Search

Monday, December 10, 2012

“ሰው ለሰው” ድራማ በውዝግብ እየተናጠ ነው

What happens between  Ethiopian Sew le sew Drama artists?
ላለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በየሳምንቱ ዘወትር ረቡእ ሲተላለፍ የቆየው “ሰው ለሰው” ተከታታይ ድራማ በፕሮዱዩሰሮች መካከል በተፈጠረ ግጭት ሊታገድ እንደሚችል ምንጮች ጠቆሙ፡፡ በድራማው ላይ የኢንስፔክተር ፍሬዘር እህት ናርዶስን ሆና የምትጫወተው ብስራት ገመቹ፤ ስሰራ የቆየሁት ገፀ - ባህሪ ለእኔ ሳይነገረኝ ለሌላ ተዋናይ መሰጠቱ አግባብ አይደለም ያለች ሲሆን በድራማው ላይ የባለቤትነት ድርሻ ቢኖራትም ሸሪኮቿ ያለእሷ እውቅና ያሻቸውን እያደረጉ መሆኑን ጠቁማ መብቷን ለማስከበር ክስ መመስረቷን ለአዲስ አድማስ ገልፃለች፡፡ ከድራማው ደራሲ የቀረበልኝን የፍቅር ጥያቄ ባለመቀበሌ ጫና ደርሶብኛል ብላለች - አርቲስት ብስራት፡፡
የዛሬ ሁለት አመት ድራማው ሊሰራ ሲታሰብ ዳንኤል ሃይሉ፣ መስፍን ጌታቸው፣ ሠለሞን አለሙ እና ነብዩ ተካልኝ በሙያቸው፣ እሷ ደግሞ የገንዘብ መዋጮ በማድረግ በሽርክና ለመስራት መፈራረማቸውን ትናገራለች፡፡
ከድራማው ከሚገኘው ገቢ 16.5 በመቶ ድርሻ ስላላትም ለሁለት አመት ስትሰራበት ለቆየችው ትወና ገንዘብ እንዳልተከፈላት እንዲሁም መኖሪያ ቤቷን የድራማው ዋና ገፀባህሪያት መስፍንና ማህሌት መኖርያ ቤት በማድረግ ለቀረፃ ሲያገለግል መቆየቱን ትናገራለች፡፡ በመኖሪያ ቤቷ ቀረፃ ሲከናወን ከስነምግባር ያፈነገጡ ድርጊቶች ስለነበሩ የአምስት ዓመት ልጇን ላለማሳቀቅ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በተደጋጋሚ በደብዳቤና በቃል ጠይቃ በመጨረሻም በኢቴቪ ጣልቃገብነት ችግሩ ለጊዜው መፈታቱን ብስራት ገልፃለች፡፡ ሆኖም በየጊዜው ችግሮች መፈጠራቸው አልቀረም ትላለች፡፡ በድራማው ላይ የምታያቸውን ድክመቶች ስትናገር እንደ ፕሮዱዩሰር ስላላይዋት ሊሰሟት እንዳልፈቀዱ ትናገራለች፡፡ የአስናቀ ቅጥር ነፍሰ ገዳይ ሆኖ ይጫወት የነበረው አርቲስት እንደተቀየረ፣ እሴተ ሆና የምትሠራውና የአስናቀ ሚስትም ለረጅም ጊዜ በድራማው እንዳትታይ መደረጉን ገልፃ፣ ተመልካቹም በሁኔታው ደስተኛ እንዳልሆነ ብትነግራቸውም ለማሻሻል ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ገልፃለች፡፡
በተለያዩ ጊዜያት ከደራሲው ማስጠንቀቂያ ደብዳቤዎች እንደተፃፈላት የምትገልፀው ብስራት፤ “ለቀረፃ ቤትሽን የማትፈቅጂ ከሆነ እርምጃ እንወስዳለን፣ቀረፃ መቀያየሩን ተረድተሽ የማትመጪ ከሆነና ከቀረፃ በፊት ይነገረኝ የሚለውን ግትር አቋምሽን ካልተውሽ አስፈላጊውን እርምጃ እንወስዳለን” የሚሉ ማስፈራርያዎች እንደደረሳት ትናገራለች፡፡ ሆኖም በወቅቱ “መልህቅ” የተሰኘውን ፊልሟን እየሠራች ስለነበር፣ላለመጨቃጨቅ ብላ ነገሩን ችላ እንዳለችው ገልፃለች - ብስራት፡፡ መስፍን ደራሲ በመሆኑ ለአስር ሳምንት አጠፋሻለሁ ብሎ ከድራማው ውስጥ እንዳጠፋት የምትገልፀው ተዋናይዋ፤ በየጊዜው የሚናገረውን ነገር ሁሉ እንደሚፈፅምባት ጠቁማለች፡፡ ቤቷን ለቀረፃ ፈቅዳ እንደነበር የምትናገረው ብስራት፤ ነገር ግን መስፍን በሚያሳየው የስነምግባር ጉድለት የተነሳ ቤት እንዲቀይሩ ብትጠይቅም፣ኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ለሦስት ወር ብቻ እንድትታገስ፣መስፍንም ከድርጊቱ እንዲቆጠብ ተነግሮት እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ እሷ በማታውቀው ሁኔታ የድራማዋ ናርዶስ በሌላ ተዋናይ (ሜሮን ተሾመ) መቀየሯን ቤቷ ቁጭ ብላ ድራማውን ስትከታተል ማየቷን ገልፃለች፡፡
በድራማው ላይ የሚተውኑ አርቲስቶችን በተለያየ ጊዜ ለመቀየር ፍላጎት እንደነበራቸው፣ ሆኖም ህዝቡ አይቀበለውም በሚል መቅረቱን የተናገረችው ብስራት፤ የ“ሰው ለሰው” ተዋናዮች ሽልማት ይሰጣቸው የሚል ሃሳብ ቀርቦም “ይጠግቡብናል” በሚል መቅረቱን ትናገራለች፡፡
የድራማው ሁለተኛ ክፍል ከተጀመረ አንስቶ ምንም አይነት ክፍያ እንዳልተከፈላት የገለፀችው ብስራት፤ በፊት በየሦስት ወሩ ክፍያ ይከፋፈሉ እንደነበር፣አሁን በየወሩ እንደሆነ ጠቁማ ሆኖም ከደራሲውና ከአዘጋጁ በስተቀር ማንም ክፍያ እንዳልትፈፀመለት ተናግራለች፡፡ በውላቸው መሠረት ሁሉም ነገር የሚወሰነው በሸሪኮቹ ፊርማ መሆኑን የምትናገረው ተዋናይዋ፤ ያለእሷ እውቅና የበፊቱ ድርጅት ተቀይሮ በሌላ ድርጅት መተካቱን፣ ሳያሳውቋት ድርጅቱ ቢሮ መልቀቁንና ሳይነገራት ሠራተኛ መቀጠሩም ከውላቸው ውጪ እንደሆነ ገልፃለች፡፡ ይሄም ሳያንስ ያለምንም ማስጠንቀቂያ ከትወናው መውጣቷ እንዲሁም በሴትነቷ ለደረሰባት ክብረ ነክ ድርጊት ክስ ለመመስረት ወደ ፍርድ ቤት እንዳመራችና ባላት የባለቤትነት ድርሻም ድራማውን ለማሳገድ ጥያቄ እንደምታነሳ ተናግራለች፡፡
የ“ሰው ለሰው” ደራሲ መስፍን ጌታቸውን ስለጉዳዩ በስልክ ጠይቀነው መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ እንዳልሆነ የገለፀልን ሲሆን የድራማው አዘጋጅ ሠለሞን አለሙ በበኩሉ፤ ከተዋናይቱ ጋር ውል የነበረን በፊት እንጂ አሁን አቋርጠናል ብሏል፡፡ ውሉ በምን መልኩ እንደተቋረጠ ግን ለመግለፅ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል፡፡
 ምንጭ: አዲስ አድማስ

1 comment: