Monday, May 11, 2015

በወንዶች ጸጉር ቤት ማማር ብቻ ሳይሆን በሽታ መሸመትም አለ!


ማሽኖችን በአልኮል መጥረግና በላይተር ማቃጠል በሽታ ከማስተላለፍ አያድናቸውም ከወራት በፊት በራስ ቅሉ መሀል ላይ የወጣችው ጭርት መሳይ ነገር መላ ጭንቅላቱንና አንገቱን ለማዳረስ የፈጀባት ጊዜ ጥቂት ሳምንታት ብቻ ነበር፡፡ ከራስ ቅሉ እየተቀረፈ በብናኝ መልክ በኮቱና ሸሚዙ ላይ በሚራገፈው ነገር መሳቀቁ ሲበዛበትና ችግሩ ሲበረታበት መፍትሄ ፍለጋ የቆዳ ሐኪሞች
ወዳሉበት አለርት ሆስፒታል ሄደ፡፡ ምርመራ ያደረገለት ሃኪምም በፈንገስና በባክቴሪያ ሳቢያ የሚከሰት “ኢንዳፎሊግላይት” የተባለ የቆዳ በሽታ እንደሆነ ነገረው፡፡ ተከታታይነት ያለው ህክምና
ማድረግ እንዳለበትና በሽታው ወደ ሌሎች ሰዎች እንዳይተላለፍ መጠንቀቅ እንደሚገባው አሳስበው፡፡ በሽታው በአብዛኛው በፀጉር ቤት ማሽኖችና ፎጣዎች ከሰው ወደ ሰው እንደሚተላለፍም ነገረው፡፡ ነገሩ ግን ለማስረሻ ፈፅሞ አልተዋጠለትም፡፡ ላለፉት አራት አመታት አንድ የፀጉር አስተካካይን በደንበኝነት ይዞ ነው የቆየው፡፡ ጸጉሩንም ሆነ ፂሙን ለመስተካከል ወደ ፀጉር ቤቱ በሄደ ጊዜ አስተካካዩ ማሽኑን በአልኮል አፅድቶና በላይተር አቃጥሎ ነው የሚያስተካክለው፡፡ ታዲያ ባክቴሪያው እንዴት ወደ እሱ ሊተላለፍ ይችላል? ሌላ መንገድ መኖር አለበት … ብሎ ነበር የገመተው፡፡ አሁን ለወራት ሲያሳቅቀው ከቆየው ችግር ለመላቀቅ የሚያስችለውን ህክምና በአለርት ሆስፒታል ጀምሮ ጥሩ መሻሻሎችን እያየ መሆኑን ገልፆልኛል፡፡ በዚህ ወጣት ላይ የደረሰው አይነት ችግር በበርካታ ኢትዮጵያውያን ወንዶች የፀጉር ቤት
ተጠቃሚዎች ላይ ሊደርስ ይችላል፡፡ የዚህን ወጣት ገጠመኝ መነሻ አድርገን በከተማችን የተለያዩ አካባቢዎች ወደሚገኙ የወንዶች ፀጉር ቤቶች ተዘዋውረን የሚጠቀሙባቸውን ማሽኖችና የንፅህና አጠባበቃቸውን ለማየት ሞክረናል፡፡ በመሳለሚያ፣ በመርካቶ፣ በፒያሳ፣ በሰሜን ሆቴል፣ አዲሱ ገበያ፣ ጦር ኃይሎችና ሜክሲኮ፣ ስድስት ኪሎና ሽሮሜዳ ተዘዋውረን የተመለከትናቸው አንዳንድ የወንዶች ጸጉር ቤቶች የማሽኖቻቸውን ንፅህና በስቴራላይዚንግ መሳሪያ እንደሚጠብቁ የሚገልፁ ታወቂያዎችን ቢለጥፉም የማፅጃ መሳሪያው ግን የላቸውም። አሊያም ደግሞ አገልግሎት
መስጠት አቁሟል። ደንበኞቻቸውን ለማጭበርበር ምንም አይነት አገልግሎት በማይሰጡ የስቴራላይዘር መሳሪያ ውስጥ የፀጉር መቁረጫ ማሽኖቹን ለደቂቃዎች ይከቱና ያወጧቸዋል፡፡ ንዳንዶቹ ደግሞ ማሽኑን በአልኮል ጠረግ ጠረግ ያደርጉና በላይተር እሳት ሞቅ ሞቅ ያደርጉታል፡፡
የጸጉር ማበጠሪያዎች፣ የፊትና የራስ ቅል የሚጠረግባቸው ቁርጥራጭ ፎጣዎችና በአንገት ዙሪያ የሚታሰሩት ጨርቆች ግን ንፅህናቸው በምን መልኩ እንደሚጠበቅና ምን ያህል ለጤና አስተማማኝ
እንደሆኑ ጠያቂም ምላሽ ሰጪም የለም፡፡
ጸጉር አስተካካዩ ሥራውን ካጠናቀቀ በኋላ በረዳቱ በሚቀርብለት ውሃ ውስጥ እየነከረ የደንበኛውን
የራስ ቅልና ፊት የሚያፀዳበት ቁራጭ ፎጣን ንፅህና ጠይቀን የምናውቅ ስንቶቻችን እንሆን? የፀጉር ማስተካከያ ማሽኑ ንፅህና የሚያሳስበንን ያህል ስለ እነዚህ ቁርጥራጭ ፎጣዎችና ስለ ማበጠሪያዎቹ አስበንና ተጨንቀንስ እናውቅ ይሆን? ባልታከሙ የፀጉር ቤት ማሽኖችና መሳሪያዎች አማካኝነት የሚከሰቱ የጤና ችግሮች አሳሳቢ ሲሆኑ
ዩኒቨርሲቲ ህክምና ፋክሊቲ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የቆዳና አባላዘር በሽታዎች ስፔሻሊስት ዶክተር
አብርሃም ተመስገን ይህንን ጉዳይ አስመልክተው ሲናገሩ፤ “የፀጉር ቤት ማሽኖች ለዚህ በተዘጋጀ የማፅጃ መሳሪያና በፈሳሽ ኬሚካል ማፅጃዎች ካልፀዱና በበቂ የሙቀት ኃይል እንዲቃጠሉ ካልተደረገ በስተቀር ኤችአይቪ/ ኤድስን ጨምሮ ሌሎች እንደ ኢነካቶይቭና ኢንዳፎሊግላይት የመሳሰሉ አደገኛ በሽታዎችን ከሰው ወደ ሰው በቀላሉ ሊያስተላልፉ ይችላሉ፡፡ የፀጉር ቤት ማሽኖችን ለማፅዳት በአብዛኛው በጥቅም ላይ የሚውለው አልኮል፣ በሽታ አምጪ የሆኑ ባክቴሪያዎችን ከማሽኑ ላይ በማስወገድ ረገድ የሚኖረው አስተዋፅኦ እጅግ ውስን ነው፡፡ ለፅዳት
የሚውለው አልኮል ሁለት አይነት ነው፡፡ ኢታኖል የተባለው የአልኮል አይነት 70% የሚደርስ ጀርሞችን የመግደል አቅም ሲኖረው ይህ ተግባራዊ የሚሆነው ግን  ማሽኑ በአልኮሉ ከተጠረገ በኋላ ለሁለት ደቂቃ ያህል ጠንከር ያለ ኃይል ባለው ሙቀት ውስጥ እንዲቆይ ሲደረግ ብቻ ነው፡፡ ሌላው
የአልኮል አይነት አይቶፕሮፕላን የሚባለው ሲሆን ይህ የአልኮል አይነት ከኢታኖል የተሻለ ጀርሞችን
የማጥፋት አቅም ያለው ነው፡፡ ይሁን እንጂ አስተማማኝ የሚሆነው መሳሪያው በኃይለኛ የሙቀት ኃይል ውስጥ መቃጠል ሲችል ብቻ ነው፡፡ ከእነዚህ ሌላ ግሎሮግዜኖል፣ ፓበዲን፣ ሃፖክሎራትና ቤንዞልኮሊሎራይድ የተባሉት ኬሚካሎች ጀርሞችንና ባክቴሪያዎችን አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ ለማስወገድ የሚችሉ ናቸው፡፡ የፀጉር ቤት ማሽኖች ማበጠሪያዎችና ፎጣዎች በእነዚህ ኬሚካሎች በአግባቡ ሊፀዱና ከባክቴሪያ ነፃ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ይህንን ማድረግ በማይቻልባቸው ሁኔታዎች ሰዎች በራሳቸው ማበጠሪያና ፎጣ እንዲጠቀሙ፣ አሊያም ከአገልግሎት በኋላ ማስወገድ በሚቻል ነገር እንዲጠቀሙ ማድረግ ተገቢ ነው” ብለዋል የህክምና ባለሙያው፡፡ በዚህ መንገድ ንፅህናቸው ባልተጠበቁ ፎጣዎችና መሳሪዎች መጠቀሙ ለከፋ የጤና ጉዳትና ኤችአይቪ ኤድስን ጨምሮ እንደ ኤፒታይተስ ቢ ላሉ እጅግ አደገኛ ለሆኑ ተላላፊ በሽታዎች
ሊያጋልጥ ይችላልና ጥንቃቄ ማድረጉ ተገቢ መሆኑን ዶክተር አብርሃም አስገንዝበዋል፡፡ እናም
በወንዶች ጸጉር ቤቶች ማማር ብቻ ሳይሆን በሽታ መሸመትም እንዳለ አውቆ ጥንቃቄ መውሰድ ተገቢ ነው እላለሁ፡፡ ፀጉር ቤቶችም ለደንበኞቻቸው ጤንነት ለይምሰል ሳይሆን ከልባቸው አስበው ተገቢውን የንፅህና አጠባበቅ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ በኃላፊነት የሚያስጠይቃቸው መሆኑንም ማወቅ አለባቸው፡፡  

No comments:

Post a Comment