Tuesday, January 8, 2013

የእኛ ሰዎች በየመን

“ህይወት ውሳኔ ነው”
የሃፍቶም ልብ ሳኡዲን አልሟል - መንገዱን ማን ያሳየው?
ስመጥሩው ፀሀፌ ተውኔት ዊልያም ሼክስፒር “The Tempest” በተሠኘው ተውኔቱ “መከራና ችግር ሰዎች ጨርሰው ከማያውቋቸው ጋር እንዲጐዳኙ ያስገድዳቸዋል” ይላል፡፡ በእርግጥም የሠው ልጅ ቀን አዘንብሎበት አስቸጋሪና የመከራ ጊዜ ሲገጥመው፣ በመልካሙ ጊዜ አብሯቸው ሊውል ከማይፈልጋቸው ወይንም ጨርሶ ከማያውቃቸው እንግዳ ሰዎች ጋር ወዳጅነት ወይም አጋርነት ይመሰርታል፡፡ አበሻ “የጨነቀው እርጉዝ ያገባል” እንደሚለው መሆኑ ነው፡፡
ሀፍቶም ግደይ የሚመራው ህይወት ከማይጨው እስከ ጅቡቲ ድረስ ባሳለፈው ጉዞ ወቅት የወሰዳቸው ውሳኔዎች ውጤት ነው፡፡ ተወልዶ ያደገበትን የማይጨው ቀዬና የሚወዳቸውን ቤተሠቦቹን ሳይሠናበታቸው ወደ ደሴ ጠፍቶ እንዲሄድ ያደረገው፣ ከደሴ ወደ ኮምቦልቻና አዲስ አበባ፣ከዚያም እንኳን በእውኑ በህልሙም አስቧት ወደማያውቃት ጅቡቲ ያሰደደውን ውሳኔ እንዲወስን ያስገደደው ግን ሼክስፒር እንዳለው ያጋጠመው መከራና ችግር ብቻ ነው፡፡
ችጋር የመከራን ቀን ያረዝማል፡፡ መከራ ሲረዝም ልብንና ቀልብን ይነሳል፡፡ እንዲህ ያለ እጣ ሲወጣ ደግሞ ልብ ቀኙን ሀሳብ ወደ ግራ አዙሮ ማሠቡ፣ አይንም ጥቁሩን አንጥቶ አጥቁሮ ማየቱ አይቀርም፡፡ የሀፍቶም ልብና አይንም ጅቡቲን እንዲያ ነጭና ብሩህ አድርጐ ያያት፣ እድሜ ዘመኑን ሙሉ እግር ተወርች አንቆ የያዘውን ችጋሩንና መከራውን ከነሠንኮፉ ነቅሎ የሚጥልባት የአለምና የሲሳይ ሀገር እንደሆነች አድርጐ የሳላትም በዚህ የተነሳ ነበር፡፡
ዝሆን የፈለገውን ያህል ቢከሳ የጫካው ግዙፍ እንስሳ እሱ ብቻ ከመሆን ምንም የሚያግደው ነገር አይኖርም፡፡ ሀፍቶም ስንት መከራና ስቃይ ተቀብሎ ጅቡቲ ከገባ በኋላ፣ ያን በእጅጉ የጓጓላትን ተአምሯን ሳትውልና ሳታድር እንደምታሳየው እርግጠኛ ነበር። ጅቡቲ ግን ጅቡቲ ነበረች፡፡ ሀፍቶም ጅቡቲን በተመለከተ የእዉቀት ማነስ የበኩር ልጅ እንደሆነ ለመረዳት የፈጀበት ጊዜ አንድ አመት ከሶስት ወር ነበር፡፡ ስለ ጅቡቲ የሲሳይና የተስፋ ሀገርነት በልቡና በአዕምሮው በጉልህ ቀለም የሳለው ስዕል፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ ቀስ በቀስ እየደበዘዘና እየጠፋ ሲመጣ፣ሳኡዲ አረቢያ አዲሷ የተስፋና የሲሳይ ሀገር ሆና በልቡና አዕምሮው ውስጥ ብቅ አለች፡፡
ተስፋ የህይወት ምሰሶ ነው፡፡ ህይወት ካለ፣ ተስፋ ማድረግም ይኖራልና ሀፍቶምም ልክ ጅቡቲን ሲያስባትና ሲያልማት እንደነበረው ሁሉ፣ ስለ ሳኡዲ አረቢያም በእውኑም በህልሙም ማሰቡንና መመኘቱን ቀጠለ፡፡ ጅቡቲ ውስጥ ሆኖ ወደ ሳኡዲ አረቢያ መሄድ ጨርሶ እንደማይችል የተረዳው ግን እንዳለፈው ከአንድ አመት ከሶስት ወር በኋላ ሳይሆን ወዲያውኑ ነበር፡፡ ዝናብ መቼም ቢሆን የአንድን ቤት ጣሪያ ብቻ ለይቶ አይመታም፡፡ ጅቡቲም ለሀፍቶም ብቻ ተለይታ የማትደላ ሀገር፣ ለሀፍቶም ብቻ ተለይታ ሲኦል የሆነች ሀገር አልነበረችም፡፡ በጉያዋና በጓዳ ጐድጓዳዋ በሺ የሚቆጠሩ የሀፍቶም ቢጤዎችን አጭቃ ይዛ ነበር፡፡
ከእለታት ባንዱ ቀን ታዲያ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ጋር ሸቀጥ ጭኖ ለመውጣት ወረፋ ከሚጠብቅ ረጅም የጭነት መኪና ስር ተኝተው የባጥ የቆጡን እያነሱ ሲያወሩ፣ ሃፍቶም ለቀናት በውስጡ ሲያብሰለስለው የነበረውን ሀሳብ ድንገት ሰነዘረ፡፡
“እዚ ጅቡቲ አንድ አመት ከሶስት ወር አደረኩ፡፡ አሁን የምፈልገው ሳኡዲ አረቢያ መሻገር ነው” አለ፡፡
“ኧ! ከጅቡቲ ሳኡዲ ልትገባ? ወዳጄ ይህን ጨርሶ አታስበው!” አለው አንዱ፡፡
“ዋይ! ንምንታይ? ማለቴ ለምን?” ሀፍቶም ጆሮውን ብቻ ሳይሆን መላ የስሜት ህዋሳቶቹን በማንቃት መልስ ጠየቀ፡፡
“አይቻልማ! ከዚህ እንዴት አድርገህ መሄድ ትችላለህ? ሳኡዲ ከዚህ እንደ ወደብ መሠለህ?” የመጀመሪያው ልጅ መልስ ሰጠው፡፡ ሀፍቶም ቀጣዩን ጥያቄውን ምን ብሎ እንደሚጠይቅ እያሰበ እያለ፣ ሌላኛው ልጅ ከተራ ቀልድ ይልቅ የማሾፍ ቃና ባለው አነጋገር “በዋና አቋርጦ መሄድ ይችላል፡፡ ጅዳ ምን አላት! እዚች እኮ ናት” አለው፣በቀኝ እጁ የሌባ ጣት ርቀቱን ለማመልከት እየጠቆመ፡፡ ሀፍቶም ለዚህ ልጅ መልስ አልሰጠውም፡፡ በሆዱ ግን ልጁን ሠደበው “ሀሳስ” (ጅል ሞኝ እንደማለት) ወዲያውኑ ግን የመጀመሪያው ልጅ የሀፍቶም ልብና ጆሮ ሊሠማው የሚፈልገውን መልስ ሲናገር ሰማው፡፡ ፊቱ በደስታ ፈካ፡፡
“ወዳጄ! ወደ ሳኡዲ ለመሻገር የምትፈልገው የምርህን ከሆነ፣ሂድ ወደ ሶማሊያ ቦሳሶ --- ከቀናህ መርከብ ካልቀናህ ደግሞ የሶማሌ ጀልባ አታጣም”
ሀፍቶም ከጅቡቲ ተነስቶ ወደ ሳኡዲ አረቢያ የሚያስኬደው መንገድ የትኛውና አቅጣጫውም በየት በኩል እንደሆነ ጨርሶ አያውቀውም ነበር፡፡ ስሜቱን ወጥሮ ይዞት የነበረው ቁልፍ ጥያቄም ይህ ነበር፡፡ አሁን ግን ድንገት ሳያስበው ቁልፍ ለሆነው ጥያቄው ቁልፍ የሆነውን መልስ ማግኘት ቻለ፡፡ እናም ከፍተኛ የሆነ ደስታ ተሰማው፡፡ ፊቱም መንፈሱም ፈካ፡፡
ሀፍቶም የአዲስ ጉጉቱና ምኞቱ አዲሷ ሀገር ወደሆነችው ሳኡዲ አረቢያ የሚያስገባው በር በሶሚሊላንድ በኩል እንደሆነ ሲያውቅ “በታላቋ የሮም ከተማ ሁለተኛ ከመሆን በትንሿ መንደር ውስጥ አንደኛ መሆን ይሻላል” በሚል የያዙትን የማጥበቅና በያዙት የመርጋትን ነገር ጨርሶ ችላ በማለት፣ ወደ ሶማሊላንድ የቦሳሶ ከተማ ለመሄድ የመውጫው ኬላ በየት በኩል እንደሆነና ኬላውንም ማለፍ የሚቻለው እንዴት ተደርጐ እንደሆነ ለማወቅ ተጣደፈ፡፡ ይሁን እንጂ ለእነዚህ ሁለት ቀላል ነገር ግን ቁልፍ የሆኑ ጥያቄዎቹ አጥጋቢ መልስ ካላገኘ በስተቀር እግሩን እንደማያነሳ ወስኖ ነበር፡፡ ከዛሬ አንድ አመት ከሶስት ወር በፊት በጅቡቲ መግቢያ ኬላ ላይ ያጋጠመው ሁኔታና የተቀበለው መከራ፣ ምንጊዜም ቢሆን ዘውድ መጫን ለራስምታት መድሃኒት ሊሆን እንደማይችል በሚገባ አስተምሮታል፡፡
ሃፍቶም ወደ ሳኡዲ አረቢያ የሚያስገባው በር የሶማሊላንዷ የቦሳሶ ከተማ መሆኗንና ወደ እሷም የሚወስደውን የመንገድ ኬላ እንዴት አድርጐ ማለፍ እንደማችል በሚገባ ከተረዳ በኋላ ግን ተጨማሪ ጊዜ በጅቡቲ ማጥፋት አልፈለገም፡፡ ከኢትዮጵያ ወደ ጅቡቲና ከጅቡቲ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመላለሱት አይነት አይሁኑ እንጂ አልፎ አልፎ ከጅቡቲ ሸቀጥ ጭነው፣ የሶማሊላንድ ዋና ከተማ ወደ ሆነችው ቦሳሶ የሚጓዙ የጭነት መኪናዎች ስላሉ በእነሱ ተሳፍሮ መጓዝ ይችል ነበር፡፡
ይህን አይነት አገልግሎት ለማግኘት ግን ክፍያ መክፈል የግድ ነው፡፡ ክፋቱ ግን ሀፍቶም ለመጓጓዣ የሚሆን ድንቡሎ ፍራንክ እንኳ አልነበረውም፡፡ መርከቧ እንዳለ ከምትሰምጥ ግን መልህቋን ብታጣ የተሻለ ነው፡፡ እናም ሀፍቶም ግደይ ከጅቡቲ ወደ ቦሳሶ ያለውን መንገድ በእግሩ አስነካው፡፡

No comments:

Post a Comment