Monday, April 13, 2015

ድሆች በዚህች አገር መጠጊያና መውደቂያ የላቸውም ማለት ነው?! The purpose of condominiums was for low income households but not anymore




ሪፖርተር 
መንግሥት የኮዶሚኒየም ቤቶችን ፕሮጀክት እውን ያደረገበት ዋነኛ ምክንያት በቤት ችግር ምክንያት የሚሰቃየውን የአዲስ አበባ ኗሪ፣ በተለይም ደግሞ ድሆችን የቤት ባለቤት ለማድረግ እንደሆነ ተደጋግሞ ሲገለጽ ሰምተናል፡፡
አሁንም መንግሥት ይህንኑ የጀመረውን ቤት አልባ ኗሪዎችን የቤት ባለቤት የማድረግ ራዕዩን ሙሉ በሙሉ የተሳካ ለማድረግ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ወጪ በማድረግ እንቅስቃሴውን አጠናክሮ ቀጥሎበታል፡፡
ይህ ሁላችንም እንደ ዜጋ ይበል የሚያሰኝና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቃሉን በተግባር የመጠበቅ አካሄድ ስለሆነ ደስ የሚያሰኘን ነው፡፡ ይሁን እንጂ አስተዳደሩ ቤት አልባ የአዲስ አበባ ኗሪዎችን ባለቤት አደርጋለሁ ባለው ቃሉ ተጠቃሚ እየሆኑ ያሉት በአብዛኛው አቅም ያላቸው የአዲስ አበባ ከተማ ኗሪዎች እንደሆኑ ግን በግልጽ እያየን ነው፡፡ ድሆች ዛሬም የዜና ማድመቂያ እንጂ የዕድሉ ተጠቃሚ መሆን አልቻሉም፡፡
ከሁለት ዓመታት በፊት አስተዳደሩ በነደፈው ዕቅድ መሠረት የከተማውን ኗሪዎች እንደየአቅማቸው የቤት ባለቤት ለማድረግ በነበረው ምዝገባ ወቅት ዓይኖቻችን ብዙ ጉድ አይተዋል፡፡ ውኃ የመሰለ መኪናቸውን ያቆሙ፣ በውድ አልባሳትና ጌጣጌጦች ያሸበረቁ ሰዎች ከእኛ ከድሆቹ እኩል እየተጋፉ ሲመዘገቡ ታዝበን በእውነት እነዚህ ሰዎች አንድ አይደለም ሁሉት ሦስት ቤት የላቸውምን? ስንል የሆዳችንን በሆዳችን አድርገን ብንናገርስ ድሃን ማን ሊሰማው በማለት አርፈንና አፍረን ተቀምጠን ነበር፡፡
እነዚሁ በውጭ አገር የሚኖሩ ልጆቻቸውንና ቤተሰባቸውን የቤት ባለቤት ለማድረግ እኛ ሙሉውንም ቢሆን መክፈል እንችላለን በማለት በእኛ በድሆቹ ላይ ሲመጻደቁ፣ የድሆች አምላክ ፈጣሪ አንተ ሁነና ብለን ወደ ላይ ተማጽነናል፡፡ መንግሥት በኪራይ እየተሰቃዩ ያሉ የከተማችንን ኗሪዎች በተለይም ደግሞ ድሆችን ተጠቃሚ እናደርጋለን በማለት ምሎ ቢገዘትም፣ የቤት ባለቤት የሆኑ ሰዎች የደረሳቸውን የኮንዶሚኒየም ቤቶች ለሌላ ሦስተኛ ወገን በማከራየት እየተጠቀሙ ያሉ በርካታ ሰዎች እንዳሉ ግን የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡
እንዲህ የገንዘብ አቅም ያላቸው ሰዎች ድምፅ ብቻ በሚሰማባት አገር ውስጥ ከአሥር ዓመታት በላይ ተመዝግበው ከነገ ዛሬ ቤት ይደርሰናል ብለው በጉጉት ሲጠባበቁ የነበሩና በድኅነት ተቆራምደን ያሳደግናቸውና የነገ ተስፋ ይሆኑናል ብለን ያልናቸው ልጆቻችን፣ በተከታታይ ገንዘብ አልቆጠባችሁም በሚል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከዕጣ ውጪ በማድረግ ለእኛም ለልጆቻችንም አንጀታችንን የሚበጥስ ወሬ አሰማን፡፡
ለመሆኑ ይህች አገር ድንበሯ ሲጣስ፣ በጠላት ስትወረር ለነፍሱ ሳይሳሳ፣ ዛሬ ተደላድላችሁ የምትመሯትን አገር ደሙን አፍስሶ አጥንቱን ከስክሶ ያቆየው የትኛው ኅብረተሰብ ክፍል ነው፣ ድሃው አይደል እንዴ?! አቅም ያላቸውና ባለገንዘቦቹማ አገር በጭንቅ ስትያዝ በባሌም ሆነ በቦሌ ብለው የአገራቸውን ጭንቀትና ብሶት ወደማያዩበትና ወደማይሰሙበት ወደ አውሮፓና አሜሪካ አይደል እንዴ የሚሰደዱት?
ይኸው ድሃ ሕዝብ አይደል እንዴ በውድም ሆነ በግድ ሠልፍ ውጣ ሲባል ሠልፍ ወጥቶ፣ ተነስ፣ ዝመት፣ ሲባል እሺ ብሎ አንገቱን ደፍቶ የሚታዘዛችሁ? ሠልፋችሁንም ሆነ በዓላችሁን የሚያደምቀው ለመሆኑ የትኛው ሕዝብ ነው፡፡ ታዲያ ይህን የሁልጊዜም ባለውለታችሁ የሆነውን ድሃ ሕዝባችሁን በአገሩ፣ በገዛ ምድሩ ላይ አንዲት ነፍሱን የሚያስጠጋበት መጠለያ እንዳይኖረው ማድረግ የግፍ ግፍ አይደለም እንዴ?!
እነዚህ በድኅነት ተምረው አሁንም ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ገቢ እኛን ቤተሰቦቻቸውን እየደጎሙ ያሉ ልጆቻችን ከየትኛው ደመወዛቸው ተርፎአቸው ነው እናንተ እንደምትሉት በየወሩ 200 እና 300 ብሮችን መቆጠብ የሚችሉት? በተከታታይ ለመቆጠብ አቅሙ ያነሳቸው ልጆቻችን ዕጣ ውስጥ ተካተው ቤቱ ቢደርሳቸው ኖሮ እኛ ወላጆቻቸውም ሆንን እነርሱ ከየትም ከየትም ብለን፣ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንም ለምነን ቢሆን የዕድሉ ተጠቃሚ መሆን እንችል ነበር፡፡ መቼም ሕዝባችን አይጨክንብንምና!!
ግና እኛም ሆነ ልጆቻችን አሁን ምን ዕድል አለን? መንግሥት ድሆች በዚህች ምድር ላይ ቦታም ዕድልም የላቸውም በማለት እንደ አሮጌ ቁና ገፋን፡፡ ለዚህች ምድር ነፃነትና ልዑላዊነት ደማችን እንዳልፈሰሰ፣ ድሆች ልጆቻችን ከእናታቸው ጉያ እየተነጠቁ በደስታውም በሐዘኗም ወቅት ለአገራቸው በግንባር ቀደምትነት ራሳቸውን አሳልፈው እንዳልሰጡ፣ ዛሬ ነፍሳቸውን የሚያስጠጉበት መኖሪያ ተነፈጋቸው፡፡ ለድሆች ቁሜያለሁ የሚለው መንግሥታችንም አቅም ለሌላቸው የከተማችን ኗሪዎች፣ መናጢ ድሆች የቤት ባለቤት የሚሆኑበትን ነገር ወደፊት እናመቻቻለን ሲል ተሳለቀብን፡፡
‹‹እኔ የምሞተው ዛሬ ማታ እህል የሚደርሰው ለፍልሰታ›› እንዲሉ አበው በዚህች አገር እኛ ድሆች በሞት አፋፍ ላይ ስንሆን ነው ማለት ነው የሚታሰብልን፣ መጠጊያና መድረሻ የሌለን እኛ ድሆችስ በዚህች አገር የውራ ውራ የሆንን ዜጎች ነን ማለት ነው?! እኛ ድሆች፣ ልጆቻችንና ቤተሰባችን መቼም አላማረባችሁምና በሚል እንዲህ እንደተንከራተቱ ይኑሩ ብላችሁ ጨክናችሁ ከፈረዳችሁብን እንግዲህ ምን እንላለን? የድሆች አምላክ፣ የኢትዮጵያ አምላክ እግዚአብሔር ይፍረደን ከማለት ውጪ፡፡ አምላክ አገራችንን በሰላም ይጠብቅልን፣ ሕዝባችንንም ከስደትና ከመከራ ይሰውርልን!!
(አያ ምሕረቱና ቤተሰቦቹ፣ ከአዲስ አበባ)

No comments:

Post a Comment