Wednesday, June 5, 2013

ለቤት ምዝገባ የሚያስፈልገውን የባንክ ሂሳብ ለመክፈት የሚስተዋለውን ሰልፍ ለማቅለል መፍትሄ ማዘጋጀቱን ባንኩ ገለፀ


ኢትዮዽያ ንግድ ባንክ በ10/90 እና በ20/80 የመኖሪያ ቤት መርሃ ግብር መሰረት  ለመመዝገብ የሚያስፈልገውን ዝግ የባንክ ሂሳብ ለመክፈት በየቅርንጫፎቹ እየተስተዋለ ያለውን ሰልፍ ለማቅለል መፍትሄ እያዘጋጀሁ ነው አለ፡፡
ባንኩ  እንዳለው የሚስተዋለውን ረዥም ሰልፍ ለማስቀረት ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ከሁለት ሰአት እስከ ምሽቱ 11 ሰአት  የሚካሄደውን ምዝገባ በምሽትም ማድረግና እሁድን ተጨማሪ የስራ ቀን ማድረግም ከመፍትሄዎቹ መካካል ናቸው፡፡
ያም ሆኖ ህብረተሰቡ እስከ ሰኔ 21 ድረስ ዝግ ሂሳቡን መክፈትና ጎን ለጎንም ምዝገባውን በማካሄድ ሰልፉን ማቅለል ይችላልም ተብሏል፡፡
ባንኩ በትናንትናው እለት የቁጠባ ደብተር መስጠት የጀመረ ሲሆን ፥ በእለቱም ከ14 ሺህ የሚበልጡ ሰዎች የቁጠባ ሂሳብ ከፍተዋል፡፡ ይህ ቁጥር እስከዛሬ ረፋድም 40 ሺህ መድረሱን የባንኩ ባለስልጣናት ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቁጥር ውስጥም 2 ሺህ የሚሆኑት ብቻ ለ10/90 ሲመዘገቡ ቀሪዎች ደግሞ 20/80ን ምርጫቸው አድርገዋል ተብሏል፡፡
ሰኞ ለሚጀመረው የቤቶች ምዝገባ ከ4 ሺህ በላይ መዝጋቢ ሰራተኞች የተዘጋጁ ሲሆን ፥ በመብራት መቋረጥ ምክንያት ምዝገባው እንዳይቋረጥም በየምዝገባ ጣቢያዎቹ ጀነሬተሮች ተዘጋጅተዋል፡፡
የ 10/90 የቤት ፕሮግራም ከዚህ በፊት ያልነበረ በመሆኑ ፥ በዚህ የቤት መርሃ ግብር የሚመዘገቡ ነዋሪዎች በሚቀጥለው አመት በሚጠናቀቁት  24 ሺህ ቤቶች ቅድሚያ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡
በነዚህ የቤት መርሃ ግብሮች የሚመዘገቡ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም በሚገኙበት አገር የገንዝብ ኖት እንዲቆጥቡም በአዲስ አበባ ቤቶች ኤጀንሲ በኩል መልእክት ተላልፏል፡፡

No comments:

Post a Comment