Monday, May 20, 2013

የግሉን ዘርፍ በሙስና ወንጀል ተጠያቂ የሚያደርግ አዋጅ ሊወጣ ነው

አዲስ አበባ ፣ግንቦት 10 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌደራል ስነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን የግሉን  ዘርፍ  በሙስና ወንጀል ተጠያቂ የሚያደርግ አዋጅ  ለመደንገግ በወጣው ረቂቅ አዋጅ ላይ ከህብረተሰቡ እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በአዲስ አበባ መክሯል።
አዋጁ ህዝባዊ ድርጅቶች ናቸው ተብለው በሚታሰቡ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች  በግል ኩባንያዎች  እና በአክሲዮን ማህበራት ውስጥ የሚፈፀሙ የሙስና የወንጀል ድርጊቶችን  ተጠያቂ የሚያደርግ አንቀፅ ተካቶበታል ።
ይህም የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ወይንም የአክሲዮን ማህበርን ወይንም የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን በሚያደራጅ ሰው ወይም ኮሚቴ በድርጅቱ ውስጥ በማስፈፀም ሂደት የህዝብ ሃብት እንዳይባክን ለመከላከልም የሚያስችል  ነው ተብሏል። 
በእነዚህ የህዝብ ድርጅቶች ውስጥ የተቀጠሩ ቋሚና ጊዜያዊ ተራ ሰራተኞችም ቢሆኑ በሙስና ወንጀል ውስጥ ከተገኙ ህጉ ተፈፃሚ ይሆንባቸዋል ።
በሚስጢር ሊጠበቁ የሚገቡ የካዝና የመጋዘን ወይም ውድ እቃ የሚቀመጥባቸው የመሳሰሉ ሳጥኖችን ቁልፎች ሆን ብሎ ወይንም በቸልተኝነት ለሌላ ሰው  አሳልፎ በመስጠት ድርጅቶች እንዲመዘበሩ ያደረጉ ሰራተኞችን ለመቅጣትም  በአዋጁ ጠንካራ ድንጋጌዎች እንዲካተቱበት ተደርጓል።
የአዋጁ መውጣትም በእነዚህ የህዝብ ድርጅቶች ላይ የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችን በማስተካከል ህጋዊ መስመርን ተከትለው እንዲተዳደሩ ያግዛልም ተብሎ ታስቧል።
በ ታደሰ ብዙዓለም ።
       

No comments:

Post a Comment