Tuesday, September 17, 2013

ስለሺ ደምሴ ጋሽ አበራ ሞላ "ያምራል ሀገሬ"ን የሙዚቃ አልበም በብሄራዊ ቴአትር አስመረቀ

ስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ) "ያምራል ሀገሬ"ን በብሄራዊ ቴአትር አስመረቀ
አዲሱ የስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ)"ያምራል ሀገሬ"የሙዚቃ አልበም ጋሽ ሙላቱ አስታጥቄ፤የትዝታው ንጉስ ሙሃሙድ አህመድ፤አብርሃም ወልዴ እና በርካታ የሙዚቃ ባለሙያዎች፤አድናቂዎች በተገኙበት በብሄራዊ ቴአትር ትናንት ምሽት ተመርቋል፡፡የምርቃት ስነ ስርዓቱ በግብዣ ለተጠሩ እንግዶች ብቻ በመሆኑ በርካቶች በቴአትር ቤቱ መግቢያ ላይ ለመግባት አሰፍስፈው አምሽተዋል፡፡
የምርቃት ስነ ስርዓቱን ድምፃዊት ዘሪቱ ጌታሁን ‘’እንቁጣጣሽ’’ በተሰኘ የአዲስ አመት ዜማዋ ከፍታዋለች፡፡ዘሪቱ ከአርባ አመታት በፊት ያቀነቀነችውን ዜማ ዛሬም ከባህላዊ የሙዚቃ ባንድ ጋር በመድረክ ስትጫወት ለታዳሚው የተለየ ደስታን ፈጥራለች፡፡ዛሬም ድረስ ሙሉ የመጫወት አቅሟ አብሯት መኖሩን አሳይታለች፡፡
የ ‘’ኢትዮ ጃዝ’’ አባት እየተባለ የሚጠራው ሙላ አስታጥቄ በመክፈቻ ንግግሩ ስለሺ ደምሴ የኢትዮጵያን ማህበረሰባዊ ሙዚቃ እና የሙዚቃ መሳሪያዎች ጠብቆ ለማቆየት የሚያደርገውን ጥረት አመስግኗል፡፡
በመድረኩ ነግሶ ያመሸው ስለሺ ደምሴ ከአዲሱ የሙዚቃ አልበሙ በርከት ያሉ ስራዎችን ከ"ያምራል ሀገሬ" ባህላዊ የሙዚቃ ቡድን ጋር ተጫውቷል፡፡ስራዎቹ በባህላዊ ጭፈራ እና ክዋኔ የታጀቡ በመሆናቸው ማራኪ ትዕይንት ሆኖ አምሽቷል፡፡
ስለሺ ደምሴ በሙዚቃ ስራው በክራር አጨዋወቱ፤በዜማዎቹ እና ግጥሞቹ እጅጉን የተለየ አቀራረብ እና አጨዋወት የሚከተል የሙዚቃ ሰው ነው፡፡በብሄራዊ ቴአትር ከአዲሱ አልበሙ ባቀረባቸው ስራዎቹ እንቁጣጣሽን እና የሰርግ ዜማን ከተለመደው ለየት ባለ መንገድ በማቅረብ የአድናቂዎቹን ቀልብ ገዝቶ አምሽቷል፡፡

No comments:

Post a Comment