Search

Monday, May 27, 2013

“ሰዎች እንብላ የሚሉት ከልባቸው ነው ወይስ እንደው ለነገሩ ያህል?” የዳሰሳ ጥናት ውጤት

ሰሞኑን ማህበረሰባዊ እሴቶቻችን ከሚባሉት በአንዱ ላይ የብድግ ብድግ ናሙና ወስጄ ጥናት እካሄድኩ ነበር፡፡ የጥናቱ ትኩረት የ “እንብላ ባህላችን” ሲሆን ጥናቱን ለማካሄድ ያስፈለገበት ምክንያትም እውነት ይህ ባህል አለ ወይስ ብዙዎች እንደሚሉት “ጎጂ ባህል” ከሚባሉት ተርታ ተሰልፏል የሚለውን እና አለ ከተባለም ሰዎች እንብላ የሚሉት ለአፋቸው ያህል ነው ወይስ ከልብ የሚለውን የምርምር ጥያቄ ለመመለስ ነበር፡፡
የጥናቱ ዘዴ ደግሞ ሰዎች ምግብ በሚመገቡባቸው አካባቢዎች ላይ ማንዣበብና ማፍጠጥ ወይንም ኦብዘርቬሽን ማካሄድ ነበር፡፡ ለጥናቱ  በናሙናነት ከተወሰዱ ተመጋቢዎች መሀል ታዲያ 70 በመቶ ያህሉ “አንብላ” አላሉም፡፡ ስለዚህ አብዛኞቹ “አንብላ ጎጂ ባህል ነው”  ከሚሉት ተርታ ይመደባሉ ማለት ነው የሚል መላ ምት ላይ መድረስ ተችሏል፡፡
ቀሪዎቹ 30 በመቶ ደግሞ ለአፋቸው ያህል እንብላ ቢሉም የዚህ ጥናት ባለቤት ግብዣቸውን ተቀብሎ ለተጨማሪ ምርምር ባደረገው ጥረት ያገኘው ውጤት አስደንጋጭ ነው፡፡ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት “አንብላ ባዮች” ከምግብ ሳህናቸው ላይ አንድ ሁለት ጠብደል ጠብደል ጉርሻዎች ብድግ ብድግ ሲደረጉ ከፊታቸው ላይ የነበረው ፈገግታ ሁላ በአንድ ጊዜ ድራሹ ይጠፋና በምልክቱ አይናቸው ማጉረጥረጥ ጀምሯል፡፡ አንዳንዶቹ እንዳውም “ ቀልድ አታውቅም እንዴ” የሚለውን ጥያቄ ከማንሳት ጀምሮ “ ፍሬንድ አንተም እዘዛ” በማለት የሰው በልቶ አያድሩም ተኝቶ አይነት አቋም ሲያራምዱ ተስተውሏል፡፡ እጃቸውን እንደመታጠብ ብለው በመጥፋትም የምግቡን ዋጋ አጥኚው ከፍሎ እንዲወጣ ያደረጉም አልታጡም፡፡
ይህ ጥናት ለናሙናነት የተጠቀመባቸው ሰዎች ቁጥር አናሳና አካባቢያዊ ስብጥሩም ጠባብ ከመሆኑ የተነሳ የሀገሪቱን ገፅታ ወካይ ነው ማለት አያስደፍርም፡፡ ይሁንና ለሌሎች የማህበራዊ ሳይንስ ተመራማሪዎች ጥናት መነሻ ሊሆን እንደሚችል አጥኚው ይተማመናል፡፡
ጥያቄው አሁንም ክፍት ነው፤   “ሰዎች እንብላ የሚሉት ከልባቸው ነው ወይስ እንደው ለነገሩ ያህል?”

No comments:

Post a Comment