯል፡፡
በፊልምና በትያትር አዘጋጅነቱ የሚታወቀው አርቲስት ቢኒያም ወርቁ፤በትያትር መኖር እንደማይቻል እንደውም እዳ ውስጥ እንደሚከት ካብራራ በኋላ በአዲስ አበባ ትያትር ቤቶች ለግል ኢንተርፕራይዞች የሚሰጡት ቀናት የተመልካች ቁጥር አናሳ የሆኑባቸው እንደሆኑ ጠቁሟል፡፡
የሚቀርበው ትያትር ደረጃውን የጠበቀ ነው ወይ የሚለውን ከዋጋ ጋር ማንሳት ተገቢ ነው ያለው የኢትዮጵያ ትያትር ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚደንት አንጋፋው አርቲስት ደበሽ ተመስገን በበኩሉ፤በዚህ ስብሰባ ላይ የትያትር ቤቶች የሥራ ኃላፊዎች ቢገኙ ጥሩ ነበር፡፡
ለደራሲና አዘጋጅ ቁርጥ ክፍያ ከፍሎ ትያትር ቤቱ በራሱ ዋጋ ማሳየት ይችላል ብሏል፡፡በመጨረሻም የቢሮው ኃላፊ አቶ ገብረፃድቅ ሀጐስ “መሰናክሎቹ ተጠንተው በጋራ ውይይት መፍትሄ እንፈልጋለን፣ የትያትር ዋጋውንም ጉዳይ ቢሆን ሰው ስጡንና በጋራ ይጠና” ያሉ ሲሆን የሃላፊውን መፍትሄ ተከትሎ የተናገረው አርቲስት ሽመልስ አበራ፤ “ቁርጥ ያለ ምላሽ ስጡን፤ዋናው ማነቆ ያለው እናንተ ጋ ነው፡፡ ትያትር ቤቶች ማቅረብ ያልቻሉትን ነው የግል ኢንተርፕራይዞች እያቀረቡ ያሉት፡፡ ትያትር ቆሟል፡፡ ገቢ ቆሟል፡፡ በዚህ እየተጐዳ ያለው መንግሥትም ጭምር ነው” ብሏል፡፣
ኃላፊው በሰጡት ምላሽም “ለማቆም እንገደዳለን ማለታችሁ ስህተት ነው፡፡ መፍትሄ እስኪገኝ በገባችሁበት ውል ቀጥሉ፡፡ ችግሩ ይሰማናል፤ ከምትሰጡን ሰዎች ጋር በአጭር ጊዜ እንወስናለን” ቢሉም ጋዜጠኛ ሳምሶን ማሞ “አቶ ገብረፃድቅ ኮሚቴ ሳያስፈለገው ዛሬውኑ ብትወስን አርቲስቱ ዘለአለም ያመሰግንሃል” ሲል ተማፅኗል፡፡ አርቲስት ገነት አጥላውም “ይጠና ሲባል አጥኚው ማነው?” ብላ በመጠየቅ “የሚያጠኑት የመንግሥት ሠራተኞች ናቸው፡፡ እኛ ጉሮሮ ላይ ተቁሟል፡፡ የዋጋ ጭማሪው አጥንተን የገባንበት ነው፤ የመንግሥት ገቢና ሕዝብ ከትያትር የሚያገኘው ጥቅም ታጥቷል” ብላለች፡፡ ከተመልካቾች መካከል ትያትሮችን ተመልክቶ ጋዜጦች ላይ በመፃፍ የሚታወቀው ዳዊት ንጉሡ ረታ “ተመጣጣኝ ክፍያ ቢኖር ጥሩ ነው፡፡ ይህ ባለመሆኑም ወጪ ለመቀነስ በሚል ብቻ በትያትር የሚሳተፉ ሰዎችን ቁጥር መቀነስ የትያትሮችን ደረጃ እያወረደ ነው፡፡ ከመግቢያ ዋጋ ጭማሪው በኋላ ይሄ ባይቀጥል ደስ ይለኛል” ያለ ሲሆን ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ብዙነሽ ወንድሙ “የትኬት ዋጋ ቢጨምር ጥሩ ነው፡፡ የጥበብ ዋጋ ወረደ፡፡ የዋጋው መውረድ አንዳንዴ የተመልካች ቁጥር ይቀንሳል፡፡ ጥሩ ትያትር እስካየሁ ድረስ ዋጋ ተጨምሮ ከያንያን ቢጠቀሙ ደስ ይለኛል” ብላለች፡፡
በግል ኢንተርፕራይዞች የሚታዩ ትያትሮች በመቋረጣቸው ሌሎች ተመልካቾች ማግኘት አልቻልንም፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር እየታዩ ካሉ ስምንት ትያትሮች አራቱ፣ በሐገር ፍቅር ትያትር እየተዩ ካሉት ሰባት ትያትሮች ሦስቱ በአዲስ አበባ ማዘጋጀ ቤት ትያትርና ባህል አዳራሽ ከሚታዩት ሰባት ትያትሮች ስድስቱ በግል የትያትር ኢንተርፕራይዞች የቀረቡ ናቸው፡፡
የትያትር ባለሙያዎቹና የቢሮው ሃላፊዎች የማክሰኞ ውይይት ባለመግባባት ከተቋጨ በኋላ “መብታችን ሆኖ ለምንድነው የምንጠብቀው?” ያሉት አርቲስቶች ውይይቱን ለብቻቸው እንደቀጠሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡

No comments:

Post a Comment