Sunday, May 5, 2013

የእርድ በሬ ከባሌ ሲመጣ እስከ 3ሺ ብር ተጨምሮበት ይሸጣል


የእርድ በሬ ከባሌ ሲመጣ እስከ 3ሺ ብር ተጨምሮበት ይሸጣል አምና በዚህ ጊዜ የሽንኩርት ዋጋ በአንድ ኪሎ እስከ 19 ብር ደርሶ ሕዝቡን ሁሉ እያንጫጫ ነበር፡፡ ሰሞኑን ግን አንድ ኪሎ እስከ 9 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ የፍየል፣ የበግና የቅቤ ዋጋ ግን ንሯል፡፡ በሾላ ገበያ አንድ ፍየል ጉድ በሚያሰኝ የማይታመን ዋጋ መሸጡን በአካባቢው ያገኘናቸው ደላሎች ነግረውናል 5,500 ብር፡፡ በጥቅሉ ግን፣ የዘንድሮ ገበያ ከአምናው ጋር ሲነፃፀር ጥሩ መሆኑን ያነጋገርናቸው ሸማቾች ነግረውናል፡፡ ገበያው የሚጧጧፈው ቅዳሜ ዕለት ስለሆነ ትክክለኛውን የገበያ ሁኔታ መናገር እንደሚከብድ የተናገሩ አንዳንድ ነጋዴዎች በበኩላቸው፤ የሁለትና የሦስት መቶ ብር መጠነኛ ጭማሪ ቢኖርም ገበያው የተረጋጋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሾላ ገበያ አንድ አዛውንት ከሾላ የከብት ገበያ በግ ገዝተው እያስጐተቱ ወደቤታቸው ያመራሉ፡፡ “ስንት ገዙት?” አልኳቸው፡፡
በአጭሩ 1,200 ብር ብለው ጉዟቸውን ቀጠሉ፡፡ መካከለኛ ዕድሜ ያለው ፈርጠም ያለ ሰው ትልቅ ፍየል እያስነዳ ሲሄድ አስቁሜው “ስንት ገዛኸው?” አልኩት፡፡ ይሄ ተጫዋች ነው፡፡ “እስቲ ገምት” አለኝ፡፡ “ከብት” ገዝቼ እንደማላውቅ ነገርኩት፡፡ “2,000 ብር” ካለኝ በኋላ “ከገበሬዎች ነው የገዛሁት፡፡ የነጋዴዎቹን ዋጋ አትችለውም፡፡ ከገበሬዎቹ ገዝተው ነው የሚያተርፉብህ፡፡ ወደ ላይ ውጣና ገበሬዎቹን ለማግኘት ሞክር” ብሎኝ ሄደ፡፡ የሾላ ገበያ መግቢያው አካባቢ ነጋዴዎች፤ በጐችና ፍየሎችን ከወዲያ ወዲህ ይነዳሉ፡፡ ላዳ ታክሲዎች ከመንገዱ ግራና ቀኝ ቆመው ገዢ ይጠባበቃሉ፡፡ ትናንሽና ትላልቅ የቤት መኪኖች የመንገዱን ጠርዝ ይዘው ተደርድረዋል፡፡ ነጣ ያለውን በግ ወገብ ያዝ ያዝ አድርጌ “ስንት ነው?” አልኩት፡፡ ነጋዴው ፈርጠም ብሎ “30” አለኝ፡፡አልገባኝም፡፡ ግር መሸኘቴን አይቶ “3ሺህ” አለኝ፡፡ ፈርጠም ያለውን ዳለቻ በግ ደግሞ በጣቴ እያመለከትኩ “ያ ስንት ነው?” በማለት ጠየቅሁ፡፡
“35” አለኝ፡፡ ሦስት ሺህ 500 ብር ማለቱ ነው፡፡ የዋጋ ጥሪው የመሸጫ ዋጋ ባይሆንም ከክርክር በኋላ ትልቁን በግ እስከ 3ሺህ ብር እንደሚያደርሱት ሰምቻለሁ፡፡ መካከለኛና አነስ ያለ በግ 1500 ብር ይገኛል፡፡ መካከለኛና አነስ ያለ ፍየል፣ ከ2ሺ እስከ 2500 ብር ይሸጣሉ፡፡ በሾላ ገበያ ነጭ የአደአ ማኛ ጤፍ በኩንታል ከ1600 እስከ 1680 ብር ሲሆን፣ ሰርገኛ ጤፍ እንደየደረጃው በኪሎ 14 ወይም 15 ብር ነው፡፡ በቆሎ፤ ከ5 እስከ 6 መቶ ብር፣ ስንዴ ከ8 እስከ 9መቶ ብር፣ ገብስ ከ7 እስከ 9መቶ ብር ሲሸመት ሰንብቷል፣ የውጭው ሩዝ በኪሎ 14 ብር፣ የአገር ውስጥ ደግሞ ከአስር እስከ 12 ብር ይገኛል፡፡ ፉርኖ ዱቄት በኪሎ 11 ብር ገደማ ነው፡፡ ጐመን ዘር የተፈጨ በጣሳ ሃያ ብር፣ ነጭ ሽንኩርት በኪሎ 25 ብርና ዝንጅብል 15 ብር ሲሆን፤ ቡና የይርጋጨፌ በኪሎ 98 ብር፣ የሐረር መቶ ብር፣ የወለጋ 95 ብር፣ የጅማ 80 ብር ለግብይት ቀርቦ ነበር፡፡
ፈንዲሻ ደግሞ ሩብ ኪሎ 15 ብር ሲሸጥ ውሏል፡፡ ቅቤ ሸኖ ለጋ በኪሎ 175 ብር፣ መካከለኛው 155 ብር፣ የበሰለ 145 ብር ሲሸጥ ሰንብቷል፡፡ እንቁላል 2.40 ብር፣ ቀይ ሽንኩርት የአበሻ 13 ብር፣ ባሮ 8 ብር ሲሸጥ አይተናል፡፡ በሾላ ገበያ የቡና፣ የቅቤ፣ የሽንኩርት፣ የዕንቁላል ዋጋ የተመኑት ይመስላል - ሲዞሩ ቢውሉ የዋጋ ለውጥ የለውም፤ በሁሉም ቦታ ተመሳሳይ ነው፡፡ ዶሮ እንደየዓይነቱ ከ120 እስከ 150 ሲሸጥ ነበር፡፡ እናትና ልጅ ዶሮ ገዝተው ሌላ ነገር ለመሸመት ሲዞሩ አግኝቼ፤ “ገበያ እንዴት ነው?” አልኳቸው፡፡ ልጅቷ ትንሽ አመንትታ፣ “ጥሩ ነው” አለች፡፡ “አምና ሽንኩርት እስከ 19 ብር ሲሸጥ ነበር፡፡ ዛሬ 8 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ ዶሮም ጥሩ ነው፡፡ እነዚህን ዶሮዎች (እግሯ ስር ወዳሉት ዶሮዎች እያመለከተች) እያንዳንዱ 120 ብር ነው የተገዛው፡፡ ጥሩ ነው የሚመስለው” አለችኝ፡፡ ሦስት ዶሮዎች ገዝቶ ወደ ቤታቸው ሲያመሩ ያገኘኋቸው ጐልማሳ፤ አንዱን ዶሮ በ150 ብር፣ ሌሎቹን ሁለት ዶሮዎች በ130ብር ሂሳብ መግዛታቸውን ነግረውኛል፡፡ የሴት ዶሮ ዋጋ 80 ብር ነበር፡፡ ታዲያ የነጋዴዎቹ ጥሪ ከ120 እስከ 170ብር ይደርሳል፡፡ ገርጂ ገበያ ሁለት ትላልቅ ዶሮዎች አንጠልጥለው ያገኘኋቸው አዛውንት እያንዳንዱን በ120 ብር እንደገዙ ነግረውኛል፡፡ “እነዚህ የጐጃም ናቸው፡፡ ከታች ከወደጉራጌ የመጡት 150ብር ይባላሉ፡፡ ኧረ ዘንድሮስ ተመስገን ነው” አሉኝ፡፡
ጠና ያሉ ሁለት ዘመናዊ ሴቶች ትልልቅ የሚባሉ አራት ዶሮዎች በ160 ብር ሂሳብ እንደገዙ ነግረውኛል፡፡ የተለያዩ ዶሮዎችን ዋጋ ስጠይቅ ቆይቼ፤ አንዱን ነጋዴ “ዘንድሮ የዶሮ ገበያ እንዴት ነው?” አልኩት፡፡ “አሁን ገበያው ስላልጦፈ ምን ይታወቃል?” ገበያውኮ ገና ነው” አለኝ ረቡዕ ዕለት፡፡ በገርጂ ወደተሠራው ዘመናዊ የአትክልትና ፍራፍሬ ማዕከልም ጐራ ብያለሁ፡፡ ቀይ ሽንኩርት በኪሎ ከ7 እስከ 8.50 ሲሸጥ፣ ፎሶሊያ በኪሎ ከ12 አስከ 15 ብር፣ ቲማቲም ከ12 እስከ 13 ብር፣ ቃሪያ በኪሎ 24 ብር፣ ካሮት 14 ብር፣ ድንች ሰባት ብር፣ ነጭ ሽንኩርት ከ22 እስከ 24 ብር፣ ዝንጅብል ከ12 እስከ 14 ብር ይሸጣል፡፡ ከማዕከሉ ገዝታ የምትወጣ አንዲት ጋዜጠኛ አግኝቼ፣ “የገበያ ማዕከሉ ዋጋ እንዴት ነው?” አልኳት፡፡ “ያስወድዳሉ፡፡ በፒያሳ የአትክልት ተራ ዋጋ የማገኝ መስሎኝ ነበር፡፡ ግን አይደለም፡፡ ሽንኩርት ከ7.50 እስከ 8 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ በዚህ ዋጋማ በሰፈሬም አገኛለሁ፡፡ ሸክም ብቻ ነው የተረፈኝ፡፡ አትክልት ተራ እስከሆነ ድረስ ቅናሽ ማሳየት ነበረበት” በማለት አማርራለች፡፡ ካዛንቺስ ገበያ በዚህ ገበያ ዕንቁላል 2.50፣ ሸኖ ለጋ ቅቤ 200 ብር፣ ዶሮ ከ150 እስከ 175 ብር፣ ሽንኩርት ደግሞ 7 ብር ሲሸጥ ነበር፡፡ ከሳምንት በፊት ግን፣ ሽንኩርት በአራት ብር፣ ሸኖ ለጋ ቅቤ 140 ብር ተሸጧል፡፡ ነጋዴዎቹ ለዋጋው መጨመር የሚሰጡት ምክንያት፣ ዝናቡ ዘግይቷል የሚል ነው፡፡

No comments:

Post a Comment