Friday, April 3, 2015

በየመን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ በጦር መሳሪያ ጥቃት ተፈፀመበት

በየመን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ በጦር መሳሪያ ጥቃት ተፈፀመበት 


አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2007 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በየመን ሰንዓ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ ላይ ለትናንት አጥቢያ ላይ በጦር መሳሪያ ጥቃት እንደተፈጸመበት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴድሮስ እንዳስታወቁት በጦር መሳሪያ ጥቃቱ ጉዳት የደረሰበት ኢትዮጵያዊ የለም።
አምባሳደሩም ሆኑ ሌሎች ዲፕሎማቶች በደህና ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ነው ያስታወቁት።
ኢምባሲ በየመን ያላቸው አብዛኛዎቹ አገራት ኢምባሲዎቻቸውን ከዘጉ ሳምንታት ተቆጥረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴድሮስ “ከዜጐቻችን በፊት አንወጣም ብለው ኢትዮጵያውያንን ለመርዳት ጥረት እያደረጉ ላሉ ዲፕሎማቶችእና የአስተዳደር ሰራተኞች ምስጋናዬን አቀርባለሁ” ብለዋል።
በሌላ ዜና ከየመን ተመላሽ የሆኑ የመጀመሪያዎቹ 30 ኢትዮጵያውያን ጅቡቲ ደርሰዋል።
እስካሁን ወደ አገራቸው ለመመለስ ከ2 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ተመዝግበዋል።
የተመዘገቡትን ዜጎች በጥቂት ቀናት ውስጥ ወደ አገራቸው ለመመለስም መንግስት የተቻለውን ሁሉ በማድረግ ላይ መሆኑን ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያስታወቀው።
በየመን የሆቲ አማፂያን እና የአልቃይዳ  ክንፍ ሰፊ ግዛት እየተቆጣጠሩ በመምጣት የአገሪቱ መዲና ሰነዓን  ይዘዋል።
በአገሪቱ መንግስት ደጋፊዎች እና በአማፂያኑ መካከል የሚደረገው ግጭት የቀጠለ ሲሆን፥ በተለይም በባህር ዳርቻዋ ከተማ ኤደን ጦርነቱ ተባብሷል ነው የተባለው።
በህጋዊ መንገድ የተቀመጠውን የአገሪቱን መንግስት ወደ መንበሩ ለመመለስም በሳዑዲ አረቢያ መሪነት የአከባቢው አገራት ተጣምረው የዓየር ጥቃት በመፈፀም ላይ ይገኛሉ።

No comments:

Post a Comment