Search

Monday, May 20, 2013

ሶሪያውያን እናቶች በሴት ልጆቻቸው ላይ ጨክነዋል

በሶሪያ መላ የታጣለትን የእርስበርስ ጦርነት በመሸሽ ወደ ዮርዳኖስ የተሰደዱ እናቶች፣ ህይወት ፈተና ሆኖባቸው ሴት ልጆቻቸውን “ለጊዜያዊ ትዳር” እየሸጡ ነው፡፡ ስደተኛ ወላጆች በሴት ልጆቻቸው ላይ መጨከን እንደጀመሩ የዘገበው ሲኤስ፣ ኑሮን ለመግፋት የሚያስችላቸው ብቸኛ አማራጭ ሆኖ ያገኙት ሴት ልጆቻቸውን በሺዎች በሚቆጠሩ ዶላሮች ለጋብቻ መሸጥ ነው፡፡ ከዮርዳኖስም ሆነ በሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ጋብቻ ፈላጊ ወንዶች ለሴቷ ቤተሰቦች ገንዘብ የሚሰጡበት ባህል አለ፡፡ ይሄም ሆኖ ግን የሰሞኑ የዮርዳኖስ ስደተኛ ካምፖች “የጋብቻ ገበያ”፣ እርግጥም ወንዶች ሴቶችን ለዘላቂ ትዳር የሚገዙበት አይደለም፡፡ አብዛኛዎቹ “ትዳሮች” ከሳምንታት የዘለቀ ዕድሜ እንደማይኖራቸው የገለፀው ዘገባው፤ ይልቁንም “የወሲብ ገበያ” ሊባል የሚችል መሆኑን አስረድቷል፡፡
ይህንን የሴት ልጆች ሽያጭ ከሚያቀላጥፉትና ራሳቸውን “የጋብቻ ደላላ” ብለው ከሚጠሩት መካከል ሶሪያዊቷ ስደተኛ ኡም ማጄጅ አንዷ ናት፡፡ ኡም ማጄድ ከሰሞኑ እየጦፈ በመጣው የስደተኛ ልጃገረዶች ሽያጭ ገበያ ፋታ አጥታለች፡፡ የሞባይል ስልኳ በገዢዎች ጥሪ ተጨናንቋል፡፡ ኡም ማጄድ ከወላጆች ጋር በመነጋገር ለሽያጭ ከምታቀርባቸው ሴቶች ጠቀም ያለ ኮሚሽን ታገኛለች፡፡ ክብረ ንጽህናዋ ያልተገረሰሰ ልጃገረድ በሰሞኑ ገበያ እስከ 5ሺህ ዶላር ታወጣለች፡፡ አያ የተባለችዋ የ17 አመቷ ሶሪያዊት ስደተኛ አያ፤ ከቤተሰቦቿ ጋር በስደት ወደ ዮርዳኖስ ከመጣች አንድ አመት ያህል ሆኗታል፡፡
ይሄም ሆኖ ግን የስደት ኑሮ ለእሷም ሆነ ለቤተሰቧ አሳር ሲሆንባቸው፣ ብቸኛውን አማራጭ ለመውሰድ ተገደዱ፡፡ አያ ለ70 አመት ሳኡዲ አረቢያዊ “ትዳር ፈላጊ” ሽማግሌ በ3ሺህ 500 ዶላር ተሸጠች፡፡ ትዳር ፈላጊው ሽማግሌ ግን ከሙሽሪት አያ ጋር የመሰረተውን ትዳር ለማፍረስ የፈጀበት የአንድ ወር ጊዜ ብቻ ነበር፡፡ “ከእሱ ጋር ያሳለፍኩት አንድ አመት ልክ እንደ አስፈሪ ቅዠት ነበር፡፡ ግማሹን ወር በመራር ለቅሶ ነው ያሳለፍኩት፡፡ ከቤተሰቦቼ ጋር እንድገናኝና እንዳወራ አይፈቅድልኝም ነበር፡፡ ምርጫ አልነበረኝምና በሰቀቀን ነበር የምኖረው” ብላለች - አያ ስለ ሽያጩ ትዳሯ ስትናገር፡፡
እንዲህ ለጋ ልጃገረዶችን ለገበያ አቅርባ የምታሻሽጠው ኡም ማጄድ እየሰራችው ስላለችው ነገር ሃፍረትም ሆነ ፀፀት አይሰማትም፡፡ “መኖር የምችልበት ብቸኛው መንገድ ይህ “ስራ” ነው፡፡ ሶሪያውያን ስደተኞች በዮርዳኖስ ሌላ ስራ መስራትና ገቢ ማግኘት አንችልም፡፡ ስለዚህ ምን ማድረግ እንችላለን?...እንስረቅ?...እንግደል?” ትላለች ማጄድ፡፡ የሚገርመው ግን “አንቺስ የ13 አመት ልጃገረድ ልጅሽን ለመሸጥ ትፈቅጃለሽ?” ለሚለው የጋዜጠኞች ጥያቄ የሰጠችው መልስ ነው፡፡ “በፍፁም አላደርገውም!... ልጆቼን ከምሸጥ አይኖቼን አውጥቼ ብሸጣቸው እመርጣለሁ!” ነው ያለችው ማጄድ፡፡

1 comment:

  1. “በፍፁም አላደርገውም!... ልጆቼን ከምሸጥ አይኖቼን አውጥቼ ብሸጣቸው እመርጣለሁ!”

    እኛ ጋር ደግሞ ያለ ዋጋ ------

    በተለይም ኢትጵያዊነት መታወቂያ ለመውሰድ በሚደረግ ጥረት ውስጥ የሚደርስ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ይች ሃገር የማን ናት ያስብላል?

    ReplyDelete