Search

Monday, December 24, 2012

የአሊያንስ ትራንስፖርት ሰርቪስ አክስዮን ማህበር አውቶቡስ አገልግሎት መስጠት ሊጀምር ነው

የትራንስፖርት ዋጋው ከታክሲ ዋጋ ያነሰ ነው ተብሏል
አሊያንስ ትራንስፖርት ሰርቪስ አክስዮን ማህበር በአዲስ አበባ የግል የከተማ አውቶብስ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምርና ሃያ አምስት አውቶቡሶችን ባለፈው ረቡዕ ወደ አገር ውስጥ እንዳስገባ ተገለፀ፡፡ እያንዳንዳቸው 2 ሚሊዮን ብር ገደማ የተገዙት አውቶቡሶች ባለፈው ታህሣሥ 10 ቀን 2005 ዓ.ም አዲስ አበባ ሲገቡ አቀባበል ተደርጐላቸዋል፡ ሙሉ በሙሉ በአውሮፓ ሞተር የተሰሩትና ቻይና ውስጥ የተገጣጠሙት አውቶቡሶች፤ 100 ሰው የመጫን አቅም እንዳላቸውና ደረጃቸውን የጠበቁ እንደሆኑ አቶ አዲል አብደላ የአሊያንስ ትራንስፖርት ሰርቪስ አክስዮን ማህበር የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሣቢ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ 
አውቶቡሶቹ የቴሌቪዥን ስክሪን ያላቸው፣ የመንገደኛውን ምቾት የሚጠብቁና ለአገራችን አየር በሚስማማ መልኩ የተገጣጠሙ መሆናቸውንም አቶ አዲል ገልፀዋል ፡፡ ድርጅቱ በመጀመሪያው ዙር ሃያ አምስት አውቶቡሶችን ወደ አገር ውስጥ ያስገባ ሲሆን በቀጣዮቹ አራትና አምስት ወራት ሌሎች ሃያ አምስት አውቶቡሶችን ለማስገባት እንዳቀደ ተገልጿል፡፡
አውቶቡሶቹ የሚሰማሩበት መስመርና የትራንስፖርት ዋጋው በቀጣዩ ሣምንት ይፋ የሚደረግ ሲሆን የአገልግሎት ክፍያው የህብረተሰቡን የመክፈል አቅም ያገናዘበና ድርጅቱንም አትራፊ በሚያደርግ መልኩ እንደሚተመን የተናገሩት አቶ አዲል፤ ዋጋው ከሃይገር ባስ ከፍ ያለ፣ ከታክሲ ያነሰ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡
አሊያንስ ትራንስፖርት ሰርቪስ አክስዮን ማህበር ከአመት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚታየውን የትራንስፖርት ችግር የመቅረፍ አላማ አንግቦ የተቋቋመና ታዋቂ ባለሀብቶችና አርቲስቶች የሚገኙበት አክሲዮን ማህበር ነው፡፡
በአዲስ አበባ በተለይ በስራ ሰዓት መግቢያና መውጪያ ላይ ከፍተኛ የትራንስፖርት እጥረት እንዳለ የሚታወቅ ሲሆን በዚህም የተነሳ ነዋሪዎች ከፍተኛ እንግልት እየደረሰባቸው መሆኑ በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

1 comment:

  1. አሁን ላይስ የለበት ሁኔታ ምንድነዉ አክሲዎኑ ዉስጥ ያሉ ሰዎችስ

    ReplyDelete