Saturday, March 28, 2015

ኢትዮጵያዊቷ የISIS ሙሽራ እና “ጽንፈኛ” ሆነው የተገኙት አባቷ

ኢትዮጵያዊቷ የISIS ሙሽራ እና “ጽንፈኛ” ሆነው የተገኙት አባቷ

አስደንጋጭ ዜና ነው። ራሱን የእስልምና ግዛት ISIS ብሎ የሚጠራው አክራሪ እና ጭራቂዊ ቡድንን ለመቀላቀል ከሁለት ጓደኞቿ ጋ ከለንደን ወደ ሶሪያ የሄደችው የ15 ዓመቷ አሚራ አባት የሆኑት አቶ አባስ ሁሴን Innocence of Muslims የሚለው ፊልም እስልምና እምነትን አዋርዷል በማለት በለንደን አሜሪካ ኤምባሲ ፊት-ለ-ፊት በተደረገው ሰልፍ ላይ አሜሪካ ትቃጠል፣ ሙስሊም ክሩሴድን ያጠፋል አሜሪካንና እንግሊዝን ጨምሮ…. የሚሉ መፈክሮች ጀርባ በስሜት መፈክር ሲያስተጋቡ የሚታዩበት ቪዲዮ ይፋ ሆኗል።
መፈክር ብቻ ሳይሆን የአሜሪካንና እስራኤል ባንዲራ ሲቃጠል አቶ አባስ አጃቢ ናቸው።
ልጃቸው ወደ ሶርያ ለመግባት በቱርክ በኩል ስታቋርጥ በካሜራ እይታ ውስጥ ከገባችና ሁኔታው በእንግሊዝ መንግስት በገሊ ከተነገረ በኋላ አቶ አባስ የእንግሊዝን ፖሊስ ተጠያቂ ማድረጋቸው ይታወሳል። በወቅቱ በብሪታኒያ ፖሊስ ማዕከል ስኮትላንድ ያርድ ቃለምልልስ ሲሰጡ ልጃቸው ስለአክራሪነት ፈጽሞ የምታውቅበት መንገድ ይፈጠራል ብለው እንደማያምኑ ሳግ እየተናነቃቸው ሲናገሩ ሰምተናል።
ነገር ግን አሁን ቀስቱ ወድሳቸው ዞሯል። ከ3 ዓመታት (2012) በፊት የዛሬን ጦስ ሳያስቡት እንግሊዝን ባስበረገገው የጽንፈኞች ሰልፍ ላይ ተዋናይ መሆናቸው በቀላሉ የማይታይ፣ ለልጃቸው የISIS ነፍሰ ገዳይ ለመሞሸር ድንበር ማቋረጧ በቀጥታ ተጠያቂ መሆናቸው አይቀሬ ነው። አሜሪካንም ሆነች እንግሊዝ ጉዳዩን በቀላሉ አያዩትም። ለዚህ ምክንያቴ አቶ አባስ:–
1. የአሜሪካኑን 911 እና የእንግሊዙን 7 July 2005 የሽብርተኞች ጥቃትን በአደባባይ የደገፈው ብሪታኒያዊው አካራሪ፣ አክቲቪስትና የሙስሊም ማህበረሰብ ጠበቃዎች ሊቀመንበር አንጀም ቾዳሪ የመራው ሰልፍ ላይ መገኘታቸው
2. በዛ ሰልፍ ላይ ከታደሙት መካከል Michael Adebowale የተባለ ወጣት ከዚያ የጽንፈኞች ሰልፍ አንድ ዓመት በኋላ የብሪታኒያን ወታደር Lee Rigbyን በደቡብ ምሥራቅ ለንደን በጠራራ ፀሐይ በመኪና ገጭቶ በስለት ወጋግቶ የገደለ መሆኑ
ልጃቸውን ከማጣታቸው ጋር ተደማምሮ የአቶ አባስን ቀጣይ ሕይወት መሪር ያደርገዋል።
ሆኖም ሰው የዘራውን ማጨዱ አይቀርም ቢባልም በልጃቸው ማንነት ላይ የነበራቸውን ሚና እርግጠኛ ሆኖ መናገር አዳጋች ነው።
ሆኔታው ግን ለጅምላ ፈራጆች ትልቅ ሲሳይ እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ። የኢትዮጵያ ሙስሊሞች እንቅስቃሴን በጎሪጥ ለሚያዩ ሰዎች፣ ህወሓት የሚሰራው ፕሮፓጋንዳ ለኀይማኖታቸው፣ ለብሔራቸው… በሚመች መልኩ በትሪ ጠረጴዛቸው ላይ ቁጭ ሲቀርብ ተስገብግበው ለሚሻሙ ሰዎች ለቁንጽል መረጃቸውና ድምዳሜያቸው ግዙፍ ርዕስ አግኝተዋል።
ድምጻችን ይሰማ በዚህ ውዥንብር ሳይደናገር ላለፉት 3 ዓመታት ያሳየንን ሰላማዊ እና ስልጡን ተቃውሞ እንደሚቀጥል ቅንጣት ታህል ጥርጥር የለኝም።
Kassa Hun Yilma

posted by Aseged Tamene

 


No comments:

Post a Comment