Tuesday, February 19, 2013

የመገናኛ ብዙሃን የድምጻዊውን ዜማ ባስደመጠ ቁጥር ለድምጻዊው የሚከፍልበት የአገልግሎት ክፍያ ህግ እየተዘጋጀ ነው

የኢትዮጽያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት የአገልግሎት ክፍያ ወይም ሮያሊቲ ፊ ህግ እያዘጋጀ መሆኑን አስታወቀ። ህጉ አንድ ድምጻዊ ዜማዎቹ በተደመጡ ቁጥር ተጠቃሚ የሚሆንበት ነው።
ከዚህ ቀደም ይህ ህግ ባለመኖሩ ያለ ድምጻዊው ፍቃድ ዜማዎቹ በህገ ወጥ መንገድ ይደመጡ የነበረ ሲሆን ፥ ህጉ ተግባራዊ ከሆነ በኋላ ግን የትኛውም የመገናኛ ብዙሃን የድምጻዊውን ዜማ ባስደመጠ ቁጥር ለድምጻዊው የሚከፍልበት ሁኔታም ይፈጠራል።
ከዚህ ጋር በተያያዘም መገናኛ ብዙሃኑ  የሚያስደምጡትን ዜማ የሚቆጣጠር ሶፍት ዌርም መመረቱን ነው የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ አዴሎ የሚናገሩት።
ይህ ሲሆን ድምጻውያኖቹ በየጊዜው ጥቅማቸው ስለሚከበርላቸው   ከሚያገኙት ገቢ  ወደ ተሻለ  የኑሮ ደረጃ ይደርሳሉ ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።
የህግ ማእቀፉን ለማስተካከል እየተሰራ ሲሆን ፥ በጽህፈት ቤቱ  የተዋቀረው የብሄራዊ አዕምሯዊ ንብረት የቴክኒክ ኮሚቴም የቅጅና ተዛማጅ መብቶችን የሚፈታተኑ እንቅፋቶችን በጥናት እየለየ ነው።
የኮሚቴው ሰብሳቢና በጽህፈት ቤቱ የቅጅና የማህበረሰቦች እውቀት ጥበቃና ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተድላ ማሞ እንዳሉት ፥ የኮሚቴ አባላቱ ችግሮቹን የለዩ ቢሆንም ለባለድርሻ አካላት ፣ በዘርፉ ለሚሰማሩ የንግዱ ማህበረሰብ የእውቅና ፍቃድ ሲሰጡ እነዚህን መብቶች ከህግ ጋር አስተሳስሮ ያለመስራት ዋነኛው እንቅፋት ሆነዋል።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርም ይሁን ሌሎች ቢሮዎች  አንድ ፊልም በሲኒማ ቤት  እንዲታይ የእውቅና  ፍቃድ ሲሰጡ ፥ የቅጂና ተዛማጅ መብቶችን ያለማገናዘባቸውን በምሳሌነት አንስተዋል።
የጽህፈት ቤቱ  ዋና ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ አዴሎ  ፥ ዲጄ  የቅጂ መብቶች እና ተዛማጅ መብቶች ወቅታዊ ጋሬጣ በመሆኑ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት መፍትሄ ሊበጅለት እንደሚገባ ነው የጠቆሙት።

No comments:

Post a Comment