Search

Monday, April 20, 2015

የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት በሊቢያ በኢትዮጵያዊያን ላይ አይ ኤስ የፈፀመውን ግድያ አወገዘ


የኢትዮጵያ እስልማና ጉዳይ ጠቅላይ ምክር ቤት አሸባሪው የአይ ኤስ ቡድን በሊቢያ በነበሩ ኢትዮጵያዊያን ላይ ያደረሰውን ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት አወዘገ።
የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሼህ ሙሃመድ አወል ኡመር ጀማል፥ የአይ ኤስ ታጣቂዎች ሃይማኖትን ጭምብል ያደረጉ ፀረ ሃይማኖተኛ ናቸው ብለዋል።
በእስልምና እምነት የሰው ልጅ ከየትኛውም ፍጡር የከበረ ነው ያሉት ሼህ ሙሃመድ፥ ይህ አረመኒያዊ ተግባር እስልምናን አይወክልም ብለዋል።
ምክር ቤቱ ይህን ፀረ እስልምና እንቅስቃሴ እንደሚያወግዝ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፥  ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይህ አክራሪ ቡድን በሌሎች ሀገራት እያደረገ ያለውን ተግባር ወደ ኢትዮጵያ እንዳያስፋፋ ከመንግስትና ከፀጥታ ሀይሎች ጋር በንቃት እንዲንቀሳቀስ አሳስበዋል።
የሀገራችንን ሰላም ለመጠበቅ እምነታችን አይለያየንም ነው ያሉት ሼህ ሙሃመድ።
የፌድራል ጉዳዮች ሚኒስትር ድኤታ አቶ ሙሉጌታ ውለታ በበኩላቸው  ኢትዮጵያ ዜጎቿ  ቀዳዳውን አጥብበውት እንጂ  ለበርካታ ጊዜ የሞት ድግስ ተደግሶላት እንደነበር ተናግረዋል።
ትናንት በኢትዮጵያዊያኑ ላይ የደረሰው ጭካኔ የተሞላበት ግድያ አክራሪዎች ለሺህ ዘመናት ተዋዶ እና ተከባብሮ በመኖር ለአለም ተምሳሌት በሆኑት ኢትዮጵያውያን መካከል ክፉ ዘርን ለመዝራት ታልሞ የተደረገ መሆኑንም ነው ሚኒስትር ድኤታው የገለጹት።
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያውን ለዘመናት የኖረው ተቻችሎ እና ተዋዶ የመኖር ልምድ ልዩነትን አያበቅልም ብለዋል።
የነዚህ ንፁሃን ደም ኢትዮጵያውያንን ከፀረ አክራሪነት ትግሉ ስንዝር ወደ ኋላ እንደማይጎትታቸውም ነው ያረጋገጡት።
ሀገሪቱ የፀረ ሽብር ህግ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን የሚመለከተውን አዋጅ አውጥታ ወደ ተግባር ባትገባ ኑሮ አክራሪዎች ኢትዮጵያን እንደ ሊቢያ፣ ሶርያ፣ የመን እና ኢራቅ የፈራረሰች ባድማና የደም መሬት ባደረጓት ነበርም ብለዋል።
የትናንቱ ድርጊት የፀረ ሽብር እና ፀረ ፅንፈኝነት ትግሉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመዋል።
አይ ኤስ የተባለው አሸባሪ ቡድን ትናንት በለቀቀው ተንቀሳቃሽ ምስል ኢትዮጵያውያን ያላቸው 28 ንፀሃን 16ቱን በስለት ተቀልተው ደማቸው በባህር ዳርቻ ሲፈስ 12 ጭንቃላታቸው በጥይት ተመትቶ በበረሃ ሲወድቁ አሳይቷል።
አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን አለም አቀፉ ፅንፈኛ ቡድን አይ አይ ኤስ አል ፉቅራን ባለው ድረ ገፁ የለቀቀውን ዘግናኝ ምስል ተቀባብለውታል።
የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ሬውዳን ሁሴንም በግፍ የተገደሉት ንፀሃን ሁሉም ኢትዮጵያን ስለመሆናቸው እያጣራን ነው ብለዋል።
በሊብያ፣ በደቡብ አፍሪካም ሆነ በየመን የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው መመለስ ከፈለጉ የፈቀዱትን ለማድረግ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም አቶ ሬድዋን ገልጸዋል።
በዳዊት መስፍን
source :FBC

No comments:

Post a Comment