Thursday, September 19, 2013

ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገቡ ተማሪዎች ድልድል ይፋ ሆነ

በ2005 የትምህርት ዘመን የ12  ክፍል  የመሰናዶ  ፈተናን  ካለፉት 163ሺህ 406  ተማሪዎች መካከል  103 ሺህ 394 ተማሪዎች በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበዋል ።
ምደባው ዛሬ  በአገር አቀፍ የትምህርት ምዘና  ኤጀንሲ  የተማሪዎቹ  የዩኒቨርሲቲ  ድልደላ  ተካሂዷል ።
ተማሪዎችም የተመደቡበትን ዩኒቨርሲቲ  በኤጀንሲው ድረ ገፅ www.nae.gov.et በመግባት “placement result” የሚለውን  በመጫን መመልከት ይችላሉ ።
ወይም በአጭር የፅሁፍ መልዕክት plr ፅፎ  የመለያ  ቁጥርን በማስከተል ለ8181 በመላክ የተመደቡበትን ዩኒቨርሲቲ  ማወቅ  የችላሉ ብሏል ኤጀንሲው ።
ምደባው የተከናወነው የ70/30 ቀመርን ባሟላ  መልኩ ከጠቅላላ  ተፈታኞች  ደግሞ  40  በመቶዎቹ  በምህንድስና  ሳይንስ ዘርፍ እንዲገቡ ተደርጓል ።
በምደባው የሴቶችን ተሳትፍ  38 በመቶ  እንዲሆን ታሳቢ  ተደርጎ የተከናወነ ሲሆን ፥ የህክምና  ሳይንስን ምርጫቸው ያደረጉ  ተማሪዎች ደግሞ የመቁረጫ  ነጥብን  ለወንዶች 482  ለሴቶች ደግሞ 477 እንዲሆን  ተደርጓል ።
የምደባ  መመሪያው  በሚፈቅደው መሰረትም  የከፍተኛ  ትምህርት ተቋማትን የቅበላ  አቅምን ታሳቢ ተደርጎ ሴት ተማሩዎች ከወንዶች ጋር ተወዳድረው ከሚያገኙት በተጨማሪ 3 በመቶ እርስ በርሳቸው  ተወዳድረው ወደሚፈልጉት የትምህርት መስክ እንዲገቡ መደረጉን ነው  ኤጀንሲው የገለፀው ።
የሚያጠቡ እናቶች በአቅራቢያቸውና   ተመሳሳይ  ፆታ  ያላቸው  መንትያዎች በአንድ ቦታ እንዲመደቡ እንዲሁም ፥  የጤና  ችግር ያለባቸው  ባቀረቡት  ማስረጃ  መሰረት  ምላሽ  እንዲያገኙ  ተደርጓል ።
በዘንድሮው ድልደላ  በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የሴቶች  ቁጥር ተመጣጣኝ  እንዲሆን  ተደርጓል ።
በኮምፒውተር ታግዞ የተከናወነው ምደባ  የተማሪዎችን ውጤት ፣ የትምህርት መስክንና  የዩኒቨርሲቲ ምርጫን መሰረት በማድረግ  በውድድር ብቻ ተከናውኗል  ብሏል ኤጀንሲው ።
መቀሌ  ዩኒቨርሲቲ  7 ሺህ 312  ተማሪዎቸን  በመቀበል  ቀዳሚው  ሲሆን ፥ አዳማ   ዩኒቨርሲቲ 5 ሺህ 134  ተማሪዎች በመቀበል በሁለተኝነት ሲቀመጥ ፥  4 ሺህ 495 ተማሪዎችን የተቀበለው ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ  ሶስተኛ  ነው ።
ዝቅተኛ  ቁጥር  ያለው ተማሪ  የተቀበለው  ኮተቤ  መምህራን  ትምህርት  ኮሌጅ 955  ተማሪዎች  ተመድበውለታል ።

No comments:

Post a Comment