Search

Wednesday, May 6, 2015

አስተዳደሩ ሰማያዊ ፓርቲ መስቀል አደባባይ ላይ ህዝባዊ ስብሰባ ማድረግ እንደማይችል ገለጸ

አስተዳደሩ ሰማያዊ ፓርቲ መስቀል አደባባይ ላይ ህዝባዊ ስብሰባ ማድረግ እንደማይችል ገለጸ
• ‹‹ተቀባይነት የሌለው ተልካሻ ምክንያት ነው›› አቶ ዮናታን ተስፋዬ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰማያዊ ፓርቲ ግንቦት 9/2007 ዓ.ም መስቀል አደባባይ ላይ ለማድረግ ያቀደውን ህዝባዊ ስብሰባ እውቅና እንደማይሰጠው ለፓርቲው በላከው ደብዳቤ ገልጾአል፡፡ አስተዳደሩ በላከው ደብዳቤ ‹‹መስቀል አደባባይ ከፍተኛ የሆነ የትራፊክ መጨናነቅ ያለበት ከመሆኑም በላይ በርካታ የተከማዋ ነዋሪ የሚተላለፍበት እና የከተማው ነዋሪ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥር›› ነው ሲል ለህዝባዊ ስብሰባው እውቅና እንደማይሰጥና ሰማያዊ ፓርቲ ስብሰባውን መስቀል አደባባይ ማድረግ እንደማይችል ገልጾአል፡፡
በሌላ በኩል የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት አቶ ዮናታን ተስፋዬ አስተዳደሩ የሰጠው መልስ ‹‹ተቀባይነት የሌለው ተልካሻ ምክንያት ነው›› ሲል ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡ ኃላፊው አክሎም ‹‹አደባባዩ የተሰራው እንደዚህ አይነት ተግባራት ሊከናወኑበት ነው፡፡ ኢህአዴግ ሲጠራ ትራፊክ ተጨናነቀ ተብሎ አያውቅም፡፡ ሰማያዊ ሰልፍና ስብሰባ ሲጠራ ግን እንዲህ አይነት ተልካሻ ምክንያት ያቀርባሉ፡፡ በመሆኑም ይህን ተልካሻ ምክንያት ሰማያዊ ፓርቲ አይቀበለውም›› ብሏል፡፡
ከትራፊክ መጨናነቅ ባሻገር አስተዳደሩ ሰማያዊ ለሚያደርገው ህዝባዊ ስብሰባ የፀጥታ ኃይል ለመመደብ እንደሚቸገርም የገለጸ ሲሆን አቶ ዮናታን ተስፋዬ በበኩሉ ‹‹ለጥበቃ የለንም ያሉትን የፀጥታ ኃይል ንፁሃንን ለመደብደብ ሲያሰማሩ በተደጋጋሚ አይተናል፡፡ አሁንም የጥበቃ ኃይል የለንም የሚሉት ስብሰባውን ለማስተጓጎል ነው፡፡ ያኔ ግን ሰላማዊ ዜጎችን ለመደብደብ ይልኩታል፡፡ በመሆኑም የአስተዳደሩ ውሳኔ በምክንያት ያልተደገፈና ተቀባይነት የሌለው ነው›› ብሏል፡፡

No comments:

Post a Comment