Search

Tuesday, December 18, 2012

ታንዛንያ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ለመግዛት ጥያቄ አቀረበች

Tanzania Request to buy electric power from Ethiopian Electric Power Corporation

ዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ 4.45 ቢሊዮን ብር ብድር ፈቀደ
በውድነህ ዘነበ

ምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር ታንዛኒያ ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ለመግዛት ጥያቄ ቀረበች፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ምሕረት ደበበ መንግሥት የታንዛንያን ጥያቄ ተቀብሎ የሽያጭ ስምምነት ላይ ለመድረስ ድርድር ይጀምራል ብለዋል፡፡

ታንዛንያ ከኢትዮጵያ ኃይል የምታገኘው ኢትዮጵያና ኬኒያ በጋራ እየዘረጉት ካለው 433 ኪሎ ሜትር ከፍተኛ የኃይል ተሸካሚ መስመር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከታንዛንያ ጋር የምትደርስበት የኃይል ሽያጭ ስምምነት በራስ ፍላጎት የሚከናወን ሲሆን፣ የኤሌክትሪክ መስመሩ በኬንያ የሚያልፍ በመሆኑ ግን ኬኒያ የተወሰነ ክፍያ ይኖራታል ሲሉ አቶ ምሕረት ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት በወረቀት ላይ ገዝፎ የቆየው የምሥራቅ አፍሪካ ኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክት ዕውን ወደ መሆን ቀርቧል፡፡ ኢትዮጵያን ከኬኒያ የሚያገናኘውን የኃይል መስመር መገንባት የሚያስችለው ፕሮጀክት በርካታ የፋይናንስ ተቋማትን እየሳበ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከኬኒያ ጋር የሚያገናኛትን የኤሌክትሪክ መስመር ለመዘርጋት ከዓለም ባንክ 243 ሚሊዮን ዶላር (4.45 ቢሊዮን ብር) ብድር አግኝታለች፡፡ ይህንን የብድር ስምምነት ባለፈው ዓርብ ታህሳስ 5 ቀን 2005 ዓ.ም. የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሱፊያን አህመድና የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሚስተር ዧንግ ዚ ቼን ተፈራርመዋል፡፡

የኤሌክትሪክ መስመር ግንባታው ከደቡብ ክልል ወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ ተነስቶ ኬኒያ ድረስ የሚዘረጋ ነው፡፡ ኬኒያ የምሥራቅ አፍሪካ ኤሌክትሪክ መረብ አካል በመሆኗ፣ ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያን ከምሥራቅ አፍሪካ እስከ ደቡብ አፍሪካ ከሚገኙ አገሮች ጋር ያገናኛታል፡፡

ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያን ከኬኒያ ያገናኛል ይባል እንጂ በሁለቱ አገሮች ብቻ የሚወሰን አይደለም የሚሉት አቶ ምሕረት፣ ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ የምሥራቅና የደቡብ አፍሪካ አገሮችን ያገናኛል፡፡ የምሥራቅና የሰሜን አፍሪካ አገሮችን በከፍተኛ የኤሌክትሪክ መስመርም ያገናኛል፡፡

ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች ጋር ያላትን የመደራደር አቅም እንደሚያሳድግ አቶ ምሕረት ገልጸዋል፡፡ ምክንያቱም ከአምስት ሳምንት በፊት ኢትዮጵያ ነዳጅ ለምታቀርብላት ጎረቤት ሱዳን አንቶ መቶ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል መላክ ጀምራለች፡፡ ይህ የሙከራ ጊዜ ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ ሁለት መቶ ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ለሱዳን የምታቀርብ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ ከጥር ወር በኋላ በሁለቱ አገሮች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ይመረቃል፡፡

ኢትዮጵያ የኬኒያ የጠረፍ ከተማ ለሆነችው ሞያሌ መጠነኛ የኤሌክትሪክ ኃይል መስጠት የጀመረች ሲሆን፣ በቅርቡ የሚጀመረው የኤሌክትሪክ መስመር ሲጠናቀቅ 400 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለኬኒያ ትልካለች፡፡ ወደ ኬኒያ የሚዘረጋው የኤሌክትሪክ መስመር ግን እስከ ሁለት ሺሕ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የመሸከም አቅም ያለው መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ኢትዮጵያ ለጎረቤት ጂቡቲም 50 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እየላከች ነው፡፡ ከፍተኛ መጠን ኤሌክትሪክ ለጎረቤት አገሮች መላክ መጀመሯ ከአገሮቹ ጋር ያላትን የመደራደር አቅም እንደሚያሳድገው አቶ ምሕረት ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያና የኬኒያ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ወጪ 1.3 ቢሊዮን ዶላር የሚፈጅ ሲሆን፣ ለኬኒያ የዓለም ባንክ፣ የአፍሪካ ልማት ባንክና የተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት ብድር ሰጥተዋል፡፡

ምንጭ: ሪፖርተር

No comments:

Post a Comment