Search

Tuesday, September 24, 2013

የከተማ አስተዳደሩ በሚቀጥሉት 2 አመታት 130ሺ ቤቶችን ሊገነባ ነው

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ህዝቡን በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስክ የላቀ ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ከንቲባ ድሪባ ኩማ አስታወቁ፡፡

አስተዳደሩ ባለፉት ዓመታት ያከናወናቸውን የልማት ስራዎች በመገምገም ለቀጣዩቹ 2 ዓመታት ለሚተገብራቸው የልማት እቅዶች አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

ከንቲባ ድሪባ ኩማ እንደገለጹት አስተዳደሩ ለስራ እድል ፈጠራ፣ ለመኖሪያ ቤት ግንባታ፣ ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ፣ ለማስፈጸም አቅም ግንባታና ለመልካም አስተዳደር ስራዎች ቅድሚያ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በከተማዋ የሚታየውን ሰፊ የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለማሟላት በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ የተያዘውን 70ሺህ የመኖሪያ ቤት ግንባታ እቅድ ወደ 130ሺህ ከፍ በማድርግ የህብረተሰቡን የቤት ችግር ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ከንቲባ ድሪባ አስረድተዋል፡፡

አስተዳደሩ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት በጨርቃጨርቅ፣ በአግሮ ኢንዱስትሪ፣ በብረታብረትና በሌሎችም የማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፎች ሰፋፊ ኢንዱስትሪዎችን ከመካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ጋር በማስተሳሰር ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ እንደሚሰራም አመልክተዋል፡፡

አስተዳደሩ በትምህርት ፣በጤናና በሌሎችም የማህበራዊና መሰረተ ልማት ዘርፎች የከተማዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ለሚያስችሉ ስራዎች ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ነው የገለጹት፡፡

ከንቲባ ድሪባ እንዳሉት በመልካም አስተዳደር ረገድም የከተማዋ ነዋሪዎች በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በየዘርፉ ደረጃውን የተጠቀ አገልግሎት ማግኘታቸውን የሚያረጋግጥ ደረጃ ተዘጋጅቶ ባልተፈቱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ዙሪያ የተጠያቂነት አሰራር ተግባራዊ ለማድረግም ዝግጁ ነው፡፡

የከተማው አስተዳደር የኑሮ ውድነትን ለመፍታት በዋነኛነት ለስራ እድል ፈጠራ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው መንግስት በየዓመቱ በብዙ ሚሊዮን ብር ወጪ ወደሀገር ውስጥ የሚያስገባቸው የፍጆታ ዕቃዎች ስርጭትን ህብረተሰቡ በቅርበት እንደሚከታተላቸው በማድረግ የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎች ይሰራሉ ብለዋል፡፡

በአስተዳደሩ በማዕከል፣ በክፍለ ክተማና በወረዳ በየደረጃው የሚገኙ የአስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ተሳታፊ የሆኑበት የእቅድ ውይይት በየደረጃው ያሉ ሀላፊዎች፣ የመንግስት ሰራተኞችና ህዝቡ እንዲወያበት በማድረግ ወደ ተግባር እንደሚገባም አስታውቋል፡፡
Source - ERTA

No comments:

Post a Comment