Sunday, April 19, 2015

አይኤስ በሊቢያ በሚገኙ ስደተኞች ላይ ፈፅሜዋለሁ ያለውን ግድያ የኢትዮጵያ መንግስት አወገዘ


አይኤስ የተባለው አለምዓቀፍ አሸባሪ ቡድን በሊቢያ በሚኖሩ ስደተኞች ላይ ፈፅሜያዋለሁ በሚል በቪዲዮ ያሰራጨውን ዘግናኝ የግድያ ተግባር የኢትዮጵያ መንግስት እንደሚያወግዘው አስታወቀ፡፡
የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅሀፈት ቤት ሃላፊ ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን እንደገለፁት አሸባሪዎች በንፁሃን ዜጎች ላይ የሚፈፀሙትን ይህን መሰል የጭካኔ ተግባር ኢትዮጵያ በፅኑ የምታወግዘውን ያህል ቀደም ሲል ጀምሮ ዜጎቿንም ከሽብርና አሸባሪዎች ጥቃት ለመታደግ የሚያስችላትን አስፈላጊውን ዝግጁነት ተግባራዊ በማድረግ የአገሪቱን ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ልማት በአስተማማኝ ማረጋገጥ ችላለች ፡፡

በዛሬው ዕለት ሚያዚያ 11 ቀን 2007 የተለያዩ አለም ዓቀፍ ሚዲያዎች ባሰራጩት ዘገባ አይኤስ የተባለው አሸባሪ ቡድን ግድያ የፈፀመባቸው ስደተኞች ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ ቢገልፁም በግብፅ ካይሮ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ግን ስደተኞቹ ኢትዮጵያውያን ስለመሆናቸው ማረጋገጫ እንዳልሰጠም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
አሸባሪው ቡድኑ ለህልፈት የዳረጋቸው ዜጎች ኢትዮጵያውያን ቢሆኑም ባይሆኑም መንግስት በንፁሃን ላይ የሚፈፀም ይህን መሰል አፀያፊና ዘግናኝ የሽብር ድርጊት አጥብቆ ይኮንናል ብለዋል፡፡

በሊቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው መመለስ የሚፈልጉ ከሆነም መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በመሆኑም ከሊቢያ ወደ ሀገር ተመላሽ ፈላጊ ስደተኞች በግብፅ ካይሮ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር ግኑኝነት እንዲፈጥሩም የኢትዮጵያ መንግስት አሳስቧል ሲል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅሀፈት ቤት በላከው መግለጫ አመልክቷል፡፡
source FBC

No comments:

Post a Comment