Search

Thursday, April 18, 2013

‹‹እኔ ማርያም ነኝ›› ያለችው ወይዘሮ ትዕግስት በእስራትና በገንዘብ ተቀጣች

(ሰንደቅ ሚያዚያ 9 2005 ዓ.ም)፡- የፌደራሉ አቃቢ ሕግ የማይገባትን ጥቅም ለማግኝት በማሰብ በተለያዩ ጊዜያትና ቦታዎች በመንቀሳቀስ ሰዎችን በማታለል ‹‹እኔ ማርያም ነኝ ፤ እንደ ኢየሱስም በጅራፍ ተገርፌአለሁ ፤ ከሞትም ተነስቻለሁ ፤ የወለድኳቸውን ልጆች ያገኝሁት በመንፈስ ነው›› ስትልና የዓለም ፍጻሜ ደርሷል በሚል የሰዎችን የግል ሀብት ለራሷ ስታደርግ ደርሼባታለሁ ሲል ክስ የመሰረተባት የ34 ዓመቷ ትዕግስት ብርሃኑ ወ/ጊዮርጊስ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 6ተኛ ወንጀል ችሎት ፊት ቀርባ ጥፋተኛ ሆና በመገኝቷ በ2 ዓመት ከ4 ወር ጽኑ እስራትና በ1000 ብር የገንዘብ መቀጮ እንድትቀጣ ሲል ባሳለፍነው ሳምንት ወሰነ፡፡

እንደ አቃቢ ሕግ የክስ ዝርዝር ከሆነ ግለሰቧ በአራት የተለያዩ ክሶች የተወነጀለች ሲሆን ፤ የፊደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ‹‹ለሰው ሕይወት ማለፍ ሳቢያ ነች›› ሲል አቃቢ ሕግ ያቀረበውን ክስ ያልተሟ ነው ሲል ውድቅ ሲያደርገው በተቀሩት 3 ክሶች ግን ጥፋተኛ ነች ብሎ እንድትከላከል ብይን ሰጥቷል፡፡
ተከሳሽ ጥፋተኛ የተባለችበት አንደኛ ክስ በ1999 ዓ.ም በየካቲትና በመጋቢት ወራት ውስጥ የማይገባትን ጥቅም ለማግኝት አስባ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 21 ልዩ ቦታው ኪዳነ ምህረት ተብሎ የሚጠራው ከ300 በላይ ሰዎችን በመሰብሰብ ‹‹እኔ ማርያም ነኝ ፤ እንደ ኢየሱስ በጅራፍ ተገርፌ ከሞትም ተነስቻለሁ›› የሚል የሀሰት ወሬ በመንዛትና የዓለም ፍጻሜ ደርሷል ፤ ንብረት አያስፈልግም በሚል ያላችሁን አምጡ ስትል ከተለያዩ የግል ተበዳዮች ጥሬ ገንዘብና ወርቅ የተቀበለች ሲሆን በአጠቃላይም 40ሺህ ብር ለግል ጥቅሟ አውላለች ሲል የክስ መዝገቡ ያስረዳል፡፡
እንደ አቃቢ ሕግ ቀጣይ ክስ ደግሞ ተከሳሿ በሰኔ 1 1999 ዓ.ም በየካ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 16 ልዩ ቦታው ላምበረት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ 50 የሚደርሱ ሰዎችን በመያዝ ወደ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን በመጓዝ ወንጪ ገዳም ተብሎ ወደሚጠራው መንፈሳዊ ቦታ በመውሰድ በጾምና በጸሎት ሰበብ አብረዋት የነበሩትን ሰዎች ለአምስት ቀናት ምግብ እንዳይበሉ በማድረግ እንዲዳከሙና ለከፋ ጉዳት እንዲዳረጉ አድርጋለች ሲል ክሱ ያካትታል፡፡
በሌላ በኩልም ግለሰቧ በጥር 24 ቀን 2003 ዓ.ም በልደታ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 11 ልዩ ቦታው ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን ቅጥር ውስጥ ወደ 20 የሚጠጉ ህጻናት ልጆችና ሴት ተከታዮቿን በመያዝ ‹‹እኔ ማርያም ነኝ ፤ ልጆቼን የወለድኳቸው በመንፈስ ነው እንጂ ከወንድ ጋር ተገናኝቼ አይደለም›› በማለትና ተከታዮቿም ‹‹እሷ ማርያም ነች፡፡ ሞታም ተነስታለች እንዲሁም 40 ቀን ያለምግብ ትጾማለች›› በማለትና ሀሰተኛ ወሬዎችን እንዲነዙ በማድረግ ስታስተምር እንደነበር ከፖሊስ የምርመራ ደርሶኛል ያለው ዐቃቢ ሕግ ፤ በዚህም ምክንያት በቤተክርስቲያኗ ቅጥር ግቢ ውስጥ የነበሩ ሌሎች ምዕመናን ‹‹ሀሰት ነገር አትናገሪ›› ሲሉ በመቃወማቸው ወደ ሁከት ውስጥ እንዲገቡ ያደረገች በመሆኑ በፈጸመችው የሃሰት ወሬዎችን በማውራትና ህዝብን በማነሳሳት ወንጀል ተከሳለች ይላል፡፡
ጉዳዩን ሲመረምረው የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 6ኛ ወንጀል ችሎትም የዐቃቢ ሕግን ክስ ተከሳሿ ማስተባበል ባለመቻሏ ጥፋተኛ ሆና አግኝቻታለሁ ሲል መጋቢት 25 ቀን 2005 ዓ.ም በዋለው ችሎት 2 ዓመት ከ4 ወር ፅኑ እስራትና በ1000 ሺህ ብር እንድትቀጣ ወስኖባታል፡፡

No comments:

Post a Comment