ሴቶች በፍቅር ውስጥ አጥብቀው የሚፈልጉት ምንድነው?
በጥንዶች መካከል ለሚኖር የተሳካ የፍቅር ግንኙነት የፍላጎት መጣጣም እጅግ አስፈላጊ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ የሰው ልጆች በአጠቃላይ፣ ተመሳሳይ የሚመስል መሰረታዊ ፍላጎቶች ቢኖራቸውም ወንዶችና ሴቶች በየግል ከፍተኛ ቦታ የሚሰጧቸው የተለያዩ የስሜት ፍላጎቶች ይኖሯቸዋል፡፡
በግንኙነት መስክ ውስጥ ከምንጠቀምባቸው ክህሎቶች ሁሉ የመጀመሪያውና ጠቃሚ ነገር፣ የተጓዳኛችንን ጥልቅ ፍላጎት እና ተግባራት አስቀድሞ መረዳት ሲሆን፣ ይህ ማስተዋል አብሮን ያለውን ሰው ጠንቅቀን እንድንረዳ ስለሚያግዘን ችግሮች ከመሰከታቸው በፊት እንድንታደጋቸው ብሎም ከተፈጠሩ በኋላ በንቃት እና በጥበብ መለስ እንድንል ይረዳናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ የሰዎችን መሻት ሳይነግሩን የማወቅ ክህሎትን መማርና መለማመድ፣ አታካችና አድካሚ ቢመስልም ውጤቱ ግን እጅግ አመርቂ እንደሚሆን አያጠያይቅም፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በጥንዶች መካከል ተቀራርቦ ፍላጎቶችን ማውራት፣ ስሜትን መጋራትና ምክንያትን መግለጽ፣ የተሻለ ቅርርቦሽን በመፍጠር በትዳር ላይ መተማመንን ስለሚጨምር መልካም የሚባል ውጤትን ሊያስገኝልን ይችላል፡፡
ብዙውን ጊዜ ሰዎች ጥምረት የሚገቡት በዘርፉ በቂ የሚባል ዝግጅት ሳይኖራቸው እንደሆነ በተደጋጋሚ በዚህ አምድ ላይ የተነሳ ጉዳይ ነው፡፡ ይህም ትዳርን ውስብስብ እና አታካች እያደረገ መጥቷል፡፡ ከስልጣኔ ጋር ተያይዞ የመጣውም የሰው ልጅ ፍላጎት መጨመርና በትንሽ ነገር ያለመርካት አባዜ፣ በትዳር ውስጥ ተስፋ መቁረጥ የራሱን የሆነ ሚና ይጫወታል፡፡
በአንድ ወቅት ኖራ ሃይደን የተባለች የማህበራዊ ህይወት ተመራማሪ በመጽሐፏ እንዳለችው፣ አብዛኛው ወንዶች ስለ ሴቶች ያላቸው አተያይ እጅግ አስደንጋጭ ነበር፡፡ በወንዶች ዓይን ሴቶች ማለት፣ በዚህች ምድር ላይ ካሉ ነገሮች ሁሉ በላቀ ደረጃ እጅግ ውስብስብና፣ ፍላጎታቸው የማይታወቅ በቀላሉ የማይረኩ ፍጡሮች እንደሆኑ ይገልፃሉ፡፡
በዚሁ ጥናት ላይ የሴትን ልጅ ፍላጎት ከመረዳትና፣ ሴትን ልጅ ደስተኛ ከማድረግ ይልቅ (ኑዩክለር ፊዚክስ ማጥናት እንደሚቀል ገልጧል)
ይህ በእውነቱ ከእውነታው ጋር እጅግ የሚጣረስና ለሴቶች እጅግ አስደንጋጭ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ እሳቤ የሚመነጨው ሁላችንም በራሳችን ግለኛ ዓለም ውስጥ ተከልለን የራሳችንን ተፈጥሮና ፍላጎት ብቻ ስለምናዳምጥና የሌሎችን ማንነት ለማወቅና ተጣጥሞ ለመኖር ምንም አይነት ጥረት ስለማናደርግ ይመስለኛል፡፡
በተለያየ ጊዜ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች፣ ስለወንዶችና ሴቶች ረቂቅ ባህሪያትና ፍላጎት ለማወቅ በርካታ ጥናቶችን አካሂደዋል፡፡ ከእነዚህ ጥናቶች የተውጣጣውን መደምደሚያ መሰረት በማድረግ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሴቶች የሚስማሙበትንና፣ ሴቶች ከትዳር አጋራቸው ወይም ፍቅረኛቸው አጥብቀው የሚሹትን 6 ነጥቦችን ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ላካፍላችሁ ወደድኩ፡፡
የሴትን ልጅ ልብ ለመማረክ እና ቀጣይነት ያለው ግንኙነት ለመመስረት የሚረዱ 6 ነጥቦች
(Caring) እንክብካቤ
1. በጥናቱ ውስጥ ከተካተቱ አብዛኛዎቹ ሴቶች በፍቅር ለሚንከባከብ ወንድ በቀላሉ እንደሚሸነፉ ገልፀዋል፡፡ ይህም የሚሆነው ሴቶች በተፈጥሮ ካላቸው የእንስትነት ባህሪ የተነሳ ከወንዶች ስሜት እና ፍቅርን ብቻ ሳይሀን፣ ከለላን፣ አለኝታነትን እና እክብካቤን አጥብቀው እንደሚሹ ተናግረዋል፡፡ ይሄም ምኞት እና ደህንነት እንዲሰማው ስለሚያደርግ ህይወትን ለቀቅ አድርገው በመመልከት የበለጠ ደስተኛ ያደርጋቸዋል፡፡
2.
ትኩረት
ይሄንን ፍላጎት በሁለት ከፍለን ልናየው እንችላለን፡፡
2.1 መደመጥ
Joeu Barton የተባለ የስርዓተ ፆታ ተመራማሪ በጥናቱ ላይ እንዳሰፈረው፣ ሴቶች በቀን ውስጥ በአማካኝ 20,000 ቃላቶችን ሲጠቀሙ፣ በተቃራኒው ወንዶች ደግሞ 7,000 ቃላትን በመጠቀም ሀሳባቸውን ያስረዳሉ፡፡ ይህም በግልፅ እንደሚያስረዳን አንደኛ ሴቶች ለቋንቋ እና ለንግግር ፈጣን የሆነ አዕምሮ እንዳላቸው ሲሆን፣ ሌላው እና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ፣ ሴቶች በንግግር ራሳቸውን በመግለፅ የበለጠ ነፃነት እንደሚሰማቸው ሲሆን ችግር በገጠማቸውና በጨነቃቸውም ጊዜ በማውራት ብቻ ያለ ምንም ተጨማሪ ምክርና መፍትሄ የተሻለ እፎይታና እረፍት እንደሚሰማቸው ሲሆን፣ በዚህም ጊዜ ንግግራቸውን በትኩረት ለሚያዳምጣቸው ወንድ የተለየ ፍቅርና አክብሮት ይኖራቸዋል፡፡
2.2 አንዲሰት ሴት አብሯት ካለ ወንድ ከፍቅርና እንክብካቤ ባሻገር አትኩሮ ትሻለች
በርካታ የህይወት ተሞክሮዎች እንደሚያመለክቱት፣ ሰዎች በተሰበሰቡበት ግብዣ ላይ አንድ ወንድ ፍቅረኛውን ወይም የትዳር አጋሩን ከሰዎች ጋር በሚኖረው ጨዋታ እጇን በማሻሸት ወይም በመሳም፣ አብሮነቱን ቢያረጋግጥላት በቀላሉ ልቧን በፍቅር በማቅለጥ የጥሩ ስሜት ባለቤት እንድትሆን እንደሚረዳ ይታመናል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ወንዶች በግንኙነት ውስጥ የሚመለከቱት፣ ትልቁን ምስል ብቻ በመሆኑ አብሮነት በራሱ በቂ ነው ብለው ሊያስቡ ይችላሉ፡፡ ሴቶች ደግሞ ባላቸው የተለያየ አፈጣጠር ዝርዝር ነገሮች ላይ ትኩረት ስለሚያደርጉ እያንዳንዱን እንቅስቃሴና ፍሰት ይከታተላሉ፡፡ በመሆኑም ወንዶች ፍቅረኛቸው ወይም የትዳር አጋራቸውን ከመነፈጠሯም ረስተው ለረጅም ሰዓት ከሶስተኛ ወገን ጋር ጨዋታ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ፡፡ ይህ በሴቶች አዕምሮ ውስጥ የመተውና አትኩሮት የማጣት ስሜትን ሊያጭር ስለሚችል ወንዶች ትኩረት ሊያደርጉበት ይገባል፡፡ ይሄንን በጣም ቀላል ግን ከፍተኛ ተፅዕኖ ሊፈጥር የሚችል እውነታ በመረዳት፣ በሄዳችሁበት ሁሉ ለሴቶቻችሁ አብሮነት ትኩረትና ዕውቅናን በመስጠት፣ ስሜታቸውን ከመጉዳት ብትታደጉ በምላሹ ፍቅር እና አድናቆትን ትቀበላላችሁ፡፡
እዚህ ጋ ልብ ልንለው የሚገባው እውነታ፣ ይህ ዓለም መስጠትንና መቀበልን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ የሰውን ስሜት ጎድቶ መልካም የስሜት ምላሽ መጠበቅ የዋህነት ስለሆነ፣ የምንፈልገውን ለማግኘት የሚፈለገውን መስጠት ግድ ይለናል፡፡
3. (Security) ጥበቃ
ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው፣ የወንድ ልጅ ከለላ እና መጋ መሆን፣ አሁንም ድረስ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያለው እውነታ ነው፡፡ በዚህ በሰለጠነው እና የሴቶች እኩልነት በተረጋገጠበት 21ኛው ክፍለ ዘመን እንኳን፣ ሴት ልጅ በግሏ ገቢ በማስገኘት ሀብት ማካበት ብትጀምርም፣ የወንድ ልጅ ግብአት አቅራቢ እና ጠባቂ መሆን የሴትን ልጅ ስሜት ለማረጋጋት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህም በዘለለ ወንድ ልጅ ለሴት ከተለያየ አደጋ ጠባቂ ሆኖ መገኘቱ፣ እምነቷን የበለጠ ስለሚያጠነክረው ፍቅሯ እየጎለበተ ይሄዳል፡፡
4. Blind Loyalty (ፍፁም የሆነ ተአማኒነት)
በአብዛኛው አንዲት ሴት የፍቅር ግንኙነት ውስጥ ስትሆን ወይም በወንድ ስትፈቀር ራሷን የተለየች ፍጡር አድርጋ እንድታይ ትሆናለች፡፡ ይህም ምን አልባት ከሴቶች ተፈጥሮ በተጨማሪ ወንዶች በፍቅር መብረቅ በተመቱ ጊዜ ያፈቀሯትን ሴት የግላቸው ለማድረግ የሚጠቀሙበት ገደብ የለሽ ሙገሳና ማሞካሸት፣ ሴቶች ለራሳቸው ያላቸውን አመለካከት በማዛባት፣ ውጫዊ መስህብን እንደ ብቸኛ የማንነታቸው መለኪያ አድርገው እንዲወስዱት ሳያስገድዳቸው አልቀረም፡፡
በመሆኑም በግንኙነት ውስጥ አንዲት ሴት የራሷን የመስህብ ደረጃ ጠንቅቃ ብታውቅም ባፈቀራት ወንድ እይታ ስትፈረጅ ‹‹ሁሉን ያስናቀች ቆንጆና ፀባየ ሰናይ መሆኗን እንዲነገራት ትፈልጋለች›› በማንኛውም አጋጣሚ የእሷ ወንድ የሌላዋን ቆንጆ አለባበስ ወይም አቋም ቢያደንቅ እሷን የወሰደባት ያህል ስለሚሰማት መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም የሰውን ቆንጆ በመቃረም፣ የትዳር አጋራችንን ስሜት ከምንጎዳ፣ ያገባናትን ሴት በትዳር አብረን እንድንኖር ውሳኔ ላይ ያደረሰንን መልካም ሰብዕና፣ ውበት፣ ወይም ተግባር በማስታወስ ከልብ የመነጨ አድናቆታችንን እና ሙገሳችንን መቸርን ብንለማመድ፣ ለትዳራችን ዕድሜ ማራዘሚያነት እንደሚጠቅም ጥናቶች እና ተሞክሮዎች ያመለክታሉ፡፡
5. Understanding (መረዳት)
በርካታ ሴቶች ከተጓዳኛቸው አጥብቀው የሚፈልጉት ተጨማሪው ነገር፣ የትዳር አጋራቸው የእነሱን ሚና እና በቤት ውስጥ ያላቸውን አስተዋፅ እንዲረዳ እና ዕውቅና እንዲሰጥ ነው፡፡ አንዳንድ ወንዶች ሴት ልጅ በቤት ውስጥ የምታከናውናቸውን ረቂቅና እጅግ ወሳኝ ተግባራት ባለማወቅ ዕውቅናን ሲነፍጉ ይስተዋላሉ፡፡ የሴት ልጅ ተፈጥሮ ማለትም በሴትነት የምታልፋቸውን ከባባድ ደረጃዎች፣ እርግዝና፣ ወሊድ፣ ማጥባት እና ልጅን መንከባከብ በምድራችን ካለ ነገር ሁሉ እጅግ ውድ፣ ፈታኝ እና ዋጋ ሊተመንለት የማይችል መሆኑን በመረዳት፣ ሴት ሆነው ያንን መክፈል እንኳን ባይችሉ፣ ክብደቱን በመረዳት እና ርህራሄ በማሳየት ሊያዝኑላቸው፣ ሊንከባከቧቸው እና ሊደግፏቸው ይገባል፡፡ ይሄም በሴት ልጅ ልቦና ውስጥ እስከ መጨረሻው ለመቀመጥ ጥርጊያ መንገድ ይሆናል፡፡
6. Sex (ወሲብ)
በተጣማሪዎች መካከል ፍቅር ሰምሮ ኑሮ እንዲደረጅ፣ በሐሳብ እና ፍላጎት መጣጣም ተቀዳሚው መሆኑ የማያጠያይቅ ሀቅ ነው፡፡ መከባበሩ፣ መፈቃቀሩና የሐሳብ መጣጣሙ እንደተጠበቀ ሆኖ በወሲብ አለመጣጣም ባለትዳሮች ከትዳራቸው ውጪ ሌላ ሰው መጎብኘታቸው የተለመደ ተግባር እየሆነ መጥቷል፡፡
ብዙውን ጊዜ ተጣማሪዎች፣ የሐሳብ አለመጣጣምን አቻችለውና ተቻችለው ኑሮን ሲገፉ ይስተዋላል፡፡ በአሁኑ ዘመን እየተስተዋለ የመጣው እውነታ እንደሚያመለክተን ግን በወሲብ አለመጣጣምን ማስታመም ስለሚያቅታቸው ወይም ከሌላ ጋ ሲማግጡ ወይም ከነጭራሹ ትዳርን ሲያፈርሱ ይታያሉ፡፡
በአብዛኛው በርካታ ወሲብ ነክ ፅሑፎችና ጥናቶች አንድን ወንድ እንዴት ለወሲብ ማነሳሳት እንዳለብን እና እንዴት እርካታ ላይ እንዲደርስ መርዳት እንዳለብን የሚገልፁ ናቸው፡፡ ይህም የሚያሳየው የሴት ልጅ ስሜት ይሄ ነው የሚባል አትኩሮት ከማህበረሰቡ ጭምር እንዳልተቸገረው ነው፡፡
Nora Hayden (How to satisfy a women every time) በተሰኘው መጽሐፏ ላይ እንደገለፀችው 80% የሚሆኑት ሴቶች፣ እውነተኛ እርካታ ላይ እንደሚደርሱ ሆኖም የትዳር አጋራቸውን ለማስደሰት ሲሉ ብቻ እርካታ ላይ እንደደረሱ እንደሚያስመስሉ ይናገራሉ፡፡ ይህም የሚሆነው ወንዶች በወሲብ ጊዜ የሴትን ልጅ ፍላጎት እና የስሜት ምስጢር መረዳት ስለሚያቅታቸው እነሱ በሚረኩበት መንገድ ይረካሉ ብለው በማሰብ ዘልማዳዊ የሆነውን ግንኙነት ያደርጋሉ፡፡ ሆኖም ፈጣሪ ወሲብን በትዳር መካከል እንድትደሰትበትና ትውልድን እንድናስቀጥልበት የሰጠን ታላቅ ፀጋ በመሆኑ፣ የሴትም ልጅ ስሜት መጠበቅ እና በባሏ መደሰት እንዳለባት በመረዳት በግልፅ በመወያየትም ሆነ በዘርፉ የተፃፉ ጽሑፎችን በማንበብ፣ ደስታውን የጋራ የማድረግ የወንዶች ተቀዳሚ ኃላፊነት ነው፡፡
በመጨረሻ ማንሳት የምፈልገው ነጥብ፣ ብዙዎች በትዳር ላይ በግንኙነት ዙሪያ በመርህ ደረጃ የሚነሱ ጠቃሚ ምክሮችን ማንበብ ፋይዳ ቢ መሆኑን ሲናገሩ ይታያል፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያትነት የሚያነሱት መከራከሪያ የፀሐፊዎቹ ወይም አነበብን የሚሉ ሰዎችን ግለ ህይወት በናሙናነት በማንሳት፣ በትዳር ህይወታቸው ስኬታማ አለመሆናቸውን ነው፡፡ እዚህ ጋ መረዳት ያለብን ቁም ነገር፣ ችግሩ ያለው ከዕውቀቱ ወይም ከንባቡ ሳይሆን ያወቅነውን እና የሰማነውን በልቦናችን አኑረን መተግበር ስለሚሳነን መሆኑን ነው፡፡ በመሆኑም ተፈጥሮ የለገሰችን ሰብዕና፣ በህይወት ተሞክሮ እና ዕውቀት በማዳበር፣ ያካበትነውን ዕውቀት በመተግበር እና ለውጥ በማምጣት ትዳራችን በግምት ሳይሆን፣ በጥበብ የምንመራትን ልቦና ይስጠን፡፡
ሴት ልጅ ምን መስማት አትሻም!
ሴቶች ስለ ሌላ ሴት ወይም ስለ ቀድሞ ጓደኛህ ስታደንቅ መስማት አትፈልግም፡፡ ከሌላ ሴት ጋር እንድታወዳድራትም እንዲሁ፡፡ ስለ ሰውነት ቅርጽና ውበቷ አድናቆት እንጂ ነቀፌታ ቅር ያሰኛታል፡፡ በድንገት ተሳስተህ የሌላ ሴት ስም ማንሳትም አይኖርብህም፡፡ በሌላ መንገድ ያስጠረጥርሃልና፡፡ ከአሁን ቀደም በነበረህ የሴት ልጅ ትውውቅ ውስጥ አላግባ ያደረካቸውን ነገሮች ማውራትህ ከባድ ግምት ውስጥ ይጥልሃልና በተቻለ መጠን ከኋላ ፈቅር ታሪክህ ውስጥ ጥሩ ጥሩውን እንጂ የሚያስተችህን ለመርሳት ወይም ላለማንሳት ጥረት አድርግ፡፡ በሌላዋ ላይ ይህን ያደረገ በእኔም ላይ ማድረጉ አይቀርም የሚል እምነት ይኖራታልና፡፡ ሴቶች ስለ አንተ ማወቅ የሚፈልጉትን ሲጠይቁህ እውነቱን መናገሩን ብቻ ነው የሚያዋጣው፡፡ ብዙ ጊዜ ሴቶች ለማወቅ በሚመስል መልኩ ይጠይቃሉ እንጂ የሚጠይቁትን ነገር ቀድሞውኑ ያውቁታልና አትዋሽ!
በተቻለ መጠን ከአሁን ቀደም ከነበረህ የፍቅር ትስስር እንዴት እንደተለያየህ ምክንያትህን አሳማኝነት ያለውና ከአንተ በኩል ከፍተኛ ጥረት ማድረግህ ላይ ያነጣጠረ ይሁን እንጂ ኃላፊነትህን ስላለመወጣትህ የሚያንፀባርቁ ምክንያቶችን ወይም ደግሞ ቀድሞውኑ ለመለያየት የማያበቁ ምክንያቶችህን ሴቶች መስማት አይፈልጉም!! ቢሰሙም ትዝብት ውስጥ ይጥሉሃልና ጠንቀቅ በል!!
source: www.zehabesha.com