Search

Tuesday, April 23, 2013

Pregnant woman died while medical staff watching Sew Le Sew Drama

የህክምና ባለሞያዎች ድራማ እየተመለከቱ የታካሚዋ ህይወት ጠፋ

ወ/ሮ ሰፊያን እንደዋጋው የተባሉት የቤት እመቤት የህክምና ባለሙያዎች ተገቢውን ኃላፊነት ባለመወጣታቸው  ህይወታቸው ማለፉን ቤተሰቦቻቸው ለፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል አስታወቁ፡፡
የሟች ቤተሰቦች በሠነድ አስስደግፈው ለዝግጅት ክፍላችን እንዳስታወቁት የጥሩነሽ ቤጂንግ አጠቃላይ ሆስፒታ የዕለቱ ተረኛ ሐኪሞች በፈጠሩት ኃላፊነት የጎደለው አገልግሎት አሰጣጥ የእህታቸውን ህይወት ሊያጡ ችለዋል፡፡
የሟች ቤተሰቦች እህታችን አጣን የሚሉበት ሁኔታ ሲያስረዱ “እህታችን መንታ ማርገዟ ተነግሯት ተገቢውን የህክምና ክትትል እያደረገች የእርግዝና ጊዜዋን ጨርሳለች ፡፡ መጋቢት 26 ቀን 2005 ዓ/ም ለሊት ምጥ ያዘኝ አለች፡፡ እያማጠችና እየተሰቃየች ነጋ በማግስቱ ጠዋት ነተስተን ሳሪስ ጤና ጣቢያ ወስደናት፤ ጤና ጣቢያው የደረሰነው 4 ሰዓት ነው፡፡ ለጊዜው ምንም ዕርዳታ ሳይደረግ 6 ሰዓት ሆነ፡፡ የጤና ጣቢያው ሠራተኞች ለምሳ ወጡ፡፡ 7 ሰዓት ሲመለሱ የላብራቶሪ ምርመራ አድርገው ከአቅማችን በላይ ስለሆነ ብለው ለጥሩነሽ ቤጂንግ አጠቃላይ ሆስፖታል ሪፈር ተጻፉልን፡፡
ከቀኑ 8 ሰዓት ሲሆን ጥሩነሽ ቤጂንግ አጠቃላይ ሆስፒታል ደረስን፡፡” በማለት ይገልጻሉ፡፡
ቤተሰቦቿም በመቀጠልም ሲያብራሩ  “8 ሰዓት ሆስፒታሉ ብንደርስም ከ8-11 ሰዓት ድረስ ከሆስፒታሉ ምንም ዓይነት እርዳታ ማግኘት አልቻለችም፡፡ ከ11 ሰዓት በኃላ ወደ ዘውዲቱ ሆስፒታል ሪፈር ጻፉልን፡፡ 12 ሰዓት ሲሆን ዘውዲቱ ሆስፒል ደረስን፡፡
የዘውዲቱ ሆስፒታል የዕለቱ ተረኞች ምንም እርዳታ ሳያደርጉ ተኝታ መታከም አለባት፡፡ እኛ አልጋ የምንሰጠው እኛ ጋ ክትትል እያደረጉ ለቆዩ ታካሚዎች ነው፡፡
ስለዚህ ወደ መጣችሁበት ሆስፒታል ተመለሱ፤ ብለው ጻፉልንና ተመልሰን ወደ ጥሩነሽ ቤንጂንግ ሆስፒታል ሄድን፡፡ የዕለቱ ሐኪሞች ተመልሰን ስንመጣ ተቀብው ሊያስተናግዱን አልቻልንም፡፡ የደረስነው ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ነው፡፡ ሐኪሞች በአንድ ክፍል ተሰብስበው “ሰው ለሰው” ድራማ ይመለከቱ ነበር፡፡ ቀን የተመለከተቻት ሐኪምም ቆማ ድራመውን ትመለከታለች እህታችን ህመሙ ጨምሮባት የስቃይ ድምጽ ታሰማለች፡፡ ደም ይፈሳታል፡፡ ኸረ እባካችሁ ልትሞትብን ነው! እርዳታ ስጡልን ብለን ለመንን፤ ከውጪ የጥበቃ ሠራተኞች ጠርተው ሆስፒታሉን እየረበሹ ስለሆነ አስወጧቸው ብለው አስወጡን፤ ባለሞያዎቹ እኛ ነን እንጂ እናንተ አይደላችሁም ምታውቁት መውለጃ ጊዜዋ ገና ነው ብሎን አግዳሚ ላይ አስቀምጠዋት እነሱ ወደ ድራማቸው ሄዱ፡፡
እኛም አላስችል ብሎን እየተመላለስን በቀዳዳ ስንመለከት ስትሰቃይ ተመልክተናል፡፡” ሲሉ በለቅሶና በቁጭት ሁኔታውን ይገልጹታል፡፡
የሟች ቤተሰቦች በማያያዝም ሲናገሩ “እስከ ለሊቱ 6 ሰዓት ድረስ ምንም እርዳታ አላገኘችም:: ከሌሊቱ 6 ሰዓት አልጋ ተገኝቶላታል ገንዘብ ክፈሉ ተባልን ለጊዜው ደስ ብሎን ከፍለን አልጋ ይዛ ተኛች፡፡ ከቀን ጀምሮ እንደተመለከትነው አሁንም ደም ይፈሳትል የምጥ ስሜት የተናነቃታል፡፡
መርዳት ባለመቻላችን እያየን አዝነን ጥለን ወጣን፡፡ ከዚያ በኋላ መግባት እንደማንችልም ተነገረን፡፡ እስከ ለሊቱ 9፡15 ድረስ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለች ማወቅ አልቻልንም በትግስት ተቀምጠን ጠበቅን፡፡ ዘጠኝ ሰዓት ከሩብ ሲሆን አንድ ወንድና አንድ ሴት ልጅ በሠላም መገላገሏን ለእሷ የተመደበችውና ቆማ ድራማውን የምትከታተለዋ ሐኪም አበስረችን፡፡ ለልጆቹ ልብስ ጠየቀችን፤ ይዘን ስለነበረ ሰጠናት፡፡ ማየት እንችል እንደሆነ ጠየቅን ቆይ አሁን ትረጋጋ ብላን ሄደች፡፡
ከንጋቱ 12 ሰዓት ሲሆን አሁንም ማየት እንድንችል ጠየቅን አሁን የሚያስፈልጋት አጥሚት ስለሆነ አምጡላት አሉን፤ ሰጠናት፡፡ እኛ ደግሞ አንድ ቀን ሙሉ ደም ሲፈሳት ስለዋለች ልባችን ሊረጋጋ ባለመቻሉ ማየት ፈለግን አልፈቀዱልንም የሰጠናትን አጥሚት ትጠጣም አትጠጣም ያወቅነው ነገር የለም፡፡
ሀኪሟ ተመልሳ መጥታ በጣም በጥሩ ሁኔታ ላይ ናት ከ2-7 ሰዓት ትወጣለች አለችን፡፡ ሁላችንም በጣም ደስ አለን፡፡ በየአቅጣጫው እየደወልን ለዘመድ አዝማድ ተናገርን፤ ይዘናት ለመውጣት ስንዘጋጅ ትንሽ ደም ስለፈሰሳት ደም ያስፈልጋታል አሉን፡፡ ሁላችንም የእህታችንን ህይወት ለማትረፍ ወደ ስታዲየም አካባቢ ደም ለመስጠት ቀይ መስቀል ሄድን ፡፡”  በማለት ያስረዳሉ፡፡ አክለውም “ሟች እህታችን ከዚህ በፊት ሁለት ጊዜ በቤት ውስጥ ወልዳለች፡፡
የመጀመሪያ ልጇ 17 ዓመት ከሁለት ወሩ ሲሆን ሁተኛዋ ልጇ 16 ዓመቷ ነው፡፡
ሁለተኛዋ ልጇ ተደብቃ ገብታ እናቷን ስትመለከት በጀርባዋ ተንጋላ ተኝታለች አያኗም ተጫፍኗል፡፡ ብላ ነገረችን፡፡ እኛ ደም ለመለገስ ስንሯሯጥ የ17 ዓመት ከሁለት ወር የሆነውን ልጇን አስፈርመው አፕራሲዮን አደረግን አሉን፡፡ ከኦፕራሲዮን በኃላ መሞቷ ተነገረን፡፡ በምን ምክንያት ኦፕራስዮን ልትሆን እንደቻለች ሊያስረዱን አልቻሉም ዕድሜው 18 ዓመት ያልሞላ ልጅ ለምን ማስፈረም ፈለጉ?፡፡ አስክሬን ለማስረከብ  እና ገንዘብ ለመቀበል ይህ ነው የማይባል በደል ደርሶብናል፡፡ አስክሬን ለማውጣት ገንዘብ ለመክፈል በሊፍት ውስጥ የገባውን ባለቤቷን መብራት ጠፍቶ ለ30 ደቂቃ በአየር እጥረት ተዳክሞ በብረት ታግለንና ሊፍቱን ፈልቅቀን ስናወጣው የሊፍት ሠራተኛው እረፍት ሄዷል  መብራት ስለጠፋ ነው ብለው አላግጠዋል፡፡
አስክሬኑን ከወሰድን በኋላ ከፍተን ስንመለከተው  የተከፈተው አካሏ በአግባቡ አለመሰፋቱን ማየት ችለናል፡፡
እህታችን የሞተችው በሐኪሞች ጥፋት ነው፡፡ የተፈጸመብንን በደል ህዝብና የሚመለከተው የመንግስት አካል ይወቅልን፡፡” ሲሉ ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ዝግጅት ክፍላችን ድረስ በመምጣት አስረድተዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ የጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ኃላፊዎች አስተያየት እንዲሰጡበት ተመላልሰን ጥያቄ አቅርበን ነበር፡፡ በተሰጠን መልስም “በዚህ ጉዳይ መልስ መስጠት የሚችሉት ኃላፊ የሉም፤ ጥያቄውን በደብዳቤ መጠየቅ አለባችሁ፤ ከመምጣታችሁ በፊት ስልክ ደውሉልን”   በሚል ምክንያቶች የሆስፒታሉን አስተያየት ማካተት አልቻልንም፡፡

 

No comments:

Post a Comment