Search

Saturday, November 17, 2012

Who Really Invented the Ethiopian Alphabet?

የ”ሀለሐመ” ፊደል ገበታ ፈጣሪ ማነው?
ከዛጉዬ ስርወ መንግስት በኋላ ግዕዝን ተክቶ ለንግግርና ለፅሁፍ ማገልገል የጀመረውና “የመንግስት የስራ ቋንቋ” የሆነው አማርኛ፤ ግዕዙን የፊደል ገበታ የቀረፀው ማንና መቼ እንደሆነ ለማወቅ ጉጉት እንደፈጠረው ሁሉ የአማርኛው “ሀለሐመ” የሚለውም እንዴት፣ መቼና በእነማን ተፈጠረ ብሎ መጠየቅ አጓጊ ነው፡፡“የፊደል ገበታ አባት” የሚል ቅፅል መጠሪያ ያገኙት ተስፋ ገብረስላሴን የህይወትና የስራ ታሪክ የሚያስቃኘው መፅሃፍ፤ ስለአማርኛ የፊደል ገበታ ፈጣሪዎች ማንነትና ዘመን ማብራሪያ ባይኖረውም፣ ባለታሪኩ በመጀመሪያ በብራና ላይ በእጃቸው እየፃፉ፣ በመቀጠልም በማተሚያ ቤት ማሽን እያባዙ ለህዝብ እንዲደርስ ያደረጉት “የአማርኛ የፊደል ቅርፅ በወቅቱ በእንጦጦ ማርያም፣ በባዓታ ለማርያምና በመካነየሱስ ስላሴ አጥቢያዎች እንዲሁም በገጠር አብያተ ክርስትያናትና በገዳማትና በዋሻዎች ብቻ ተወስኖ” እንደነበር መረጃ ይሰጣል፡፡
ይህ ፍንጭ አጥኚዎች የፊደል ገበታውን በእነዚህ ተቋማት ያኖረውስ ማነው ብለው እንዲጠይቁ የሚያግዝ ጥቆማ ነው፡፡
ለ100 ዓመት ሴተኛ አዳሪዎች ያልተለዩት መንደር
ተስፋ ገብረስላሴ በ1909 ዓ.ም የ15 ዓመት ልጅ ሆነው ከትውልድ መንደራቸው ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ያረፉበት መንደር አራት ኪሎ ነበር፡፡
በዚያ ዘመን ከአራት ኪሎ መንደሮች አንዱ በሆነው “እሪ በከንቱ ደንበኛ መጠጥ ቤቶችና ጥሩ ጥሩ ሴተኛ አዳሪዎች የሚገኙበት የከተማይቱ ደማቅ አካባቢ ፤አዝማሪና ሸላይ የማይታጣበት የቆንጆዎች መቀጣጠሪያ ነበር” ይላል በመፅሃፉ ገፅ 29 የሰፈረ መረጃ፡፡ የፓርላማ ማስፋፊያና የባሻ ወልዴ ችሎት መንደር ለዳግም ልማት ባይፈርስ ኖሮ ሴተኛ አዳሪነት ሁለተኛውን ምዕተ ዓመት ማስቆጠሩ አይቀርም ነበር ወይ ያሰኛል - መረጃው፡፡
ይፍረስ የተባለው የነጋድራስ አቡነከር ቤት
ተስፋ ገብረስላሴ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ ሰርተው ራሳቸውን ለመቻል በእንጨት ፈለጣ፣ ውሃ በመቅዳት፣ ጉድጓድ በመቆፈር፣ በጎዳና ንግድ እና መሰል ትናንሽ ስራዎች ላይ ተሳትፈዋል፡፡ ነጋድራስ አቡበከር ከጅቡቲ ከሚያስመጧቸው በተለይ ሽቶ እየተቀበሉ በየሆቴሉ ዞረው ሸጠዋል፡፡በዘመኑ በአራት ኪሎ መንደር በንግድ ስራቸው በጣም ታዋቂ የነበሩት ነጋድራስ አቡበከር የአፋር ብሄረሰብ ተወላጅ ነበሩ፡፡
ከፈረንሳይ አገር የሚያስመጡትን ሸቀጥ በጅቡቲ በኩል ወደ አዲስ አበባ በማስገባት አገልግሎት ሲሰጡ በዕድሉ ከተጠቀሙት አንዱ የነበሩት ተስፋ ገብረስላሴ፣ በኋለኛው ዘመን ላይ የነጋድራስ ግቢ ለሽያጭ ሲቀርብ ገዝተው ባለንብረት መሆኑ ቻሉ፡፡ ከህትመት ስራ ጋር የተያያዘ ከ100 ዓመት በላይ ታሪክ ያለው ግቢ ከባሻ ወልዴ ዳግም ልማት ስም ይፍረስ መባሉና ከዚህ ጋር የታዩ ክስተቶች ምን እንደሚመስሉ “ዘመን ተሻጋሪ ባለ-ውለታ” ታሪክን አስፍሮ መማሪያ እንዲሆን ማድረግ ችሏል፡፡
መንግስት በከተሞች ያገኘው ቤንዚን
በአሁኑ ወቅት በአገራችን ኢትዮጵያ እየተመዘገበ ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት የነዳጅ ምርትን መሰረት ያደረገ አለመሆኑ ብዙዎችን እንዳስደመመ ይታወቃል፡፡ ካሁን በፊት በመንግስትና በህዝብ የተሰሩትን ሳይጨምር በአምስት ዓመት የትራንስፎርሜሽን እቅድ ተግባራዊ እንዲሆኑ የታቀዱ ሃሳቦችን ለመንደፍ መንግስትን የልብ ልብ የሰጠው ምንድነው ለሚለው ጥያቄ አንዱ መልስ “መንግስት በከተሞች ያገኘው ቤንዚን ነው” የሚል ነው፡፡
ዛሬ በከተማ የሚገኝ አንድ ሜትር ካሬ የመሬት ዋጋ ስንት እየተከፈለበት ነው ለሚለው ጥያቄ አንባቢ ከያለበት ሆኖ የሚያውቀውንና የሰማውን ለራሱ መልስ በመስጠት ያግዘኛል፡፡ የዛሬ 70 ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ ያውም በአራት ኪሎ መንደር ለአንድ ሜትር ካሬ መሬት የተከፈለው ከፍተኛው ገንዘብ 2 ብር ከ35 ሳንቲም ነበር፡፡ የተስፋ ገብረስላሴ ማተሚያ ቤት የሚገኝበት ግቢ ከመጀመሪያው ባለይዞታ ወደ ሁለተኛው ባለሃብት የዞረው በዚህ ሽያጭ እንደነበር የ“ዘመን ተሻጋሪ ባለ-ውለታ” መረጃ ለአንባቢያን አቀብሏል፡፡ ለካንስ መንግስት ለታሪክና ለቅርስ ደንታ የሌለው መስሎ የሚታየው ለ “ነዳጁ” የተለየ ክብርና ዋጋ ስለሰጠ ነውም ያስብላል - መረጃው፡፡
የሚስተር ዴቪድ ውለታ
በ1990ዎቹ አጋማሽ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በወጣ ዜና፤ “የመጀመሪያውን የአማርኛ መፅሃፍ ቅዱስ ተርጉሞ ለህዝብ የቀረበው በዓፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግስት ከእንግሊዝ የመጣ ሚስዮናዊ ነው፡፡” የሚል ማንበቤን አስታውሳለሁ”” የተስፋ ገብረስላሴን የህይወትና የስራ ታሪክ በሚያስቃኘው መፅሃፍ ውስጥ በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን ለወንጌል አገልግሎት ስለመጣ የካቶሊክ ሚሲዮናዊ ስለ ሚስተር ዴቪዲም ያነሳል፡፡
የኤደን ዜግነት የነበረው ሚስተር ዴቪድ፤ ከአፄ ቴዎድሮስ ህልፈት በኋላ በአፄ ምኒልክ ዘመን ወደ አዲስ አበባ በመምጣት “ፒያሳ በተባለው አካባቢ በአሁኑ ሲኒማ አምፒር መደዳ ካለ በአንደኛው ሰቀላ ቤት ላይ መፅሃፍ ቅዱስ እያሳተመ፣ አንዱን መፅሃፍ በአንድ ብር (ማርያትሬዛ) ማንበብና የመግዛት አቅም ላላቸው ሰዎች በየቤታቸው እያንኳኳ ይሸጥ እንደነበር ተገልጿል፡፡
የዚህ ሰው ተግባርና ውለታ ብቻውን በመፅሃፍ በቀረበለት የሚያሰኝ ነው፡፡ የክርስትና ሃይማኖት ለአገራችን የህትመት ዘርፍ፣ ለአማርኛ ቋንቋ ዕድገት፣ ለመፅሃፍ መሸጫ መደብሮች መከፈት፣መፅሃፍ አዙሮ የመሸጥ ስራ ለመጀመር… ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡
ክስ፣እስርና ውንጀላ ያልተለያቸው ባለታሪክ
የተስፋ ገብረስላሴን የስራና የህይወት ታሪክን ማዕከል አድርጎ የአገራችንን ማህበራዊ ፣ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ጉዳዮች በስፋት የሚያስ(ነኘው “ዘመን ተሻጋሪ ባለ-ውለታ” መፅሃፍ፤ ባለ ታሪኩ የህዝብና የአገር ባለውለታ መሆን የቻሉት በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ አልፈው እንደሆነ ይገልፃል፡፡
በንጉሱ ዘመን (ከኢጣሊያ ወረራ በፊትና በኋላ) ፣በጠላት ወረራ ወቅት፣ በደርግም አገዛዝ ለክስ፣ ለእስርና ውንጀላ ተዳርገዋል፡፡ በመጨረሻ ሁሉንም አሸንፈው በተደጋጋሚ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ ከአፄ ኃይለስላሴ መንግስት የቀኝአዝማች ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ደጋግሞ አመስግኗቸዋል፡፡
ሞትን መቅደም
ታላቅ ተግባርና ትልቅ ስም አርቆ መድረሻን ለማቀድ፣ከብዙ ጥረትና ልፋት የሚገኝ ነው፡፡ በአመታት ድካም የተገነባ መልካም ተግባርና ስም ሊጠፋ፣ ሊረሳና ሊዘነጋ የሚችልባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ እኔ ከሞትኩ በኋላ ጥረትና ድካሜ ምን ይሆናል ብሎ ቀድሞ አለማሰብ ታላቅ ተግባርና ስም እንዲጠፋ ሰበብ ከሚሆኑት አንዱ ነው፡፡ ቤተሰቦቻቸውን ባለ አክሲዮን በማድረግ ኃ.የተ.የግ.አ/ማህበር በ1991ዓ.ም ያቋቋሙት ባለታሪኩ፤ ስራና መልካም ተግባራቸው እንዳይጠፋ ማድረግ ችለዋል፡፡
ለሟች መታሰቢያ ሐውልት ይሻላል ቤተ መፅሃፍት
ተስፋ ገብረስላሴ ግንቦት 26 ቀን 1992ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ፣ የ97 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ ነበሩ፡፡ ከመሞታቸው በፊት የቀብር ቦታቸውን በስላሴ ካቴድራል ለማዘጋጀት አስበው የነበረ ቢሆንም የአርበኞች ማህበር አርበኝነታቸውን አላውቅም ስላለ ቀብራቸው በእንጦጦ ኤልያስ ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል፡፡ ባለ ሁለት ክፍል መቃብር ቤት ቤተ መፅሃፍት ሆኖ እንዲያገለግል ስለታሰበም በውስጡ ከ300 በላይ መፅሀፍት ይዟል፡፡
ይህ በአገራችን በስፋት ሊለመድ የሚገባ ጥሩ ጅማሮ ነው፡፡ “የፊደል ገበታ አባት” የሚል ቅዱስ መጠሪያ ያላቸው የቀኝ አዝማች ተስፋ ገብረስላሴን የህትመትና የስራ ታሪክ የሚያስቃኘውን መፅሃፍ የማስተዋወቅ ዳሰሳዬን የማጠቃልለው የዚህ ዓይነት መፅሃፍት ህትመት ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱ ይበል የሚያሰኝ መሆኑን ገልጬ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment