ከ31 ዓመታት በኋላ በአፍሪካ ዋንጫ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምድብ ማጣሪያው ተሰናብቶ ተመልሷል፡፡ የቡድኑን ውጤት ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶች እየተደመጡ ነው፡፡
በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ያደረገውን እንቅስቃሴ መሠረት በማድረግ፣
የአገሪቱ እግር ኳስ የመንግሥትንና የሚመለከታቸውን አካላት ትኩረት ካገኘ ተስፋ እንዳለው ብዙዎች የተስማሙበት
ሆኗል፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ ከአሠልጣኝ ጋር በተገናኙ ድክመቶች እንጂ ቡድኑ የተሻለ ውጤት የሚያስመዘግብበት አቅም
እንደነበረውም የሚናገሩ አሉ፡፡ አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻውስ ምን ይላሉ? ደረጀ ጠገናው እነዚህንና ሌሎችንም ተያያዥ ነጥቦችን በማንሳት አነጋግሯቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ከ31 ዓመታት በኋላ ለ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ በቅቶ ተመልክተናል፡፡ በውጤቱም የተለያዩ አመለካከቶች እየተደመጡ ነው፡፡ የቡድኑ አሠልጣኝ እንደመሆንዎ ውጤቱን እንዴት ይገልፁታል?
የኢትዮጵያ ቡድን ከረጅም ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ የሚያበቃውን ውጤት ለማግኘት ከቅድመ ማጣሪያ ጀምሮ የተለያዩ ውድድሮች አድርጎ ነው ወደ ደቡብ አፍሪካ ያመራው፡፡ ክንውኑም ከአሁን በኋላ ታሪክ ሆኖ ይቀመጣል፡፡ ታሪክ ደግሞ መቼም ቢሆን በጥሩም ሆነ በመጥፎ ሲነሳ የሚኖር ነው፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ግን ከእንግዲህ በኋላ ወደኋላ ተመልሶ እንዳለፉት ዓመታት ተመልካች እንዳይሆንና ወደ ተሻለ ደረጃ ማሸጋገር ይቻል ዘንድ ጥረት ማድረግ የግድ ነው፡፡ ከሁሉም ወገን ከፍተኛ ርብርብ ይጠበቃል፡፡ በደቡብ አፍሪካ ቆይታችን እኔም ሆንኩ ተጫዋቾቼ እጅግ በጣም ብዙ ነገር ተምረናል፡፡ ቡድናችን በመድረኩ የካበተ ልምድ ካላቸው ቡድኖች ጋር ሲወዳደር ታይቷል፡፡ በእንቅስቃሴው በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ያልጣማቸው እንደተጠበቁ ሆኖ ጅምሩን አድንቀዋል፡፡ መንግሥትም ምስጋናውን ሰጥቷል፡፡ ከእንግዲህም መሥራት ከተቻለ የተሻለ ደረጃ መድረስ እንደምንችል፣ በአገሪቱ የተግባር እንጂ የክሕሎት ችግር እንደሌለ አረጋግጠናል፡፡
ውጤቱ አርክቶኛል እያሉ ነው?
በፍጹም በውጤቱ አልረካሁም፡፡ ከዚህ በላይ መሔድ የሚያስችል፣ ነገር ግን በራሳችን ጥቃቅን ስሕተቶች ልጆቹም አቅም እያላቸው መሔድ ሳንችል ቀርተናል፡፡ እግር ኳስ ነውና መቀበል የግድ ነው፡፡ ቁም ነገሩ ካለፈው ስሕተታችን መማሩ ላይ ነው፡፡ ምክንያቱም በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ለዋንጫው ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው አይቮሪኮስት ትጠቀሳለች፡፡ የእግር ኳስ ባሕሪ ነውና የተመለከትነው በተቃራኒው ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ በዙሩ ጨዋታ የተሰናበቱ፣ ነገር ግን ጥሩ የተንቀሳቀሱ ዲሞክራክት ኮንጎ፣ ሞሮኮ፣ አልጄሪያ፣ አንጎላና ሌሎችም አልተሳካላቸውም፡፡ ይህ ማለት የእግር ኳስ ባሕሪ የሚፈጥረው ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ልጆቻችን ቀደም ሲል እንደገለፅኩት ድክመቶቻችን እንደተጠበቁ፣ ሜዳ ላይ ባሳዩት ብቃት ታላላቅ መገናኛ ብዙሃን ሳይቀር አድናቆታቸውን ቸረዋቸዋል፡፡ በዚህ ረክቻለሁ፣ ነገር ግን ውጤቱ አላረካኝም፡፡ ምክንያቱም ከዚያም በላይ መሔድ የሚችል አቅም ስለነበረን ነው፡፡
ተጫዋቾቼ ከዚህ በተሻለ መሔድ ይችሉ ነበር ካሉ ለተፈጠረው ድክመት ምክንያት የሚሉትን ቢገልጹልን?
ባለፈ ነገር ተብሎ እንዳይተረጎምብኝ እንጂ ድክመቶቻችን ለቡርኪና ፋሶ ከነበረን ግምት ይጀምራል፡፡ ቡርኪና ፋሶ ለፍጻሜ የደረሰ ቡድን ሆኗል፡፡ ገና ወደ ደቡብ አፍሪካ ሳንሔድ ከሚዲያው ሳይቀር የኢትዮጵያ ቡድን ከዛምቢያና ናይጀሪያ ነጥብ ተጋርቶ ቡርኪና ፋሶን አሸንፎ ከምድቡ ማለፍ እንደሚችል የተሳሳተ ግምት ነበር ሲነገር የነበረው፡፡ ያለምክንያትም አልነበረም፡፡ የቡርኪና ፋሶ ተጫዋቾችን በወዳጅነትም ሆነ በሌላ አጋጣሚ አልተመለከትናቸውም፡፡ ለተመለከትናቸው ዛምቢያና ናይጀሪያ መሥራት ያለብንን ሠርተን ቡርኪና ፋሶን ግን በቀላሉ እንደምናሸንፍ ራሳችን እንድናሳምን ሆነ፣ እኔም ሆንኩ ልጆቼ ተመሳሳይ ስሜት ነበረን፡፡ መሥራት ያለብንን ሳንሠራ እምነት መጣል እጅግ በጣም ትልቅ ስሕተት ነው፡፡ ለወደፊቱም ትልቅ ትምህርት ሰጥቶናል፡፡
ከቡርኪና ፋሶ ጋር በነበራችሁ ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ 20 እና 25 ደቂቃዎች በኳስ ቁጥጥር ተሽላችሁ ነበር፡፡ ነገር ግን መዝለቅ አልቻላችሁም?
እውነት ነው፡፡ ጨዋታው ሲጀመር ቀለውን ስለነበር ልጆቻችን መከፋፈት ጀመሩ፡፡ እንደተመለከትነው ሺመልስና ሳላዲን ሰይድ በቀላሉ ጎል መሆን የሚችሉ ኳሶች አምልጧቸዋል፡፡ ለተጨማሪ ሙከራ ጫና ማድረግ ነበረብን፡፡ በክፍተቶቻችን ሊጠቀሙብን ቻሉ፡፡
ክፍተቱን ማስተካከል የማን ድርሻ ነበር?
ምክንያት ለማቅረብ ሳይሆን፣ ድክመቱ ከእኔ ጀምሮ የሁላችንም ነው፡፡ ማስተካከል አልቻልንም፣ ቀላል ኳሶች ሳይቀር እየተነጠቁ ጎል ተቆጥሮብናል፡፡ ማስተካከል ያለብን ድክመት ነው፡፡ ተጫዋቹም በሒደት ዓለም አቀፍ ልምድና ተሞክሮን እያጎለበቱ ሲሔዱ የሚቀረፍ ነው፡፡ ጥሩ ትምህርት ሰጥቶን እንዳለፈ ክስተት ነው የምወስደው፡፡
ዓለም አቀፍ ልምድ እጦት ለድክመታችን መንስዔ ሆኗል እያሉ ነው?
ግልፅ ነው፡፡ ለምሳሌ ከናይጀሪያ ጋር በነበረን ጨዋታ፣ በጨዋታ ተበልጠን አልነበረም ጎል የተቆጠረብን፡፡ ጨዋታውን እንደተመለከትነው እስከ 80ኛው ደቂቃ ድረስ 0ለ0 ነበርን፡፡ ጎል ማስቆጠር ካልቻልን አቻ አይጠቅመንም፡፡ ጎል ለማግባት ደግሞ ሰዓቱም በመጠናቀቅ ላይ ስለነበር የተጫዋቾቻችን በስሜት መሳብ ለጎሉ መቆጠር ምክንያት ሆነ፡፡ ናይጀሪያውያን በልምድ የተሻሉ ስለነበሩ በክፍተቶቻችን ተጠቀሙ፡፡ ልብ ብለን ከሆነ እስከ 80ኛው ደቂቃ ሳላዲን ሰይድን ለሦስት ሲይዙት ነበር፡፡ የእኛ ልጆች እየተነገራቸው ቦታቸውን ማስጠበቅ ተስኗቸው ነበር፡፡ የእኛ ተጫዋቾች ናይጀሪያውያኑን ከጨዋታ ውጭ ለማድረግ የቦታ አጠቃቀማቸው በራሱ ከፍተኛ ችግር ነበረበት፡፡ እነዚህ ሁሉ ከልምድ ማነስ የመጡ ናቸው እንጂ ልጆቻችን መጫወት ተስኗቸው አልነበረም፡፡
እነዚህና ሌሎችም በርካታ ድክመቶቻችንን በቀጣይ በምናደርጋቸው የወዳጅነትና መደበኛ ውድድሮች የሚቀረፉ እንደሚሆኑ የፀና እምነት አለኝ፡፡
የኢትዮጵያ ቡድን በውድድሩ ሦስት ጨዋታዎችን አድርጓል፡፡ በሦስቱም ጨዋታዎች የመጀመሪያ ተሰላፊ ተጫዋቾችን ከመምረጥ ጀምሮ የጨዋታውን አጠቃላይ ድክመትና ጥንካሬ እንዴት ይገልፁታል?
ሲጀመር ዛምቢያ ያለፈው ዓመት የአፍሪካ ሻምፒዮን ነው፡፡ ጠንካራ ቡድን መሆኑን እናውቃለን፣ ክብደትም ሰጥተንዋል፡፡ ጨዋታው ከባድ እንደሚሆን ግምት ነበረን፡፡ እንቅስቃሴያችንም ጥንቃቄ የተመላበት ነበር፡፡ ጀማል ጣሰው (በረኛው) በቀይ የወጣው ጨዋታው 40 ደቂቃ እየቀረው ነው፡፡ በአሥር ልጆች የአሰላለፍ ሽግሽግ ተደርጎ በጥሩ የኳሱ ቅብብል ውጤቱን አስጠብቀን መውጣት ችለናል፡፡ በወቅቱ የነበረው የሙቀት መጠን 35 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ነበር፡፡ በዚያ ላይ ልጆቻችን የነበራቸውን ሁሉ አሟጠው ተጠቅመዋል፡፡ ብዙዎቹ ልጆች ወደ አቋማቸው ለመመለስ 48 ሰዓት መጠበቅ ነበረባቸው፡፡ እኛ ደግሞ በየቀኑ ለአንድ ሰዓት ያህል ልምምድ ማድረግ የግድ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ ክፍተቱን ለማስተካከል ለቡርኪና ፋሶ ጨዋታ የግድ የተወሰኑ ልጆችን መለወጥ ነበረብን፡፡ ያስገባናቸው ልጆችም ቢሆኑ ኳስ ተቆጣጥሮ መጫወት የሚችሉ ለመሆናቸው በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ተመልክተናቸዋል፡፡ ነገር ግን ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደሞከርኩት ሳናሸንፋቸው እንደምናሸንፋቸው አምነን የገባንበት ስለነበር ውጤቱ በታየው መልኩ ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡ ሦስተኛውንና ከናይጀሪያ ጋር ያደረግነውን ጨዋታ በተመለከተ ብዙዎቹ ተጫዋቾች ከድካማቸው አገግመው ስለነበረ ጨዋታውን ቢያንስ 1ለ0 ለማጠናቀቅ ተነጋግረን ነው የገባነው፡፡ ናይጀሪያውያኑም የታክቲክ ተጫዋቾች በመሆናቸው ተቆጣጥረን ለመጫወት አልከበዱንም፡፡ በኳስ ዓለም ከባዱ ከታክቲክ ውጭ እንደ ጎርፍ የሚመጣ ቡድን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ነው፡፡ ነገር ግን ማን የት እንደሚጫወት ከታወቀ አያስቸግርም፡፡ በዋናነት ደግሞ ልጆቹ በቡርኪና ፋሶ ላይ የሠሩት ስህተት ስላስቆጫቸው ለናይጀሪያ ጥንቃቄ አድርገው የገቡበትና ጥሩም የተንቀሳቀሱበት ነበር የነበረው፡፡
የኢትዮጵያ ቡድን በሥነ ልቦናውም ሆነ በአካል ብቃቱ ረገድ ብዙ እንደሚቀረው ለዚያም ቡድኑ የግጥሚያ ቡድን እንዳልሆነ ማሳያው በቡርኪና ፋሶ ጨዋታ፣ ጨዋታውን በጀመረበት ትንፋሽ ሊጨርስ አልቻለም፡፡ ሌላው ደግሞ ጎል ሲቆጠርበት ተረጋግቶ ከመጫወት ይልቅ ሲደነባበር ታይቷል፡፡ ይህስ እንደመከራከሪያ ሊቀርብ አይችልም?
ክርክር የሚወድ መከራከሪያ አያጣም፡፡ ማንም ሰው የሚመስለውን መናገር ይችላል፡፡ ነገር ግን የሚመስለውን ስለተባለ ብቻ ፍሬ የማይቋጥር መከራከሪያ ማቅረብ ትርፉ ጊዜ ማጥፋት ነው፡፡ ወደ ጥያቄው ስመለስ ሥነ ልቦና ስለተባለው ባለሙያ አብሮን ተጉዟል፡፡ ባለሙያው በየጊዜው ከተጨዋቾቹ ጋር እየተገናኘ ማድረግ ያለበትን አድርጓል፡፡ ዋናውና ለድክመቱ መፈጠር የዛምቢያን ጨዋታ ተከትሎ አድናቆት መብዛቱ ነው፡፡ ከአቅም በላይ መካብ ይዞት የሚመጣው ችግር አደገኛ ነው፡፡ እውን ሆኖ ያየነውም ይኼው ነው፡፡
የአድናቆቱ ትርጉም ገብትዎት ከሆነ ተጫዋቾቹ ጥንቃቄ እንዳያደርጉ ማዘናጊያም ሊሆን ስለሚችል የማስረዳት ኃላፊነት አልነበረብዎትም?
በሚገባ ተናግሬያለሁ፡፡ ሠርተናል ብለን እንዳንኩራራ መድረክ ፈጥረን አውርተናል፡፡ መኩራራት የሚገባን ለሕዝባችን ቃል የገባነውን አሳክተን ስንገኝ ሊሆን እንደሚገባው ተነጋግረናል፡፡ ምክንያቱም ተጋጣሚያችን የተቻለውን ሁሉ ለማድረግ ጥርሱን ነክሶ ስለሚመጣ ማለት ነው፡፡
በሦስት ጨዋታ ሙሉ 23 ተጫዋቾችን የተጠቀመ የመጀመሪያው አሠልጣኝ የሚሉ አሉ፡፡ እውን እርሶ የመጀመሪያ ተመራጭ አሥራ አንድ ምርጥ ነበረዎት ማለት ይቻላል?
ያለኝን ኃይል መጠቀሜ አሪፍ ያስብለኛል እንጂ አያስተቸኝም፡፡ ምክንያቱም አሥራ አንድ ልጆች ሲፋለሙ የተቀረው አብሮ የተጓዘው ሸሚዝ ሊገዛ ነው? አዳነ ወይም አስራት ሲጎዱ ሁለቱን ተጫዋቾች ተክተው የሚገቡ ተጫዋቾች ተጠባባቂ ነን ብለው እንዲያስቡ ፍላጎት የለኝም፡፡ አዳነም ሆነ አስራት አልያም ምንያህል ከ23ቱ ተጫዋቾች እኩል ናቸው፡፡ ተክተው የሚጫወቱ ልጆች የ23ቱ ልጆች አባላት ናቸው፡፡ እንዲያውም ሁሉንም መጠቀም መቻል ጉልበት ለመቆጠብ አማራጭ ነው፡፡ መታየት ያለበት የ23ቱ ልጆች አባል የተደረገው ተጫዋች ብቃት ሳይኖረው ከሆነ መነጋገር ይቻላል፡፡ ችሎ የተመረጠ ከሆነ ግን ለምን ተሰለፈ ማለት ከሆነ እቸገራለሁ፡፡ ዋናው ነገር የገቡት ሁሉ ኃላፊነታቸውን በሚገባ ተወጥተዋል አልተወጡም የሚለው ስለሆነ በቀጣይ የተሻለውን ይዞ ለመቀጠል ጠቃሚ ነው፡፡ ጥያቄው መነሻ አለው፣ ምክንያቱም በርካታ አሉባልታዎች እሰማለሁ፡፡ አሥራ አንድ ምርጥ የለውም የሚባል ነገር አለ፡፡ ምን ማለት እንደሆነ ግልፅ አይደለም፡፡ ከዛምቢያ ጋር የተጫወተው ቡድን ምርጥ አሥራ አንድ አይደለም? ጉዳትና ድካም ሲፈጠርስ መቀየር የለበትም?፣ የገቡትስ ምርጥ አሥራ አንድ አይደሉም?፣ ካልሆኑ የቡድኑ አባል ሆነው መሔዳቸው ስህተት ነበር ማለት ነው፡፡ አዳነ ግርማና አስራት መገርሳ ተጎዱ፣ ጀማል ጣሰው በቀይ ወጣ መተካት የለባቸውም? ወይስ በሽተኞቹን በመርፌ ማስገባት ነበረብኝ?
ሙያተኞች መከራከሪያ አላቸው?
ይህን ያሉት ሙያተኞች ከሆኑ መድረክ ፈጥሮ መነጋገር ይቻላል፡፡ በዚህ ጉዳይ ተጨባጭ መከራከሪያ ይዞ የሚነግረኝ ካለ የምቀበለው በደስታ ነው፡፡ በጓሮ ከሆነ ግን ጥቅም የለውም፡፡ ስሕተት ከሆነ መተራረም ክፋት የለውም፡፡ ከፊት ለፊታችን ታላላቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ይጠብቁናል፡፡ ተቀራርበንና በግልፅ ተነጋግረን የሚጠቅመውን ሐሳብ ይዘን መሔድ ወቅቱ የሚጠይቀውና ተመራጭም ነው፡፡
መከራከሪያ ሐሳቡ ለፍፃሜ የቀረቡትን ናይጀሪያንና ቡርኪና ፋሶ ከአምስት ጨዋታ በላይ ሲያደርጉ የተጠቀሟቸው ተጫዋቾች አሥራ አምስት የህሉን ነው፡፡ ተጫዋች ሲጎዳ የሚቀየሩ እንደተጠበቁ ሆኖ፣ ነገር ግን የተቀሩት አብሮ የመጫወት ተደጋጋሚ ዕድል ባገኙ ቁጥር የበለጠ እየተግባቡ የሚሄዱበት ሁኔታ የበለጠ ጥቅም እንዳለው ነው፡፡
አባባሉ እውነትነት ቢኖረውም፣ ነገር ግን እኛ የቀየርናቸው ልጆች መቀየር ያለባቸውን ነው፡፡ ለምሳሌ ሳላዲንን አልቀየርንም፡፡ አቅም የነበራቸውን ምንያህልና ሌሎችንም ያሳረፍነው ለተወሰኑ ደቂቃዎች ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ሙሉ ለሙሉ እንዲቀየሩ የተደረጉ ልጆች በቢጫና ቀይ ካርድ እንዲያርፉ የተደረጉ ናቸው፡፡ ሌሎቹም ቢሆኑ መቀየር ስላለባቸው የተቀየሩ እንጂ የተለየ ፍልስፍና ኖሮኝ አይደለም፡፡ ክፍተቶችን ለመድፈን ታስቦ የሚደረግ አማራጭ ነው፡፡ ተቀይረው የገቡ ተጫዋቾች ውጤታማ ሲሆኑ ማጨብጨብ፣ ካልተሳካላቸው ደግሞ የትችት ስለት መምዘዝ ዕድገት አያመጣም፡፡ ዕድገት የሚመጣው ቀና በሆነ አመለካከት ደካማና ጠንካራ ጎኖችን በስታስቲክስ ተደግፎ ተነጋግሮ ወደ ሚበጀው አቅጣጫ በመሔድ ነው፡፡
አሠልጣኙ ተጫዋቾችን መቀያየር ያበዙት ጫና ስለሚፈሩ ነው የሚሉ አሉ፡፡
በፍፁም ያመንኩበትን ካልሆነ የሰዎችን ጫና ፈርቼ ለሰከንድ አላደርገውም፡፡ ለወደፊቱም ቢሆን የማደርገው አይደለም፡፡ ሲጀምርም ጫና ያደረገብኝ አካል የለም፡፡ ያደረግኩት ማድረግ ስለነበረብኝ ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ልጆቼን ከመነሻው ጀምሮ እንቅስቅሴያቸውንና ወቅታዊ ብቃታቸውን የማውቀው እኔ ነኝ፡፡ ባየሁትና ይጠቅመኛል ባልኩት መሠረትና ድክመት በተመለከትኩት ቦታ ደግሞ ቀይሬ የማስገባውን ተጫዋች ማንነት መወሰን የእኔ ነው፡፡ አሠራሩም ይኼው ነው፡፡
ቡድኑ በዲሲፕሊን ረገድ እጅግ በጣም ብዙ ጉድለቶች እንደነበሩበት ግልፅ ነበር፡፡ ይቀበሉታል ወይስ….?
ትክክል ነው፣ የዲሲፕሊን ጉዳይ ከፍተኛ ዋጋ ካስከፈሉን ድክመቶቻችን ዋነኛው ነው፡፡ በዚህ ረገድ ብዙ መሥራት አለብን፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ የተመለከትነው በአዲስ አበባ ስታዲየም ያዳበርነውን ተሞክሮ ነው፡፡ ስለዚህ ተጫዋቾቻችን ሁሉም የዳኛን ውሳኔ በፀጋ ከመቀበል ይልቅ መክበብና ማመነጫጨቅ ነበር፡፡ ድርጊቱ በአዲስ አበባ ስታዲየም ተቀባይነት ኖሮት ይሆናል፡፡ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ግን አላስኬደንም፡፡ በአዲስ አበባ ስታዲየም ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ተቃራኒ ተጫዋችን አፈር ከድሜ የሚቀላቅል ተከላካይ በተመልካች ጩኸት የዳኛ ቀይና ቢጫ ካርድ ሰለባ ከመሆን ሲያመልጥ የኖረ መጥለፍ ቀርቶ መነካካት በማይቻልበት መድረክ መጋለጡ አይቀርም፡፡ የገጠመን ይኼው ነው፡፡
በዚህ በኩል ዳኞቻችን ሕጉን በመተግበር ተጫዋቾችን መስመር ማስያዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሙያ ግዴታቸውም ነው፡፡ የክለብ አመራሮች፣ አሠልጣኞችና ደጋፊዎች ለሕጉ መተግበር አጋር መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ካልሆነ ግን ጉዳቱ ለአገር ነው፡፡ እያንዳንዱ ተጫዋች የዲሲፕሊኑ ሁኔታ መታየት ያለበት በክለቡ ነው፡፡ ሰውነት ጋር ሲመጣ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ተጣሞ እንዲያድግ የተደረገ ዛፍ ከጠነከረ በኋላ ለማቃናት እንደማይቻል ሁሉ ወደ ብሔራዊ ቡድን የሚመጡ ተጫዋቾችም በሁሉ ነገር ተስተካክሎ ነው መምጣት ያለባቸው፡፡ ለአፍሪካ ዋንጫ የመጨረሻ ማጣሪያ የተጫወትነው ከሱዳን ብሔራዊ ቡድን ጋር መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚያን ወቅት የቡድኑ ዋና በረኛ ሲሳይ ባንጫ ነበር፡፡ ሲሳይ በሱዳኑ ጨዋታ ቢጫ ካርድ እንዳይመለከት በሚገባ ተነጋግረን ነው ወደ ሜዳ ያገባው፡፡
ሲሳይ ግን የተነጋገርነውን ሁሉ ዘንግቶ የቢጫ ካርድ ሰለባ ሆነ፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ነገር የዳኞች ኮሚቴ ለሚመድባቸው ዳኞች የማያዳግም ምክርና ተግሳፅ መስጠት መቻል ይኖርበታል፡፡ ክለቦችና ደጋፊዎች ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መሥራት አለበት፡፡ ምክንያቱ አሠልጣኝ ሰውነት ሱቅ ሔዶ ያለቀለት ኮትና ሱሪ መግዛት ሲገባው የጎደለ ነገር ይዞ ከሔደ ችግሩ የራሱ ነው፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ ከዲሲፕሊን ጋር በተያያዘ የተመለከትናቸው ጥፋቶች የራሳችን ድክመቶች ናቸው፡፡ የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋች ሲመጣ ሁሉን ነገር በልኩ ጨርሶ መምጣት አለበት፡፡ ሰውነት እንዲገራው የሚጠብቅ ካለ ተሳስቷል፡፡
በዚህ ረገድ ዋጋ ከፍለናል ብለን እንቀበል?
እጅግ በጣም፡፡
ኃላፊነትን ለመሸሽ ሆን ብለው የሚያደርጉ ተጫዋቾች እንዳሉ ይነገራል?
ውሸት ነው፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ ገብቶ መጫወት የማይፈልግ የለም፡፡ ድርጊቱ የሚፈጠረው በውስጣቸው ይዘውት የቆየው በእንቅስቃሴ ወቅት ባልጠበቁት መንገድ ስለሚወጣ ነው፡፡ ይህ ግን እናቴ በእንቁላሉ ጊዜ… እንደሚባለው ቀደም ብሎ እርምት ተደርጎበት ቢሆን ግን አንቸገርም፡፡ የእኛ ተጫዋቾች ከተቀሩት የአፍሪካ አገሮች ተጫዋቾች ጋር ሲነጻጸሩ የልምዱ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ በዲሲፕሊን ረገድ ከፍተኛ ድክመት ነበረባቸው፡፡ እግር ኳስ በስሜት አይሆንም፡፡ ከአደጋ ቀጣና ኳስ መውጣት ባለበት ሰዓት ኳስ እንዲያወጣ የሚነገረው ተጫዋች የተባለውን የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡ ይህንን ማድረግ ካልቻልን ግን ልጆቻችን በፍፁም ከማንም ጋር ቢገናኙ እንደማያንሱ ማረጋገጥ እፈልጋለሁ፡፡ ናይጀሪያዊው ጆብ ኦቢ ሚካኤል ምን ያህልን የበለጠው በቁመት እንጂ ኳስን በተገቢው መንገድ አደራጅቶ ለጓደኛ በማድረሱ አይደለም፡፡ በእርግጥ የአየር ኳስ በጭንቅላት በመግጨት ይበልጠዋል፡፡ ለዚያም መፍትሔ ያልነው ኳስ በመሬት ካልሆነ የሰማይ ኳሱ እንዳንጠቀም ነው፣ ተግብረነዋልም፡፡ አንድ ሳላዲን ብቻውን ባለበት የክንፍ ኳስ ሴንተር እንዲደረጉ አልፈቀድንም፡፡ የጨዋታውን ስታስቲክ ስንመለከት ከሦስት ጨዋታ ለሳላዲን ክሮስ የተደረገው በናይጀሪያው ጨዋታ ላይ አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡
የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎዋችንን ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶች እየተደመጡ ነው፡፡ እግር ኳሱ ከመንግሥት ጀምሮ እስከ ክለቦችና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት መሠረታዊ የሆነው ሥራ መሥራት ከተቻለ የክሕሎት ችግር እንደሌለ ነው፡፡
እግር ኳስ ተጨዋች የለም የሚሉ ካሉ ከተጠያቂነት መሸሽ እንዳይሆን እሰጋለሁ፡፡ ምክንያቱም አሁን በአፍሪካ ዋንጫ ከተመለክተናቸው ተጨዋቾቻችን ለአንድ እግር ኳስ ተጨዋች የሚደረግለት ተደርጎለት ያደገ ካለ መወቀስ እችላለሁ፡፡ እውነቱ ግን ማናቸውም በአጋጣሚ ካልሆነ ደረጃውን በጠበቀ ፕሮጀክት ወይም ተመሳሳይ ነገር እገዛ ተደርጎለት እዚህ ደረጃ የደረሰ የለም፡፡ እነዚህ ልጆች በአጋጣሚ እግር ኳስን እየተጫወቱ አድገው ነው፣ ሁሉ ነገር ተሟልቶላቸው ካደጉ አገሮች ጋር ተገናኝተው የተሻለ መንቀሳቀስ እንደሚችሉ ካሳዩን በአገሪቱ በክለቦችም ይሁን በሌላ አጋጣሚ ነገሮች ተሟልተው ለታዳጊ ተጨዋቾች ትኩረት ቢሰጥ የት መድረስ እንደሚቻል ለመገመት ነቢይ መሆንን አይጠይቅም፡፡ ፕሮጀክት ተነድፎ፣ በዚያ መሠረት ታዳጊ ወጣቶች በዕድሜያቸው ማግኘት የሚገባቸውን ሥልጠና አግኝተው እንዲያድጉ ቢደረግ፣ ክለቦቻችን በእግር ኳስ ከውድድር ባሻገር ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ለማግኘት ዓላማ ካላቸው መሆን ይቻላል፡፡ ስለሆነም አደረጃጀቶቻቸውን ሕዝባዊ መሠረት አሲዘው ከፕሮጀክት ጀምሮ ‹‹ሲ›› እና ‹‹ቢ›› ቡድኖቻቸው ላይ ጠንክረው ቢሠሩ ዓለምን የሚያስደምሙ አስራ አንድ ምርጦችን ቀርቶ፣ አምስትና ስድስት ምርጥ ብሔራዊ ቡድኖች ማፍራት ይቻላል፣ በቂ ክሕሎት አለ፡፡
መንግሥት በአሁኑ ወቅት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ በገርጂ አካባቢ እየተገነባ ያለው የወጣቶች አካዴሚ ሥራ ከጀመረ ችግሩን ሙሉ ለሙሉም ባይሆን ለውጦችን እናያለን የሚል እምነት አለኝ፡፡ የክልል መንግሥታትም ተመሳሳይ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ መንግሥት የበኩሉን ድርሻ መወጣት ይኖርበታል፡፡ ክለቦቻችን በተመሳሳይ ራሳቸውን መፈተሽና ወደ ትክክለኛው መስመር እንዲገቡ መደረግ አለበት፡፡ ምክንያቱም በአገሪቱ ከጥቂት ክለቦች በስተቀር አብዛኞቹ በመንግሥት በጀት የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ እያንዳንዳቸው በዓመት አኃዙን በትክክል መግለጽ ባልችልም፣ የዓመት በጀታቸው ከ10 ሚሊዮን ብር እንደማያንስ ነው፡፡ በፕሪሚየር ሊጉ ብቻ የሚወዳደሩ 14 ክለቦች አሉ፡፡ የሁሉም ሲደመር 140 ሚሊዮን ብር ማለት ነው፡፡ እውን እግር ኳሱ ከውድድር ባለፈ ለሚወጣበት ገንዘብና ሕዝቡ የሚፈለገውን ለውጥ አምጥቷል?፣ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ለውጥ ማምጣት ቀርቶ አቅጣጫውን ያገኘ አይመስልም፡፡ ከዚህ ውስጥ የተወሰነውን ቀንሶ ለታዳጊ ወጣት ፕሮጀክቶች ቢውል በግሌ እመርጣለሁ፡፡ ምክንያቱም መሠረት በሌለው ነገር የትም ልንደርስ አንችልም፡፡
እግር ኳሱን ወደ ገንዘብ ከመለወጥ አንጻርስ?
ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደሞከርኩት እግር ኳሱን ለመለወጥ አደረጃጀቶች ሲለወጡ እግር ኳሱም የግድ የፋይናንስ አማራጭ መሆኑ የማይቀር ነው፡፡ ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ከተመለከትን በቂ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ግን መሠረቱ ላይ የግድ መሥራት ይጠይቃል፡፡ እየተንገታገትን ያለው በሌላና መሠረት በሌለው ነገር ነው፡፡ ክለቦቻችን የታዳጊ ወጣት ፕሮጀክቶች ቀርቶ ‹‹ሲ›› እና ‹‹ቢ›› ያላቸው ስንቶቹ ናቸው? የራሳቸው ሜዳስ ያላቸው ብለን ስናነሳ መሬት ላይ የምናገኘው ስሌት ዜሮ ነው፡፡ እሩቅ ሳንሔድ የሱዳን ክለቦች ሜሪክና አልሂላል የራሳቸው ሜዳ አላቸው፡፡ በዚያ ላይ ታዳጊዎቻቸውን የሚያሳድጉበት የሥልጠና ተቋም አላቸው፡፡ ለምን እኛስ? ትላልቅ ገቢ ያላቸው ኩባንያዎችና ድርጅቶች አሉን፡፡ በአገሪቱ የሥርዓትና የዕቅድ ችግር እንጂ የገንዘብ ችግር እንደሌለባት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት ወቅት የተገኘውን ገንዘብ መመልከቱ በቂ ነው፡፡ ወጣቶች ላይ ኢንቨስት የማድረጉ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው፡፡
በተጨዋቾቻችን የዕድሜ ችግር ተጨማሪ ችግር ተደርጎ እየተነገረ ነው፤
ምንም ዓይነት ሥርዓት በሌለበት፣ ታዳጊዎች በዕድሜያቸው የሚሠሩበት ተቋም በሌለበት የዕድሜ ችግር ባይኖር ነው የሚገርመኝ፡፡
የአፍሪካ ዋንጫን ተከትሎ ገንዘብ ተገኝቷል፡፡ ይህ ለፌዴሬሽኑም ሆነ ለክለቦች ምን ትርጉም አለው?
ፌዴሬሽኑ እስከዛሬ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ገንዘብ ማግኘት የቻለው የብሔራዊ ቡድኑን ውጤት ተከትሎ ነው፡፡ ስለዚህ ፌዴሬሽኑም ሆነ ክለቦች ከዚህ የተሻለ ቢሠሩ አሁን ከተገኘው በበለጠ ተጠቃሚ የሚሆኑበት አጋጣሚ እንደሚኖር ነው፡፡ ለዚህ ነው የታየውን የእግር ኳስ ጭላንጭል ለማስቀጠል ከመሠረቱ መሥራት ይኖርብናል የምለው፡፡
ለ2014 የዓለም ዋንጫ ኢትዮጵያ ምድቧን እየመራች ነው፡፡ ምን እንጠብቅ?
ተጨዋቾቻችን ከአፍሪካ ዋንጫ ብዙ ተምረዋል፡፡ ከእንግዲህ ማንንም የሚፈሩበት ወቅት አብቅቷል፡፡ በሚገባ ማጣሪያውን አልፈን ወደ ብራዚል እናመራለን፡፡
ዝግጅት የሚጀመረው መቼ ነው?
ከሚቀጥሉት ሁለት ሳምንት በኋላ ተጨዋቾቹ ይሰባሰባሉ፡፡ ምክንያቱም በአፍሪካ ዋንጫ የተመለከትናቸውን ድክመቶቻችንን ማረም የምንችለው በሚኖረን የዝግጅት ጊዜ ነው፡፡ የተሻለ ቡድን ለመሥራት የተሻለ የዝግጅት ጊዜ የግድ ነው፡፡
በአፍሪካ ዋንጫ ስኬትዎ ፌዴሬሽኑና መንግሥት የተለያዩ ማበረታቻዎችን አበርክቶልዎታል?
ከማስበው በላይ ነው፣ ቃላት ያጥረኛል፡፡
ከዚህ በፊት እንደተነገረው፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያበረከተልዎት ሽልማት ሊፋን የቤት መኪና መሆኑን ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን የፌዴሬሽኑ ሽልማት መኪና ሳይሆን፣ ለመኪና መግዢያ የሚውል የገንዘብ ሽልማት እንደሆነ ነው፡፡
ገንዘቡ መኪናዋን መግዛት ከቻለ ምን ችግር አለው? የሆነ ሆኖ ግን ፌዴሬሽኑ የሰጠኝ ገንዘብ 520 ሊፋን የቤት መኪና መግዣ የሚሆን 288.000 ብር ነው፡፡ መኪናዋ ትንሽ ስለሆነች ከእሷ የተሻለ ሞዴል ለመግዛት ከሊፋን ጋር ተነጋግሬ ጨርሻለሁ፡፡
ምንጭ: ሪፖርተር
No comments:
Post a Comment