Saturday, May 11, 2013

የገቢዎች ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታና ሌሎች ተጠርጣሪዎች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ዋሉ

ግንቦት 3 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌዴራሉ የስነ ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን የገቢዎች ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታን እንዲሁም፣ምክትል ዳይሬክተሩን አቶ ገብረዋህድ ወልደ ጊዮርጊስን ጨምሮ 12 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አዋለ።
 በግለሰቦቹ ላይ በቂ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች የተሰባሰቡ ሲሆን ጉዳዩ ለፍርድ ቤት እስኪቀርብም ድረስ ተጠርጣሪዎቹ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዲቆዩ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱንም ኮሚሽኑ ገልጿል።
የፌዴራሉ የስነ ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን በህዝብና በመንግስት ንብረት ላይ የሚፈጸሙ የሙስና ወንጀሎችን ተከታትሎ አስፈላጊውን መረጃ ካሰባሰበ በኋላ በህግ ፊት አቅርቦ በማስጠየቅ ሙስናን የመከላከልና የመቆጣጠር ኃላፊነት በአዋጅ የተሰጠው አካል ሲሆን ፥ ከዚሁ መሰረታዊ ግንዛቤና ቁርጠኝነት በመነሳትም ኮሚሽኑ ከተለያዩ መንግስታዊ አካላትና ከመላው የሃገራችን ህዝብ ጋር በመደጋገፍ በተጠርጠሪዎች ላይ ህጋዊ ስርዓትን ተከትሎ ምርመራ ያካሂዳል።
በዚህም መሰረት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተለያዩ ባለ ጉዳዮችና ከንግዱ ማህበረሰብ እንዲሁም፣ከልዩ ልዩ መንግስታዊና ህዝባዊ አካላት ጥቆማዎችን ሲቀበል ቆይቷል።ጥቆማዎቹ በአንዳንድ የገቢዎችና ጉምሩክ መስሪያ ቤት ኃላፊዎችና ሰራተኞች እንዲሁም ፥በግል ንግድ በተሰማሩ ህገ ወጥ አካሄድን በሚያዘወትሩ ግለሰቦች ላይ  ያተኮሩ ነበሩ።
ኮሚሽኑ ከህዝቡ  የተቀበላቸውን እነዚህን ጥቆማዎች መነሻ በማድረግም ከብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመተባበር ጥናት ሲያደርግ ቆይቷል።በጥናቱም በቂ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን ሰብስቧል።
ኮሚሽኑ እንዳለው ጉዳዩ ለፍርድ ቤት እስኪቀርብ ድረስ ተጠርጣሪዎቹ ግለሰቦች በፖሊስ ቁጥጥር እንዲቆዩ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። በዚህም መሰረት ከፍርድ ቤት ህጋዊ የብርበራና የእስር ትዕዛዝ በማውጣት፣የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታን እንዲሁም፣ምክትል ዳይሬክተሩ አቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስን ጨምሮ 12 ያህል ተጠርጣሪዎች ናቸው፥በቁጥጥር ስር እንዲውሉ የተደረገው።
ኮሚሽኑ በአዋጅ የተሰጠውን ስልጣን መነሻ በማድረግ ተጨማሪ ምርመራውን እንዳጠናቀቀ ህጋዊ ስርዓቱን ተከትሎ ተጠርጠሪዎቹን ከተሟላ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች ጋር ለመደበኛው ፍርድ ቤት እንደሚያቀርብ ገልጿል።
ኮሚሽኑ ወደፊትም በጉደዩ ላይ እንዳስፈላጊነቱ ተጨማሪ ማብራሪያ እንደሚሰጥ አመልክቷል።
በዚህ አጋጣሚም መላው የሃገራችን ህዝብ መንግስት ሙስናን ለመዋጋት ለሚያደርገው ጥረት የተለመደ ትብብሩን እንዲቀጥል ጠይቋል።

No comments:

Post a Comment