“በድብቅ አላስተላለፍኩም፤ በድርድር ላይ ነን” ኢቴቪ
አለማየሁ አንበሴ በደቡብ አፍሪካ እየተካሄደ የሚገኘውን 29ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ በቀጥታ እያስተላለፈ
የሚገኘው የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ስርጭቱን በድብቅ ሲያስተላልፍ እንደነበረ በይፋ ከተነገረ በኋላ
የተለያዩ አስተያየቶችና ወቀሳዎች እየቀረቡበት ሲሆን ድርጅቱ በበኩሉ ጨዋታው እየተላለፈ ያለው በድብቅ አለመሆኑን
እና እስከ አሁን ድረስ ድርድር እያደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በዕለቱ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በድብቅ እያስተላለፈ
መሆኑን በሚመለከት በቴሌቪዥን ስክሪኑ ላይ የተጻፈው እና በኳስ ተንታኞች የቀረበው ተደጋጋሚ ወቀሳ ድርድር ላይ
ያለው ድርጅት አቋም ነው ወይስ የጋዜጠኛው የሚለውን እያጠራ እንደሆነም ጠቁሟል፡፡ ኢቴቪ ውድድሩ ከመጀመሩ ቀደም
ብሎ ከቴሌቪዥን ባለመብቱ ኩባንያ ጨዋታውን የማስተላለፍ መብት ለማግኘት ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ መጠየቁን አስታውቆ
የተጠየቀው ክፍያ ተገቢ አይደለም በሚል ራሱን ጨምሮ በርካታ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች መቃወማቸውንና በድርድር ላይ
መሆናቸውን አስታውቆ ነበር፡፡
በዚህ ሁኔታ ላይ እያለም ከመክፈቻ ሥነስርዓቱ ጀምሮ ሲያስተላልፍ
ቆይቶ የኢትዮጵያና የዛምቢያ ጨዋታ በሚታይበት ወቅት የኢትዮጵያ ቡድን ጐል ማስቆጠሩን ተከትሎ ጨዋታው ይተላለፍበት
የነበረው “አፌኔክስ” የተሰኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ በስክሪኑ ላይ “ይህን ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴሌቪዥን
ያለፍቃድ እያስተላለፈ ነው” የሚል የእንግሊዝኛ ጽሑፍ መልቀቁ ይታወቃል፡፡ ጽሑፉ ከተለቀቀ በኋላም በወቅቱ ጨዋታውን
ሲዘግቡ የነበሩት ተንታኞች በተደጋጋሚ “ይህን ጨዋታ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ያለፍቃድ እያስተላለፈ ነው፡፡ ምናልባትም
በሕግ ሊጠየቅ ይችላል” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ጣቢያው በሕግ መጠየቅ እና ቅጣትም እንዳለው እያወቀ ያለፍቃድ
ማስተላለፉ ሳያንስ ፍቃድ በሌለውና ክፍያ ባልተፈፀመበት ፕሮግራም ላይ ስፖንሰር ሰብስቦ ማስተላለፍ ተገቢ አለመሆኑን
አስተያየታቸውን ለአዲስ አድማስ የሰጡ የቴሌቪዥን ተከታታዮች ተናግረዋል፡፡ የቴሌቪዥን ፍቃድ ሳያወጡና ግብር
ሳያስከፍሉ ተጠቃሚ መሆን በሕግ ያስቀጣል እያለ ራሱ ለሕግ ተገዢ አለመሆኑ አሳፋሪ ነው” የሚሉ መልዕክቶችም
በማኅበራዊ ድረገፆች ላይ ሲተላለፉ ቆይተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት የመዝናኛና የስፖርት ዘርፍ
የሥራ ሂደት መሪ አቶ ፍቅር ይልቃል ስለተፈጠረው ሁኔታ ለአዲስ አድማስ ሲያብራሩ፤ የጨዋታውን በቴሌቪዥን
የማስተላለፍ መብት ከገዛው መቀመጫውን ቤኒን ካደረገው “LC2-Lancia” ድርጅት ጋር የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቭዥን
ድርጅት እየተደራደረ ቀደም ሲል የተከናወኑትን አምስት የአፍሪካ ዋንጫዎች በደንበኝነት አብረው ሲሠሩ መቆየታቸውን
ገልፀዋል፡፡
አቶ ፍቅር ቀደም ሲል የነበሩትን ድርድሮች በማሳያነት ሲጠቅሱም፣
ከድርጅቱ ጋር ሲሠሩ በነበረበት ወቅት መጀመሪያ አካባቢ ድርጅታቸው ይከፍል የነበረው 50ሺሕ ዩሮ (1ሚ.200 ሺ
ብር) ሲሆን መጨረሻ ላይ ደግሞ የከፈለው 75ሺህ ዩሮ (1ሚ.800ሺ ብር) ነበር፡፡ በዚኛው ጨዋታ ግን ቀደም ሲል
ከነበሩት ከ10 እጥፍ በላይ በመጨመር 750 ሺህ ዩሮ እና የአየር ሰዓት ክፍያ 250 ሺህ ዩሮን ጨምሮ በአጠቃላይ
ወደ 1 ሚሊዮን ዩሮ (24ሚ.ብር) መጠየቁን አብራርተዋል፡፡ ዋጋው በዚህ መልኩ ሊጨምር የቻለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ
ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ በማለፉ ምክንያት ሊሆን ይችላል የሚል የግል አስተያየት እንዳላቸው የተናገሩት አቶ ፍቅር፤
ቀደም ካሉት ክፍያዎች በሚያስገርም ሁኔታ በመጨመሩ ምክንያት የድርድር ሂደቱ ሊራዘም እንደቻለ እና ጉዳዩ ዕልባት
ሳያገኝ ጨዋታው መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ ድርጅታቸውም መልዕክቱ እስከተላለፈበት ጊዜ ድረስ እና አሁንም ጭምር
(በትናንትናው ዕለት) በድርድር ላይ መሆናቸውን፣ ወደ መስማማቱም እየተጠጉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ጨዋታውም ከድርጅቱ
ዕውቅና ውጪ በድብቅ ይተላለፍ የነበረ ባለመሆኑ ድርጅታቸው ላይ የሚደርስ የሕግ ተጠያቂነት እንደሌለ አስረድተዋል፡፡
ድርጅታቸው እስከዛሬ ይካሄዱ የነበሩ 10 የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎችን ሲያስተላልፍ ቆይቶ አሁን የኢትዮጵያ ብሔራዊ
ቡድን የተሰለፈበትን ጨዋታ ሳያስተላልፍ መቅረት የአድማጭ ተመልካቹን ፍላጎት አለማሟላት ነው ያሉት አቶ ፍቅር፤
እስከመጨረሻው ድረስ ተደራድረው ክፍያ በመፈፀም ኢቴቪ ጨዋታውን ማስተላለፉን እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡
ምንጭ : አዲስ አድማስ