Search

Wednesday, December 19, 2012

ተቀናቃኞቹ እስራኤልና ኢራን በኤርትራ ወታደራዊ ካምፖች መሥርተዋል›› ስትራትፎር ግሎባል ኢንተለጀንስ

ጋዜጣው ሪፖርተር

ለረዥም ጊዜ የቆየና ሥር የሰደደ የፖለቲካ ፍጥጫ ውስጥ የሚገኙት እስራኤልና ኢራን የቀይ ባህር አካባቢን ለመቆጣጠር የሚያደርጉት ፉክክር ማየሉን፣ ለዚህ ፍላጐታቸውም በኤርትራ ወታደራዊ ካምፖችን ማቋቋማቸውን መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው ወታደራዊ የስለላ ድርጅት ስትራትፎር ግሎባል ኢንተለጀንስ ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት ገለጸ፡፡ የስለላ ተቋሙ ዲፕሎማት ምንጮችን በመጥቀስ እንደገለጸው፣ እስራኤል ወታደራዊ ካምፕዋን በኤርትራ ግዛት በዳህላክ፣ በምፅዋና በአምባ ሳወራ አካባቢዎች መሥርታለች፡፡

እስራኤል በኤርትራ መሬት ላይ ወታደራዊ ካምፖቿን የመሠረተችው በቀይ ባህር አካባቢ ያለውን ማንኛውንም ዓይነት ወታደራዊ እንቅስቃሴ ለመሰለል፣ በተለይም ደግሞ በአካባቢው የኢራንን እንቅስቃሴ ለመከታተል አቅዳ ነው ሲል ሪፖርቱ ይተነትናል፡፡

ኤርትራ ከእስራኤል በተጨማሪ የኢራን ወታደራዊ ካምፖችን ማስጠለሏን የሚጠቅሰው የስትራትፎር ሪፖርት፣ የእስራኤል በዚህ አካባቢ መገኘትም ኢራን በቀይ ባህርና አካባቢው የምታደርገውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ በመብለጥ በአካባቢው ተፅዕኖ መፍጠር የሚችል የጦር ኃይል መገንባት መሆኑን ያስረዳል፡፡

ሮኬቶችንና የተለያዩ ከባድ የጦር መሣሪያዎችን የጫኑ መርከቦች በቀይ ባህር አድርገው ወደ ሱዳን ከዚያም ወደ ግብፅ እንደሚጓዙ፣ በመቀጠልም በየብስ ወደጋዛ እንደሚያመሩ ሪፖርቱ ይጠቅሳል፡፡

ኢራን ወታደራዊ ካምፕዋን በኤርትራ ግዛት ውስጥ መመሥረቷም ባብ ኤል መንዳብ የተባለውን የቀይ ባህር ስትራቴጂካዊ ቦታና ወደ ስዊዝ ካናል የሚወስደውን የውኃ መስመር ለመቆጣጠር ዋነኛው ወታደራዊ ፍላጐቷ መሆኑን ይገልጻል ይላል ሪፖርቱ፡፡

ኤርትራም ለሁለቱ ተቀናቃኝ አገሮች ግዛቷን በመፍቀድ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ጥቅም እንደምታገኝ የስትራፎር ትንተና ያስረዳል፡፡

በተለይም ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ድጋፍና የጦር መሣሪያዎችን እንዲሁም ከኢትዮጵያ በኩል ሊሰነዘርባት ከሚችል ወታደራዊ ጥቃት ራሷን ለመከላከል ይረዳት ዘንድ የአየር ኃይሏን አቅም ለማጐልበት የእስራኤልን ድጋፍ በተለዋጭነት ልትጠይቅ እንደምትችል ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

በተጨማሪም በእስራኤልና በአሜሪካ መካከል ያለውን ወዳጅነት በመጠቀም ከአሜሪካ ጋር ያላትን የተበላሸ ፖለቲካዊ ግንኙነት ማደስ ሌላኛው የኤርትራ ፍላጐት ሊሆን እንደሚችል ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡

እስራኤል በተለያዩ ጊዜያት የሱዳን ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን ከአየር መምታቷን፣ ከወራት በፊት ደግሞ በካርቱም አቅራቢያ የሚገኘውን ዮርሙክ የተባለ የጦር መሣሪያ ማምረቻን ከግዛቷ ባስወነጨፈችው ሮኬት ማውደሟን የሚገልጹ ዘገባዎች መውጣታቸው ይታወሳል፡፡

No comments:

Post a Comment