Search

Saturday, March 30, 2013

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የጋብቻ ሥነ ሥርዓታቸውን በሄሊኮፕተር ያካሄዱት ጥንዶች

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የጋብቻ ሥነ ሥርዓታቸውን በሄሊኮፕተር ያካሄዱት ጥንዶች

ሙሽሮቹ "የጋብቻ ሥነ ሥርዓታችንን በሄሊኮፕተር ያካሄድነው ሞልቶን ተርፎን ሳይሆን የኢትዮጵያን የዕድገትና የለውጥ ሂደት ለኢትዮጵያውያንና ለመላው ዓለም ለማሳወቅ ነው" ብለዋል፡፡

"ኢትዮጵያ በዓለም ላይ የምትታወቀው በረሃብና በድርቅ ነው" የሚሉት ሙሽሮቹ " በአሁኑ ወቅት ግን ኢትዮጵያ ዓለምን በሚያስደምም ሁኔታ እያደገች መሆኗንና የተለየ ገጽታ እንዳላት ለማሳወቅ በተለየ ሁኔታ የጋብቻ ሥነ ሥርዓታችንን በሄሊኮፕተር ለማድረግ ችለናል፡፡" ነው የሚሉት ሙሽሮቹ ።

የጋብቻ ሥነ ሥነ ሥርዓታቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ በሄሊኮፕተር ያካሄዱት አቶ ሙሉቀን ፋንታዬ ወይም በቅጽል ስሙ / ሉክ/ እና ወይዘሪት ወይንሸት ሙሉነህ ውይም በቅጽል ስሟ /ወይኒ/ ናቸው፡፡

ሉክ በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ ሙያዎች ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ ወይኒ ደግሞ የአፄ ቴዎድሮስ አራተኛ የልጅ ልጅ ነች፡፡


በሊሞዚን መኪኖች በትልቅ ሆቴል ከሚካሄድ ቅልጥ ያለ የሠርግ ሥነ ሥርዓት ያነሰ ወጪ እንዳወጡ የሚናገሩት ሙሽሮቹ ፥ በጋብቻ ሥነ ሥርዓታቸው ላይ እንዲታደም የጠሩት ሰው ቁጥር 150 ያህል ብቻ ነው፡፡

ምንጭ፦ ኢዜአ

Thursday, March 28, 2013

ሁለት እጅ አልባዋ አብራሪ ጄሲካ ሰኞ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ልምዷን ታካፍላለች


ሁለት እጅ አልባዋ አሜሪካዊትአውሮፕላን አብራሪ ጄሲካ ኮክስ ቻምቤሌይን የፊታችን ሰኞ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ንግግር ታደርጋለች።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ እንደገለጸው ፥ በተፈጥሮ ሁለት እጆቿን ያጣችው የ32 ዓመት ወጣት በዩኒቨርሲቲው ለ300 ተማሪዎች መጋቢት 23 ቀን 2005 ንግግር ታደርግላቸዋለች።
በቀስቃሽ ንግግሮቿ የምትታወቀው ጄሲካ  ወደ ኢትዮጵያ የምትመጣው ሃንዲካፕ ዓለም አቀፍ በተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅትና በአሜሪካ ዓለም የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩ ኤስ ኤይድ) ትብብር ነው።
ጄሲካ በመላው ዓለም እንድትታወቅ ያደረጋት ፥ እጆች ሳይኖሯት አውሮፕላን ለማብረር በመቻሏና ለዚህም የአብራሪነት ፈቃድ ማግኘቷ ነው።
በአሪዞና ግዛት ተስከን የተወለደችው ጄሲካ ከጽንስ ጀምሮ እጆቿ የእግርንም ባህርይ ይዘው በመወለዷ  ፥ ለምታከናውናቸው ተግባራት ችግር እንደማይፈጥርባት መረጃዎች ያመለክታሉ ፤ በዚህም የምትፈልገውን ሁሉ በእግሮቿ ለማድረግ እምብዛም አትቸገርም።
ሃንዲካፕ ዓለም አቀፍ ፥ አካል ጉዳተኛ ሕጻናት ከትምህርት እንዳይገለሉ በሚደረገው ጥረት አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑንም መግለጫው አመልክቷል።

Wednesday, March 20, 2013

ሲሳይ ባንጫ በእሁዱ ጨዋታ አይሰለፍም

በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ ከናይጄሪያ ጋር በነበራት 3ኛ የምድብ ጨዋታ ላይ የቀይ ካርድ የተመለከተው ሲሳይ ባንጫ ፥ በካፍ በመቀጣቱ ቡድኑ እሁድ ከቦትስዋና ጋር በሚኖረው የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ አይሰለፍም።

በሌላ በኩል ቦትስዋና ማላዊን በሜዳዋ አስተናግዳ 1 ለ 0 በሆነ ውጤትያሸነፈች ሲሆን ፥ ቡድኑ ከኢትዮጵያ አቻው ጋር ላለበት የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ነገ አዲስ አበባ ይገባል።
ኢትዮጵያዊው አጥቂ ሳላዲን ሰኢድም ከብሄራዊ  ቡድኑ በቀረበለት ጥሪ መሰረት  ዛሬ ቡድኑን የሚቀላቀል ይሆናል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከትናንት ወዲያ ጀምሮ ልምምድ መጀመሩ የሚታወስ ነው።

Monday, March 18, 2013

አማርኛ በቻይና ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሊሰጥ ነው

በቤጂንግ  የውጭ  ትምህርቶች ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ  ቋንቋን ማስተማር የሚያስችለውን ስምምነት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር ገብቷል ።
ሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች ስምምነቱን ባለፈው ሳምንት  ተፈራርመዋል ።
በስምምነታቸው መሰረትም አማርኛ  ቋንቋ ከሚቀጥለው መስከረም ወር  ጀምሮ በዩኒቨርሲቲው  መሰጠት ይጀመራል ።
የአዲስ  አበባ  ዩኒቨርሲቲም የቻይና  ቋንቋ  ስልጠና  ፕሮግራሙን  ወደ መጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ ከፍ የሚያደርግ ይሆናል ።
የትምህርት መርሃ ግብሩን ለመጀመርም ዛሬ  አዲስ አበባ  ላይ  የስምምነት ፊርማ ይፈፀማል ።